የእሳተ ገሞራ አደጋ ባንዣበበበት አካባቢ መኖርና መስበክ
“አስፈሪ የሆነ የሕይወት ገጠመኝ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ከሚናገርለት የዓለም መጨረሻ ጋር ሊመሳሰል የሚችል ነበር። በእያንዳንዷ ዕለት በይሖዋ ፊት ጥሩ አቋም በመያዝ በንቃት መመላለስ አለብን።” ይህን የተናገረው ቢክቶር የተባለ አንድ የይሖዋ ምሥክር ሲሆን በሜክሲኮ በሚገኘውና በተለምዶ ፖፖ ተብሎ በሚጠራው የፖፖካቴፔትል እሳተ ገሞራ አቅራቢያ ይኖር በነበረበት ጊዜ ያጋጠመውን ሁኔታ ለመግለጽ የተጠቀመው በእነዚህ ቃላት ነበር።
ይህ የጉምጉምታ ድምፅ ያለው እሳተ ገሞራ ከ1994 ጀምሮ ዓለም አቀፋዊ ዜና ሆኖ ነበር።a ባለ ሥልጣናት ከገሞራ ቆሬው (crater) በ30 ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ነገር ለከፍተኛ አደጋ የተጋለጠ ይሆናል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰው ነበር። ገሞራ ቆሬው ወደ ደቡብ አቅጣጫ ያዘነበለ በመሆኑና በገሞራ ቆሬው በኩል ገሞራ ፍስና (lava) ጭቃ ሊተፉ የሚችሉ ጥልቀት ያላቸው በርካታ ሸለቂቶች (ravines) በመኖራቸው በተለይ በእሳተ ገሞራው በስተ ደቡብ ያለው አካባቢ ለከፍተኛ አደጋ የተጋለጠ ነበር።
እሳተ ገሞራው በከፍተኛ ኃይል ቢፈነዳ ሜክሲኮ ሲቲ ምን ይደርስባት ይሆን እያሉ ያሰቡ ብዙዎች ነበሩ። ከተማዋ ለአደጋ የተጋለጠች ትሆን? ከዚህም በላይ ከእሳተ ገሞራው በስተ ደቡብ በምትገኘው በሞሬሎስ ግዛት የሚኖሩ ሕዝቦችም አሉ። በዚያ አካባቢ የሚኖሩ ሁሉ አደጋው ያሰጋቸው ይሆን? እንዲሁም እያንዳንዱ ቀን ምን ይዞ እንደሚመጣ በማይታወቅበትና የእሳተ ገሞራ አደጋ ባንዣበበበት አካባቢ መኖር ምን ስሜት ይፈጥራል?
እሳተ ገሞራው ያስከተለው ስጋት
የሜክሲኮ ሲቲ መሃል ከተማ ከፖፖካቴፔትል ሰሜናዊ ምዕራብ በ70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ቢሆንም ከመሃል ከተማው ወጣ ያሉ አንዳንድ የመኖሪያ አካባቢዎች ግን 40 ኪሎ ሜትር ያህል የተጠጉ ናቸው። ሃያ ሚልዮን የሚያክል ሕዝብ የሚኖርባቸው የከተማው የመኖሪያ አካባቢዎች ከአደጋ ቀጠና ውጭ ናቸው ለማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ በነፋስ አቅጣጫ ላይ የተመካ ቢሆንም እሳተ ገሞራው ከፍተኛ መጠን ያለው አመድ ከተፋ ይህ አካባቢ ጉዳት ሊደርስበት ይችላል።
ከእሳተ ገሞራው የሚወጣው አመድ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትለው በአብዛኛው በእሳተ ገሞራው በስተ ምሥራቅ ባለው አካባቢ ላይ ነው። ይህ አካባቢ የፑኤብላን ከተማ እንዲሁም በርካታ ቁጥር ያላቸውን አነስተኛ ከተሞችና መንደሮች የሚያካትት ሲሆን 200,000 የሚያክሉ ሰዎች በዚህ ከፍተኛ አደጋ በተደቀነበት አካባቢ ይኖሩ ነበር። እሑድ ግንቦት 11, 1997 እሳተ ገሞራው ወደ አየር የተፋው ብዙ ቶን የሚመዝን አመድ ወደ እነዚህ አካባቢዎች ከመሰራጨቱም በላይ በስተ ምሥራቅ በኩል 300 ኪሎ ሜትር በላይ ርቆ እስከሚገኘው እስከ ቫራክሩዝ ግዛት ድረስ ዘልቆ ነበር። ከእሳተ ገሞራው በስተ ደቡብ የሚገኘው የሞሬሎስ ግዛት አካባቢ ለከፍተኛ አደጋ ሊጋለጡ የሚችሉ ወደ 40,000 የሚጠጋ ሕዝብ የሚኖርባቸው በርካታ ከተሞችና መንደሮች አሉ።
በዚህ ሁሉ መኻል የሚኖሩና የሚሠሩ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ። በሜክሲኮ ሲቲ 1,700 በሚያክሉ ጉባኤዎች የታቀፉ ከ90,000 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኛሉ። የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ ከሜክሲኮ ሲቲ ሰሜን ምሥራቅ በኩል ወጣ ብሎ ከእሳተ ገሞራው 100 ኪሎ ሜትር በሚሆን ርቀት ላይ ይገኛል። ከ800 የሚበልጡ ፈቃደኛ ሠራተኞች በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ የሚያገለግሉ ሲሆን 500 የሚሆኑ ሌሎች ፈቃደኛ ሠራተኞች ደግሞ በከፍተኛ የግንባታ ፕሮጀክት ላይ ተሠማርተዋል። ሁሉም ከአደጋ ቀጠናው ውጪ ናቸው።
በሞሬሎስ ግዛት ውስጥ ከ2,000 የሚበልጡ አስፋፊዎችን ያቀፉ ወደ 50 የሚጠጉ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች አሉ። ከእነዚህ ጉባኤዎች መካከል አንዳንዶቹ በቴቴላ ዴል ቦልካን እና በዌያፓን የሚገኙ ሲሆን ከገሞራ ቆሬው የሚርቁት 20 ኪሎ ሜትር ያህል ብቻ ነው። ከዚህም በተጨማሪ በስተ ምሥራቅ በኩል በሚገኘው የፑኤብላ ግዛት ከእሳተ ገሞራው በ20ና በ30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ 600 የሚሆኑ አስፋፊዎች ያሏቸው ጉባኤዎች አሉ። እነዚህ ቦታዎች ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስባቸው እንደሚችል የተረጋገጠ ነው።
የይሖዋ ምሥክሮች ዘወትር ንቁዎች ናቸው
የማያቋርጥ ስጋት ቢያንዣብብባቸውም በዚህ አካባቢ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች የስብከት ሥራቸውን አላቆሙም። እንዲሁም በዚህ አስፈሪ ሁኔታ ሥር አንድነታቸውንና የመተማመን መንፈሳቸውን እንዲጠብቁ አስተዋጽኦ በሚያደርጉላቸው ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረው መገኘታቸውን አላቋረጡም። (ዕብራውያን 10:24, 25) ከአንደኛው ጉባኤ የመጣ ሪፖርት እንዲህ ይላል:- “ሕዝቡ ለመንግሥቱ ምሥራች ያለው አመለካከት አስገራሚ በሆነ መንገድ በመለወጥ ላይ ነው። ለምሳሌ ያህል በአንዲት ትንሽ መንደር የሚኖሩ 18 ሰዎች በቅርቡ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላቸው የቀረበላቸውን ግብዣ ተቀብለዋል።”
ከእሳተ ገሞራው በ20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ አንድ ሌላ ጉባኤ ደግሞ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “የሚታየው እድገት በጣም ከፍተኛ ነው። ይህ ጉባኤ የተመሠረተው በኅዳር 1996 ነበር። በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ውስጥ 10 ግለሰቦች በመስክ አገልግሎት ለመካፈል ብቁ ሆነዋል። የአንዳንድ አስፋፊዎች መኖሪያ ከገሞራ ቆሬው የሚርቀው 20 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው። ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የሚደረጉት እዚያው ሲሆን ወደ 40 የሚጠጉ ሰዎች በስብሰባው ላይ ይገኛሉ።”
ከእሳተ ገሞራው 25 ኪሎ ሜትር ብቻ ርቆ በሚገኘው በሳን አጉስቲን ኢክስታዊክስትላ፣ ፑኤብላ የምትኖረው ማግዳሌና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በንቃት ስትመራ ቆይታለች። አንድ ከባድ ፍንዳታ ከደረሰ በኋላ ስለሆነው ነገር እንዲህ በማለት ትተርካለች።
“ቤታችንን ጥለን እንድንሸሽ ስለተነገረን ከበላያችን የአመድ ዝናብ እየወረደብን ሽሽታችንን ተያያዝነው። አጣዳፊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም መጽሐፍ ቅዱስ አስጠናቸው የነበሩት የዶራዶ ቤተሰብ ትዝ አሉኝ። እኔና ጥቂት ወንድሞች ወደ ዶራዶ ቤት ሄድንና ሰላማዊ ወደሆነ ቦታ እንዲሄዱ ረዳናቸው። በአቅራቢያችን በምትገኘው በፑኤብላ ከተማ የይሖዋ ምሥክሮች የእርዳታ ኮሚቴ ሥራውን ቀደም ብሎ ጀምሮ ነበር። የዶራዶ ቤተሰብ በተደረገልን እንክብካቤ በጣም ተገረሙ። ክርስቲያን ወንድሞቻችን በተለያዩ ቦታዎች ለማረፍ እንድንችል አስቀድመው ዝግጅት አድርገውልን ነበር። የምንኖረው ከቤታችን ርቀን ቢሆንም ምንም ነገር አልጎደለብንም። ይህ ቤተሰብ በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ በሚደረጉ አንዳንድ ስብሰባዎች ላይ ይገኝ ነበር። ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም ፈጽሞ አይተዋቸው የማያውቁ ወንድሞች ባሳዩአቸው ፍቅር በጣም ተደነቁ። ወደ መኖሪያ ቤታችን ከተመለስን ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ይህ ቤተሰብ በሁሉም ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ መገኘት ጀመረ። ከጥቂት ጊዜ በኋላም የምሥራቹ አስፋፊ ለመሆን ብቁ ሆኑ። አሁን ሁለቱ ተጠምቀዋል። ለተወሰኑ ወራት ረዳት አቅኚ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን ወደ ዘወትር አቅኚነት አገልግሎት ለመግባት ዝግጅት በማድረግ ላይ ናቸው።”
ከገሞራ ቆሬው 21 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትኖረው የ20 ዓመቷ ማርታ የአካል ጉዳተኛ መሆኗ ለመስበክ የሚያስችላትን እያንዳንዱን አጋጣሚ ከመጠቀም እንዲያግዳት አልፈቀደችም። እውነትን የተማረችው ከሦስት ዓመት በፊት እሳተ ገሞራው እንደገና ንቁ በሆነበት ጊዜ ነበር። በምትኖርበት አካባቢ ያለው ዳገታማ መሬት በተንቀሳቃሽ ጋሪዋ መጓዝን አስቸጋሪ ስለሚያደርግባት በስብከቱ ሥራ የምትካፈለው አህያ ላይ ተቀምጣ ነበር። ወደ ስብሰባዎች የምትሄደው በዚያው አህያ ላይ ሆና ነው። ማርታ አህያው ላይ የሚያወጧትና ከአህያው የሚያወርዷት በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ እህቶች በመሆናቸው የዚህ አፍቃሪ የሆነ የወንድማማች ማኅበር አባል በመሆኗ ይሖዋን ከልብ ታመሰግነዋለች። በየወሩ ከ15 የሚበልጥ ሰዓት ለአገልግሎት ታውላለች።
በእነዚህ ገለልተኛ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ጎረቤቶቻቸው በሚያከብሯቸው ሃይማኖታዊ በዓሎች ላይ እንዲካፈሉ ብዙ ጊዜ ግፊት ይደረግባቸዋል። ከእሳተ ገሞራው 20 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ቱልሲንጎ በሚባል መንደር የሚኖር አንድ ሰው ለበዓሉ ድግስ የሚውል ገንዘብ ከእያንዳንዱ ምሥክር እንዲያሰባስብ ይላካል። ወንድሞች በእነዚህ ሃይማኖታዊ በዓላት ላይ የማይካፈሉት ለምን እንደሆነ ረጋ ብለው አስረዱት። ሰውዬው ከወንድሞች ገንዘብ ለማግኘት ሲል ሁልጊዜ ይመላለስ ስለነበረ ከምሥክሮቹ ጋር መቀራረብ ጀመረ፤ እንዲሁም አንዳንድ እምነቶቻቸውን ሊያውቅ ቻለ። ለሚጠይቃቸው ጥያቄዎች የሚሆኑ መልሶች ከራሱ የካቶሊክ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በማግኘቱ በጣም ተደሰተ። ከሚስቱና ከሴት ልጁ ጋር ሆኖ ለአንድ ዓመት ያክል ጊዜ በስብሰባ ከተገኘ በኋላ የምሥራቹ አስፋፊ ለመሆን ያለውን ምኞት ገለጸ።
ዝግጁ መሆን የምትችሉት እንዴት ነው?
የእሳተ ገሞራ ተመራማሪዎች (volcanologists) ፖፖካቴፔትል ሊያስከትል ስለሚችለው አደጋ ጥናት እያደረጉና ይፋዊ መግለጫ ቢያወጡም እሳተ ገሞራው ምን ሊያደርስ እንደሚችልና መቼ እንደሚፈነዳ አስረግጦ የሚያውቅ የለም። የዜና ማሰራጫዎችና በአቅራቢያው የሚኖሩ ሰዎች እንደሚሉት ከሆነ እሳተ ገሞራው በማንኛውም ሰዓት ሊፈነዳ ይችላል። አደጋ መከሰቱ የማይቀር ነው። እርግጥ ነው ባለ ሥልጣናት ሁኔታው በጣም ስላሳሰባቸው አደጋው ድንገት ቢከሰት በማለት አስፈላጊውን ዝግጅት ሁሉ በማድረግ ላይ ነበሩ። ሆኖም አደጋው ሊከሰት እንደተቃረበ የሚያሳይ ማስረጃ ሳይኖር መላው ሕዝብ ቦታውን ጥሎ እንዲሸሽ ማስጠንቀቂያ ከመስጠት እንደሚቆጠቡ የታወቀ ነው። ታዲያ አንድ ሰው ምን ማድረግ ይኖርበታል?
አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል፤ አላዋቂዎች ግን አልፈው ይጎዳሉ” ይላል። (ምሳሌ 22:3) ስለዚህ ምንም ነገር አይከሰትም በማለት ሁኔታውን በቸልታ ከመመልከትና አስፈሪው የተፈጥሮ ኃይል እስኪደርስ ድረስ እያመነቱ ከመጠባበቅ ይልቅ አጋጣሚው ሳያልፍ ራስን ከአደጋ ለመጠበቅ መወሰድ ያለባቸውን እርምጃዎች መውሰዱ ጥበብ ነው። በአካባቢው የሚኖሩት የይሖዋ ምሥክሮች ሁኔታውን የሚመለከቱት በዚህ መንገድ ነው።
በቅርቡ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ ተወካዮች በአደጋ ቀጠና ሥር ካሉት ጉባኤዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት ካላቸው ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ጋር በፑኤብላ ግዛት ስብሰባ አድርገው ነበር። ተጓዥ የበላይ ተመልካቾቹ ከእርዳታ ኮሚቴ አባላት ጋር በመሆን ከገሞራ ቆሬው በ25 ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ የሚኖረውን እያንዳንዱን ቤተሰብ አንዲጎበኙ እቅድ ወጣ። እነዚህ ቤተሰቦች ፍንዳታው ከመድረሱ በፊት አደገኛ ክልሉን ለቅቆ የመሄዱን አስፈላጊነት እንዲገነዘቡ ተደረገ። 1,500 ሰዎችን ወደ ፑኤብላ ከተማ ለማጓጓዝ የሚያስችል ማመላለሻና ማረፊያ ቦታዎች ተዘጋጁ። አንዳንድ ቤተሰቦች ከዘመዶቻቸው ጋር ለመኖር ወደ ሌሎች ከተሞች ሄዱ።
መጠነ ሰፊ የሆነ ማስጠንቀቂያ
ከፖፖካቴፔትል የሚወጣው ጭስ፣ እሳትና የጉምጉምታ ድምፅ እሳተ ገሞራው ሊፈነዳ የቀረው ጊዜ በጣም አጭር መሆኑን ያመለክታሉ። ከአደጋ ለማምለጥ የሚፈልግ ማንኛውም ግለሰብ ባለ ሥልጣናት የሚሰጡትን ማስጠንቀቂያ መከተልና ተገቢውን እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል። እሳተ ገሞራው አጠገብ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች የራሳቸውን ደህንነት ለመጠበቅም ሆነ ሌሎች ሰዎችም የአደጋውን አስጊነት ተገንዝበው ጊዜ ሳያባክኑ አንድ ዓይነት እርምጃ እንዲወስዱ ለመርዳት ነቅተው ይጠባበቃሉ።
የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት በሚናገረው መሠረት በዓለም ላይ እየተፈጸሙ ያሉትን ክስተቶች በከፍተኛ ደረጃ በንቃት ይከታተላሉ። ጦርነት፣ የምድር መንቀጥቀጥ፣ ረሃብ፣ በሽታና ወንጀል ልክ እሳተ ገሞራው እንደሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች በጉልህ የሚታዩ ነገሮች ናቸው። እነዚህ ሁኔታዎች ኢየሱስ “የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” ብሎ የተነበየውን ጊዜ ለይተው የሚያመለክቱ ጥምር ምልክቶች ናቸው። መጨረሻው መቼ እንደሚመጣ ማንም ሰው ሊያውቅ ባይችልም በእርግጥ እንደሚመጣና መምጫውም በጣም ቅርብ መሆኑ ምንም አያጠራጥርም።—ማቴዎስ 24:3, 7-14, 32-39
በአሁኑ ጊዜ ሰዎች “ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር ስለ ትዳርም በማሰብ እንዳይከብድ፣ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” የሚለውን የኢየሱስ ማስጠንቀቂያ በጥንቃቄ መከተላቸው በጣም አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። (ሉቃስ 21:34) ይህ ሊወሰድ የሚገባው ጥበብ የተሞላበት እርምጃ መሆኑ ግልጽ ነው። በእሳተ ገሞራው ላይ የሚታዩት የማስጠንቀቂያ ምልክቶች በቸልታ መታለፍ እንደሌለባቸው ሁሉ “ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፣ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና” የሚል ማሳሰቢያ የሰጠውን የሰው ልጅ ማለትም የኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት ችላ ልንለው አይገባም።—ማቴዎስ 24:44
[የግርጌ ማስታወሻ]
a መጋቢት 8, 1997 የወጣው ንቁ! (እንግሊዝኛ) መጽሔት ስለዚህ አስጊ እሳተ ገሞራ ዘግቧል።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ማርታ (በአህያ ላይ ተቀምጣ) እና ሌሎች በፖፖካቴፔትል አቅራቢያ ይመሠክራሉ