ሁገናውያን ነፃነት ለማግኘት ያደረጉት ሽሽት
“ወደ ንጉሣዊ ግዛታችን የሚሰደዱና የሚገቡ የፈረንሳይ ፕሮቴስታንቶች በሙሉ የመንግሥታችንን ጥበቃ ከማግኘታቸውም በላይ . . . በዚህ ግዛት ውስጥ ኑሯቸው የተደላደለና ተስማሚ እንዲሆን . . . በምንችለው ሁሉ ለመደገፍ፣ ለመርዳትና እገዛ ለማድረግ የተቻለንን ጥረት እንደምናደርግ በንጉሡና በንግሥቲቱ ስም እንገልጻለን።”
ከላይ ያለው ምንባብ የእንግሊዝ ንጉሥና ንግሥት የነበሩት ዊልያም እና ሜሪ በ1689 ካወጡት መግለጫ ላይ ተቀንጭቦ የተወሰደ ነው። ይሁን እንጂ ሁገናውያን በመባል የሚታወቁት የፈረንሳይ ፕሮቴስታንቶች ከፈረንሳይ ውጪ ባለ አገር ጥገኝነትና ጥበቃ ማግኘት ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው? ከዛሬ 300 ዓመታት ገደማ በፊት ከፈረንሳይ ያደረጉት ሽሽት በዛሬው ጊዜ ትኩረታችንን ሊስበው የሚገባው ለምንድን ነው?
በአሥራ ስድስተኛው መቶ ዘመን አውሮፓ በሃይማኖት ሳቢያ በተቀሰቀሰ ጦርነትና ውዝግብ ታምሳ ነበር። በካቶሊኮችና በፕሮቴስታንቶች መካከል የሃይማኖት ጦርነቶች (1562–1598) እየተካሄዱባት የነበረችው ፈረንሳይም ከዚህ ነውጥ አላመለጠችም። ይሁን እንጂ በ1598 የፈረንሳዩ ንጉሥ ሄንሪ አራተኛ የናንትስ ዐዋጅ ተብሎ የሚጠራ እርስ በርስ ተቻችሎ መኖርን የሚደነግግ ዐዋጅ አወጣ፤ ይህም ፕሮቴስታንቶቹን ሁገናውያን የተወሰነ ሃይማኖታዊ ነፃነት አጎናጸፋቸው። ለሁለት ሃይማኖቶች እንዲህ ያለ ሕጋዊ ዕውቅና መሰጠቱ በአውሮፓ ውስጥ እንግዳ ነገር ነበር። ይህ ሕጋዊ ዕውቅና በ16ኛው መቶ ዘመን ፈረንሳይን ከ30 ለሚበልጡ ዓመታት ክፉኛ የጎዳትን ሃይማኖታዊ ነውጥ ለተወሰነ ጊዜ ሊያቆመው ችሏል።
ምንም እንኳ የናንትስ ዐዋጅ “የማይሻርና ለሁልጊዜው የጸና” እንዲሆን ታስቦ የተደነገገ ቢሆንም በ1685 በፎንተንብሎ ዐዋጅ እንዲሻር ተደርጓል። ከጊዜ በኋላ ፈረንሳዊው ፈላስፋ ቮልቴር ይህን እርምጃ “በፈረንሳይ ውስጥ ከተፈጸሙት እጅግ አሳዛኝ ክስተቶች አንዱ” ሲል ገልጾታል። ብዙም ሳይቆይ ይህ አዋጅ ያስከተለው መዘዝ ወደ 200,000 የሚጠጉ ሁገናውያን ወደ ሌሎች አገሮች እንዲሸሹ አድርጓቸዋል። ይሁን እንጂ መዘዙ በዚህ ብቻ አላበቃም። ይሁንና በሃይማኖት ረገድ ተቻችሎ መኖርን የደነገገው የቀድሞ ዐዋጅ የተሻረው ለምንድን ነው?
ከመጀመሪያ አንስቶ ተቃውሞ ገጥሞታል
ምንም እንኳ የናንትስ ዐዋጅ ወደ 90 ለሚጠጉ ዓመታት ይፋዊ በሆነ መንገድ ሲሠራበት የቆየ ቢሆንም አንድ የታሪክ ምሁር እንዳሉት ዐዋጁ “በ1685 ከመሻሩም በፊት እየከሰመ ሄዶ ነበር።” እንዲያውም ዐዋጁ በጠንካራ መሠረት ላይ የቆመ አልነበረም። ገና ከጅምሩ በካቶሊክ ቀሳውስትና “አር ፒ አር” ብለው በሚጠሯቸው (የተሃድሶ ሃይማኖት ተብሎ በሚጠራ) መካከል ለተቀሰቀሰው “ቀዝቃዛ ጦርነት” አስተዋጽኦ አድርጓል። የናንትስ ዐዋጅ ከወጣበት ከ1598 አንስቶ እስከ 1630 ገደማ ፕሮቴስታንቶችና ካቶሊኮች በዐዋጁ ላይ ከፍተኛ ክርክር ያካሄዱ የነበረ ሲሆን ሃይማኖታዊ ድርጅቶች በሚያወጧቸው የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችም ላይ የተቃውሞ ሐሳቦች ይሰነዘሩ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ መቃቃር ብዙ ገጽታዎች ነበሩት።
የፈረንሳይ መንግሥት ከ1621 እስከ 1629 ድረስ ፕሮቴስታንቶችን ሲወጋ ከቆየ በኋላ ካቶሊኮች እንዲሆኑ ለማስገደድ የተለያዩ የኃይል እርምጃዎችን በተከታታይ ወስዷል። ይህ ጥቃት “የፀሐይ ንጉሥ” ተብሎ በሚታወቀው በሉዊ አሥራ አራተኛ የግዛት ዘመነ መንግሥት ይበልጥ ተፋፋመ። ፕሮቴስታንቶችን የማሳደድ መርሆው የናንትስን ዐዋጅ እንዲሽር አነሳሳው።
እገዳ
የፕሮቴስታንቶችን መብት ቀስ በቀስ ለመግፈፍ የተወሰደው እርምጃ የዚህ እገዳ አንዱ አካል ነው። ከ1657 እስከ 1685 ባሉት ዓመታት ውስጥ በአብዛኛው በቀሳውስቱ ቆስቋሽነት በሁገናውያን ላይ ወደ 300 የሚጠጉ ውሳኔዎች ተላልፈዋል። እነዚህ ውሳኔዎች በሁሉም የኑሮ ዘርፍ ላይ ተጽዕኖ አሳድረውባቸዋል። ለምሳሌ ያህል ሁገናውያን እንደ ሕክምናና ሕግ አልፎ ተርፎም አዋላጅነትን በመሳሰሉ በርካታ የሙያ ዘርፎች ተሰማርተው እንዲሠሩ አይፈቀድላቸውም ነበር። አዋላጅነትን በተመለከተ አንዲት የታሪክ ምሁር “ያለውን ሥርዓት የማጥፋት ዓላማ ላለው ለአንድ መናፍቅ እንዴት ሕይወትን አምኖ መስጠት ይቻላል?” ብለዋል።
በ1677 የጭቆናው ቀንበር ይበልጥ ጠበቀ። የካቶሊኮችን እምነት ለማስቀየር ሲሞክር የተገኘ የትኛውም ሁገናዊ አንድ ሺህ የፈረንሳይ ፓውንድ መቀጮ እንዲከፍል ይደረግ ነበር። መንግሥት ከልክ ያለፈ ቀረጥ በማስከፈል የሚያገኘውን ገንዘብ የሁገናውያንን እምነት ለማስቀየር ተጠቅሞበታል። በ1675 የካቶሊክ ቀሳውስት ለንጉሥ ሉዊ አሥራ አራተኛ 4.5 ሚልዮን የፈረንሳይ ፓውንድ በመስጠት “አሁን ሥልጣንህን ተጠቅመህ መናፍቅነትን ጠራርገህ በማጥፋት አመስጋኝነትህን ማሳየት ይኖርብሃል” አሉት። ይህ “በግዢ” እምነትን ለማስለወጥ የተወጠነው ሴራ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ 10,000 የሚሆኑ ሁገናውያን ወደ ካቶሊክ እምነት እንዲለወጡ አድርጓል።
በ1663 ወደ ፕሮቴስታንት እምነት መለወጥን የሚከለክል ሕግ ተደነገገ። በተጨማሪም ሁገናውያን መኖር የሚችሉባቸውን ቦታዎች በተመለከተ አንዳንድ ገደቦች ተጣሉ። ከተወሰዱት የከፉ እርምጃዎች መካከል አንዱ ሰባት ዓመት የሞላቸው ልጆች ያለ ወላጆቻቸው ፈቃድ ካቶሊኮች ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚገልጽ ነበር። ፕሮቴስታንት የሆኑ ወላጆች ኢየሱሳውያን ወይም ሌሎች የካቶሊክ አስተማሪዎች ለልጆቻቸው ለሚሰጡት ትምህርት የመክፈል ግዴታ ነበረባቸው።
ሁገናውያንን አፍኖ ለመያዝ ያገለገለው ሌላው መሣሪያ ምሥጢራዊው ኮንፓኚ ዱ ሳን ሳክረማን (የቅዱስ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ተቋም) ነው። ይህ ተቋም የካቶሊክ ድርጅት ሲሆን የታሪክ ምሁር የሆኑት ዣኒን ጋሪሶን በመላው ፈረንሳይ ከተዘረጋ “መጠነ ሰፊ ኔትወርክ” ጋር አመሳስለውታል። ወደ ከፍተኛ የኅብረተሰብ ክፍሎች ዘልቆ የገባ በመሆኑ ገንዘብም ሆነ የጠላትን ወሬ የማግኘት ችግር አልነበረውም። ጋሪሶን ይህ ድርጅት ብዙ ስልቶችን ይጠቀም እንደነበረ ገልጸዋል:- “ኮንፓኚው የፕሮቴስታንት ማኅበረሰብን ለማዳከም ሲል ስውር ተጽዕኖ ከማሳደር አንስቶ በግልጽ እስከ ማገድ፣ ጥብቅ ቁጥጥር ከማድረግ አንስቶ እስከ ማውገዝ ድረስ ማንኛውንም ዘዴ ተጠቅሟል።” ሆኖም አብዛኞቹ ሁገናውያን በዚህ የስደት ዘመን እዚያው ፈረንሳይ ውስጥ ቆይተዋል። የታሪክ ምሁሩ ጋሪሶን እንዲህ ብለዋል:- “ፕሮቴስታንቶቹ ይደርስባቸው የነበረው ጥላቻ ቀስ በቀስ እየከረረ ሲሄድ በአንድ ጊዜ አገሪቷን ለቀው አለመውጣታቸው በጣም የሚያስገርም ነው።” ይሁን እንጂ ውሎ አድሮ ነፃነት ለማግኘት መሸሹ አማራጭ የሌለው ነገር ሆነ።
ወደ ቀድሞው ሁኔታ መመለስ
የናይሜገን የሰላም ውል (1678) እና የራትስቦን የተኩስ አቁም ስምምነት (1684) ንጉሥ ሉዊ አሥራ አራተኛ ከውጪ ኃይሎች ጋር ያካሂድ ከነበረው ጦርነት ፋታ እንዲያገኝ አደረጉት። በየካቲት ወር 1685 ላይ ከባሕር ወሽመጡ ባሻገር ባለችው በእንግሊዝ አንድ ካቶሊክ በትረ መንግሥት ጨበጠ። ሉዊ አሥራ አራተኛ ይህን አዲስ ሁኔታ ለመጠቀም የሚያስችለው አጋጣሚ አገኘ። ይህ ከመሆኑ ከጥቂት ዓመታት በፊት የፈረንሳይ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የጳጳሱን ሥልጣን የሚገድቡ አራት ድንጋጌዎችን አውጥታ ነበር። በዚያን ጊዜ ሊቃነ ጳጳሳት ኢኖሰንት አሥራ አንደኛ “የፈረንሳይን ቤተ ክርስቲያን እንደተገነጠለች ያህል አድርገው ቆጥረዋት ነበር።” በመሆኑም ሉዊ አሥራ አራተኛ የናንትስን ዐዋጅ በመሻር የጎደፈውን ስሙን ማደስና ቀደም ሲል ከሊቃነ ጳጳሳቱ ጋር የነበረውን ጥሩ ዝምድና መመለስ ይችል ነበር።
ንጉሡ በፕሮቴስታንቶች ላይ ያለው ፖሊሲ ሙሉ በሙሉ ግልጽ ሆነ። ሰላማዊው መንገድ (ለማሳመን መጣርና የተለያዩ ሕጎችን ማውጣት) የተፈለገውን ውጤት ሊያስገኝ አልቻለም። በሌላ በኩል ግን ወታደሮችን በመጠቀም የተፈጸመው ጭቆናa ስኬታማ ነበር። ስለዚህ በ1685 ሉዊ አሥራ አራተኛ የናንትስን ዐዋጅ ሽሮ የፎንተንብሎን ዐዋጅ አወጣ። ዐዋጁ በመሻሩ በሁገናውያን ላይ የደረሰው ከባድ ስደት የናንትስ ዐዋጅ ከመውጣቱ በፊት ይደርስባቸው ከነበረው በደል እጅግ የከፋ ነበር። ታዲያ አሁን ምን ያደርጉ ይሆን?
መደበቅ፣ መታገል ወይስ መሸሽ?
አንዳንድ ሁገናውያን አምልኳቸውን በድብቅ ማካሄድ መረጡ። የመሰብሰቢያ ቦታዎቻቸው በመውደማቸውና በይፋ የሚያካሄዱት አምልኮ በመታገዱ ‘በበረሃ ቤተ ክርስቲያን’ መጠቀም ወይም ድብቅ አምልኮ ማካሄድ ጀመሩ። ይህን ያደርጉ የነበረው በሐምሌ ወር 1686 ላይ እንዲህ ዓይነት ስብሰባ ሲያካሄዱ የተገኙ ሰዎች እንዲገደሉ የሚያዝ ሕግ ወጥቶ እያለ ነበር። አንዳንድ ሁገናውያን ከጊዜ በኋላ እምነታቸውን መልሰው መያዝ እንደሚችሉ አድርገው በማሰብ ሃይማኖታቸውን ካዱ። እነዚህ ሰዎች የካቶሊክ እምነት ተከታዮች በመሆን የይስሙላ አምልኮ ማካሄድ ጀመሩ፤ ከጊዜ በኋላ የኋለኞቹም ትውልዶች ይህን የይስሙላ አምልኮ ኮርጀዋል።
መንግሥት ብዙዎቹ እምነታቸውን እንዲቀይሩ ለማድረግ ኃይሉን አስተባበረ። እምነታቸውን የለወጡ አዳዲስ ሰዎች ሥራ ለማግኘት እንዲችሉ በቤተ ክርስቲያን ሥነ ሥርዓቶች ላይ መገኘታቸውን የተመለከተ የደብር ቄስ የፈረመበት የካቶሊክ እምነት ተከታዮች መሆናቸውን የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት ማቅረብ ነበረባቸው። ልጆች ካልተጠመቁና በካቶሊክ እምነት ተኮትኩተው ካላደጉ ከወላጆቻቸው ተነጥለው ሊወሰዱ ይችላሉ። ትምህርት ቤቶች የካቶሊክ ትምህርት ማስፋፊያ ሆኑ። የካቶሊክ እምነትን የሚያራምዱ ሃይማኖታዊ ጽሑፎች “የመጽሐፉ [የመጽሐፍ ቅዱስ] ሰዎች” ተብለው ይጠሩ ለነበሩት ፕሮቴስታንቶች ለማዘጋጀት ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። መንግሥት ከአንድ ሚልዮን በላይ የሚሆኑ መጽሐፎችን በማተም እምነታቸውን የለወጡ ብዙ ሰዎች ወዳሉባቸው አካባቢዎች ልኳል። የሚወሰዱት እርምጃዎች በጣም ጥብቅ ከመሆናቸው የተነሳ አንድ የታመመ ሰው በካቶሊክ እምነት መሠረት በሞት አፋፍ ላይ ላለ ሰው የሚፈጸመውን ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ባይቀበልና ከጊዜ በኋላ ከሕመሙ ቢድን ይታሰራል ወይም ደግሞ ዕድሜ ልኩን በዘመኑ በነበሩት መርከቦች ውስጥ እንዲያገለግል ይደረግ ነበር። ሲሞት ደግሞ አስከሬኑ እንደ ቆሻሻ ይጣላል፤ እንዲሁም ንብረቱ ይወረሳል።
አንዳንድ ሁገናውያን የትጥቅ ትግል ማካሄድ ጀመሩ። ለእምነታቸው ቀናኢ የሆኑ ሰዎች በሚኖሩባት በሴቬን ክልል ካመዛርድ ተብለው የሚጠሩ ነውጠኛ ሁገናውያን በ1702 ዓመፁ። የመንግሥት ወታደሮች ካመዛርዶች ለሚያካሂዱት የደፈጣ ውጊያና ጨለማን ተገን አድርገው ለሚሰነዝሩት ጥቃት የአጸፋ እርምጃ በመውሰድ መንደሮችን አቃጠሉ። ምንም እንኳ ሁገናውያን አልፎ አልፎ የሚሰነዝሩት ጥቃት ለተወሰነ ጊዜ የዘለቀ ቢሆንም በ1710 የንጉሥ ሉዊ ጦር ሠራዊት ኃይል ካመዛርዶችን ደመሰሰ።
ሁገናውያን ሌላው የወሰዱት እርምጃ ፈረንሳይን ለቅቆ መሸሽ ነበር። ይህ ስደት ታላቅ ፍልሰት በመባል ይታወቃል። አብዛኞቹ ሁገናውያን አገራቸውን ለቅቀው ሲወጡ የአገሪቱ መንግሥት ንብረታቸውን ወርሶባቸው ስለነበር ምንም ነገር አልነበራቸውም። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንም መንግሥት ከወረሰው ንብረት ላይ የተወሰነውን ወስዳለች። ስለዚህ ሽሽቱም ቀላል አልነበረም። የፈረንሳይ መንግሥት አፋጣኝ እርምጃ በመውሰድ ኬላዎችን መጠበቁንና መርከቦችን መፈተሹን ተያያዘው። ለማምለጥ የሚሞክሩ ሁገናውያንን የያዘ ወሮታ ይከፈለው ስለነበር የመርከብ ዘራፊዎች ፈረንሳይን ለቅቀው የሚወጡ መርከቦችን ያስሱ ነበር። ሲያመልጡ የተያዙ ሁገናውያን ከባድ ቅጣት ይጠብቃቸው ነበር። በማኅበረሰቡ ውስጥ የተሰገሰጉ ሰላዮች ለመሸሽ ያሰቡ ሰዎችን ስም ዝርዝርና የሚሄዱበትን አቅጣጫ ለማወቅ ይጥሩ ስለነበር ሁኔታውን ይበልጥ አስቸጋሪ አደረገው። በደብዳቤዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ፣ የሐሰት ሰነዶችን በማዘጋጀት ማጭበርበርና ሴራ መተብተብ የዕለት ተዕለት ክስተቶች ሆነው ነበር።
ጥገኝነት ማግኘት
ሁገናውያን ፈረንሳይን ለቅቀው ያደረጉት ሽሽትና በሌሎች አገሮች ያገኙት ተቀባይነት ጥገኝነት በመባል ይታወቃል። ሁገናውያን ወደ ሆላንድ፣ ስዊዘርላንድ፣ ጀርመንና እንግሊዝ ተሰደዋል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ አንዳንዶቹ ወደ ስካንዲኔቪያ፣ አሜሪካ፣ አየርላንድ፣ ዌስት ኢንዲስ፣ ደቡብ አፍሪካና ሩሲያ ሄደዋል።
በርካታ የአውሮፓ አገሮች እጃቸውን ዘርግተው ሁገናውያንን እንደሚቀበሉ የሚያሳውቁ ዐዋጆች አወጡ። በዐዋጆቹ ላይ ከወጡት ማበረታቻዎች መካከል ነፃ የዜግነት መብት ማግኘት፣ ከቀረጥ ነፃ መሆንና በሙያ ማኅበር ውስጥ አባል የመሆን መብት ማግኘት ይገኙበታል። የታሪክ ምሁር የሆኑት ኤሊዛቤት ላብሩስ እንዳሉት ከሆነ አብዛኞቹ ሁገናውያን “ጥሩ የፈጠራ ችሎታ ያላቸውና ለጥሩ ሥነ ምግባር የሚገዙ ታታሪ . . . ወጣት ወንዶች” ናቸው። በመሆኑም ፈረንሳይ ይበልጥ ኃያል ሆና በነበረበት ዘመን ላይ በተለያዩ ሙያዎች የተካኑ ሠራተኞችን አጥታለች። አዎን፣ “ንብረት፣ ሀብትና ቴክኒክ” አብረው ወደ ባሕር ማዶ ነጎዱ። ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችም ሁገናውያን ጥገኝነት እንዲያገኙ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ይሁን እንጂ ይህ ፍልሰት ያስከተለው ለረጅም ጊዜ የዘለቀ መዘዝ ምንድን ነው?
የናንትስ ዐዋጅ መሻሩና በዚሁ ሳቢያ የመጣው ስደት ዓለም አቀፋዊ ውግዘት አስከትሏል። የኦሬንጁ ዊልያም ፈረንሳይን በማውገዝ የሰጠው አስተያየት የኔዘርላንድ ገዥ እንዲሆን አስችሎታል። በተጨማሪም በሁገናውያን ሹማምንት እርዳታ ካቶሊኩን ዳግማዊ ጀምስ በመተካት የታላቋ ብሪታንያ ንጉሥ ሊሆን ችሏል። የታሪክ ምሁር የሆኑት ፊሊፕ ዡታር እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “ለዳግማዊ ጀምስ መውደቅ [እና] ለኦግዝበርግ ኅብረት መቋቋም ምክንያት ከሆኑት ዋና ዋና ነገሮች አንዱ ሉዊ አሥራ አራተኛ በፕሮቴስታንቶች ላይ የነበረው ፖሊሲ ነው። . . . [እነዚህ] ክስተቶች የፈረንሳይ የበላይነት በእንግሊዝ የበላይነት እንዲተካ በማድረግ በአውሮፓ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ አስከትለዋል።”
ሁገናውያን በአውሮፓ ሥልጣኔ ላይ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። ያገኙትን አዲስ ነፃነት በመጠቀም ያከናወኗቸው የተለያዩ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች የነፃ አስተሳሰብ ፍልስፍናንና ተቻችሎ የመኖር ጽንሰ ሐሳቦችን ይበልጥ ለማዳበር አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ለምሳሌ ያህል አንድ ፈረንሳዊ ፕሮቴስታንት ጆን ሎክ የተባለውን እንግሊዛዊ ፈላስፋ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች በመተርጎም የሰብዓዊ መብቶች ጽንሰ ሐሳብን አስፋፍቷል። ሌሎች የፕሮቴስታንት ጸሐፊዎች ደግሞ የሕሊና ነፃነትን አስፈላጊነት ጎላ አድርገው ገልጸዋል። ለገዢዎች መገዛት የሚቻለው በአንጻራዊ ሁኔታ እንደሆነና በእነርሱና በሕዝቡ መካከል ያለውን ስምምነት ሲጥሱ ሥልጣናቸው ሊከበር እንደማይችል የሚገልጽ ጽንሰ ሐሳብ ዳብሯል። በመሆኑም የታሪክ ምሁር የሆኑት ቻርልስ ሪድ እንደገለጹት “ለፈረንሳይ አብዮት አስተዋጽኦ ካደረጉት ነገሮች አንዱ” የናንትስ ዐዋጅ መሻር ነው።
ከዚህ ተሞክሮ ትምህርት አግኝተዋልን?
የንጉሥ ሉዊ አሥራ አራተኛ ወታደራዊ አማካሪ የነበረው ማርኪ ደ ቮባን ስደቱ ያስከተለውን ያልታሰበ መዘዝና አገሪቱ ያጣቻቸውን ጠቃሚ የሆኑ ብዙ ሰዎች ግምት ውስጥ በማስገባት “ልብን መለወጥ የሚችለው አምላክ ብቻ ነው” በማለት ንጉሡ የናንትስን ዐዋጅ መልሶ እንዲያወጣ አሳስቦት ነበር። ታዲያ የፈረንሳይ መንግሥት ካሳለፈው ተሞክሮ ያልተማረውና ውሳኔውን ያልቀለበሰው ለምንድን ነው? ይህ የሆነበት አንዱ ምክንያት ንጉሡ የመንግሥት ሥልጣን እንይዳከም በመፍራቱ እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም። ከዚህም በተጨማሪ እየተጠናከረ ሄዶ የነበረው የካቶሊክ እምነትና በ17ኛው መቶ ዘመን በፈረንሳይ ውስጥ የነበረው ሃይማኖታዊ አለመቻቻል እንዳለ እንዲቀጥል ማድረጉ ለራሱም ሕልውና ጠቃሚ ሆኖ ታይቶት ነበር።
ከዐዋጁ መሻር ጋር ተያይዘው የተከሰቱት ነገሮች አንዳንድ ሰዎች “አንድ ኅብረተሰብ የተለያዩ እምነቶችን መፍቀድና በመቻቻል መንፈስ መኖር ያለበት እስከ ምን ድረስ ነው?” ብለው እንዲጠይቁ አድርጓቸዋል። እንዲያውም የታሪክ ምሁራን እንደተገነዘቡት የሁገናውያን ታሪክ አንድ ሰው “የሥልጣን አጠቃቀምንና ብልሹ ጎኑን” እንዲያስብ ያደርገዋል። ብዙ ዘሮችንና የተለያዩ ሃይማኖቶችን ባቀፉት በዛሬዎቹ ኅብረተሰቦች ውስጥ ሁገናውያን ነፃነት ለማግኘት ያደረጉት ሽሽት ፖለቲካ በቤተ ክርስቲያን ገፋፊነት በሕዝቡ ፍላጎት ላይ ተጽዕኖ በሚያደርግበት ጊዜ ምን ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል የሚያሳይ አሳዛኝ ማስታወሻ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ገጽ 28 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ወታደሮች
እምነትን በኃይል ለማስቀየር የወሰዱት እርምጃ
አንዳንዶች እነዚህን ጉልበተኛ ወታደሮች “ውጤታማ ሚስዮናውያን” እንደሆኑ አድርገው ተመልክተዋቸው ነበር። ይሁን እንጂ በሁገናውያን ላይ ሽብር ፈጥረውባቸው ነበር፤ እንዲያውም አንዳንዴ የእነሱን መምጣት የሰሙ መንደርተኞች ቶሎ ብለው ወደ ካቶሊክ እምነት ይለወጡ ነበር። ይሁንና እነዚህ ወታደሮች እነማን ናቸው?
እነዚህ ወታደሮች በደንብ የታጠቁ ሲሆኑ ነዋሪዎቹን ለማስፈራራት ሲሉ በሁገናውያን ቤቶች ውስጥ ያርፉ ነበር። እነዚህ ወታደሮች የተጠቀሙበት ይህ ዘዴ ድራጎኔድስ በመባል ይታወቃል። ቤተሰቦቹን ይበልጥ ለማስጨነቅ ሲባል ወደ አንድ ቤት የሚላኩት ወታደሮች ቁጥር ከቤተሰቡ ገቢ ጋር የማይመጣጠን ነበር። ወታደሮቹ ቤተሰቦቹን የማንገላታት፣ እንቅልፍ እንዳይተኙ የማድረግና ንብረታቸውን የማውደም ሥልጣን ተሰጥቷቸው ነበር። የቤተሰቡ አባላት የፕሮቴስታንትን እምነት ከካዱ ወታደሮቹ ቤቱን ለቅቀው ይሄዳሉ።
በ1681 በምዕራብ ፈረንሳይ ፖውቱ ውስጥ ሁገናውያን በብዛት በሚገኙበት አካባቢ ወታደሮቹ እምነታቸውን ለማስቀየር ይህን ዘዴ ተጠቅመው ነበር። በጥቂት ወራት ውስጥ ከ30,000 እስከ 35,000 የሚሆኑት እምነታቸውን ቀየሩ። በ1685 ሁገናውያን በሚኖሩባቸው ሌሎች ቦታዎችም ይህንኑ ዘዴ ተጠቅመዋል። በጥቂት ወራት ውስጥ ከ300,000 እስከ 400,000 የሚሆኑት እምነታቸውን ካዱ። የታሪክ ምሁሩ ዣን ኬንያር እንዳሉት ከሆነ በዚህ ስልት የተገኘው ስኬት “[ተቻችሎ መኖርን የሚደነግገው የናንትስ ዐዋጅ] እንዲሻር ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።”
[ምንጭ]
© Cliché Bibliothèque Nationale de France, Paris
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይህ በ1689 የወጣው መግለጫ ከሃይማኖታዊ የጭቆና ቀንበር መላቀቅ ለሚፈልጉ የፈረንሳይ ፕሮቴስታንቶች ጥገኝነት ፈቅዷል
[ምንጭ]
በሁገናውያን ቤተ መጻሕፍት ፈቃድ፣ የታላቋ ብሪታንያና የአየርላንድ ሁገናውያን ማኅበር፣ ለንደን
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የናንትስ ዐዋጅ መሻር፣ 1685 (ዐዋጁ እንደተሻረ የሚያሳየው የመጀመሪያ ገጽ)
[ምንጭ]
Documents conservés au Centre Historique des Archives nationales à Paris
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብዙዎቹ የፕሮቴስታንት ቤተ መቅደሶች ወድመዋል
[ምንጭ]
© Cliché Bibliothèque Nationale de France, Paris