የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 8/15 ገጽ 30-31
  • የአንባብያን ጥያቄዎች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የአንባብያን ጥያቄዎች
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ጋብቻ​—አፍቃሪ ከሆነው አምላክ የተገኘ ስጦታ
    ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’
  • የተሳካ ትዳር ለመመሥረት መዘጋጀት
    ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
  • ጋብቻ—ከአምላክ የተገኘ ስጦታ
    ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ ኑሩ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 8/15 ገጽ 30-31

የአንባብያን ጥያቄዎች

ክርስቲያኖች ለጋብቻ መተጫጨትን ምን ያህል አክብደው ሊመለከቱት ይገባል?

ለጋብቻ መተጫጨት የሚያስደስት ነገር ነው። ይሁን እንጂ ከባድ ኃላፊነትም ነው። ካልመሰለኝ በማንኛውም ጊዜ ላቆመው እችላለሁ በሚል ሐሳብ መተጫጨትን አቅልሎ የሚያይ የጎለመሰ ክርስቲያን አይኖርም። አንድ ወንድና አንዲት ሴት ተጫጭተው የሚያሳልፉት ጊዜ ከጋብቻቸው በፊት በደንብ ለመተዋወቅ የሚያስችላቸው ወቅት ነው።

በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ስንወያይ በኅብረተሰቡ ዘንድ ያሉት ከጋብቻ ጋር የተያያዙ ልማዶች እንዲሁም ከጋብቻ በፊት ደረጃ በደረጃ የሚከናወኑ ነገሮች ከቦታ ቦታና ከዘመን ዘመን እንደሚለያዩ መዘንጋት የለብንም። መጽሐፍ ቅዱስም ይህንኑ ሐሳብ ያንጸባርቃል።

‘ወንድ የማያውቁት’ ሁለቱ የሎጥ ሴት ልጆች በሆነ መንገድ አካባቢያቸው ከሚኖሩ ሁለት ወንዶች ጋር ተጫጭተው ነበር። የሎጥ ‘አማቾች ልጆቹን ሊያገቡ’ ነበር። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ከእነርሱ ጋር ለምን እንደተጫጩ ወይም እንዴት ሊተጫጩ እንደቻሉ አይነግረንም። የሎጥ ልጆች ለአቅመ ሔዋን የደረሱ ነበሩ? የሚያገቡትን ሰው በመምረጥ ረገድ የእነርሱ ሐሳብ ተሰሚነት ነበረው? የተጫጩት በይፋ በሚደረጉ አንዳንድ ክንውኖች ነው? ይህንን በተመለከተ የምናውቀው ነገር የለም። (ዘፍጥረት 19:​8-14) ያዕቆብ ራሔልን ለማግባት ለአባቷ ሰባት ዓመት ለመገዛት የተደራደረው ራሱ እንደሆነ እናውቃለን። ያዕቆብ ራሔልን “ሚስቴ” ብሎ ይጥራት እንጂ በእነዚያ ዓመታት በጾታ ተገናኝቷት አያውቅም። (ዘፍጥረት 29:​18-21) ሌላ ምሳሌ ለመጨመር ያህል ዳዊት የሳውልን ሴት ልጅ ከማግባቱ በፊት በፍልስጤማውያን ላይ ድል መቀዳጀት ነበረበት። ዳዊት የሳውልን ልጅ ሜልኮልን ማግባት ይችል የነበረው አባቷ የጠየቀውን ነገር ካሟላ ነበር። (1 ሳሙኤል 18:​20-28) ስለ “መተጫጨት” የሚገልጹት እነዚህ ታሪኮች አንዳቸው ከሌላው እንዲሁም ዛሬ በብዙ አገሮች በሰፊው ከሚታየው ሁኔታ የተለዩ ናቸው።

የሙሴ ሕግ ጋብቻና መተጫጨትን በተመለከተ መመሪያ ይሰጥ ነበር። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው ከአንድ በላይ ሚስት ሊያገባና በተለያዩ ምክንያቶች ፍቺ ሊፈጽም ይችል የነበረ ሲሆን ሚስቲቱ ግን እንደዚያ ማድረግ አትችልም ነበር። (ዘጸአት 22:​16, 17፤ ዘዳግም 24:​1-4) አንዲትን ያልታጨች ድንግል በጾታ ያስነወረ ወንድ አባቷ ከተስማማ ሚስት አድርጎ ሊወስዳት ይገባ የነበረ ሲሆን ከዚያ በኋላ ፈጽሞ ሊፈታትም አይችልም ነበር። (ዘዳግም 22:​28, 29) ከጾታ ግንኙነት የሚርቁባቸውን ጊዜያት የሚጠቁሙትን የመሰሉ ጋብቻን የሚመለከቱ ሌሎች ሕጎችም ነበሩ። (ዘሌዋውያን 12:​2, 5፤ 15:​24፤ 18:​19) ከመተጫጨት ጋር የተያያዙ ምን መመሪያዎች ነበሩ?

አንዲት የታጨች እስራኤላዊት ሴት በሕግ ፊት የምትታይበት መንገድ ካልታጨች እስራኤላዊት ሴት የተለየ ሲሆን በአንዳንድ ሁኔታዎችም እንዳገባች ተደርጋ ትቆጠር ነበር። (ዘዳግም 22:​23-29፤ ማቴዎስ 1:​18, 19 NW) እስራኤላውያን ከተወሰኑ ዘመዶቻቸው ጋር መተጫጨት ወይም መጋባት አይችሉም ነበር። ይህ በአብዛኛው የሥጋ ዘመዶቻቸውን የሚመለከት ሲሆን ከውርስ መብት ጋር በተያያዘም መተጫጨት ወይም ጋብቻ የሚከለከልባቸው አንዳንድ ሁኔታዎች ነበሩ። (ዘሌዋውያን 18:​6-20፤ የመጋቢት 15, 1978 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 25-28 ተመልከት።) የአምላክ አገልጋዮች መተጫጨትን አቅልለው ሊመለከቱት እንደማይገባ ግልጽ ነበር።

እስራኤላውያን እነዚህን በመሳሰሉት የሕጉ መመሪያዎች ሥር ነበሩ። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች የመተጫጨትና የጋብቻ ሥርዓቱን ጨምሮ በአጠቃላይ በሕጉ ሥር አይደሉም። (ሮሜ 7:​4, 6፤ ኤፌሶን 2:​15፤ ዕብራውያን 8:​6, 13) እንዲያውም ኢየሱስ ክርስቲያኖች በጋብቻ ረገድ የሚከተሉት መመሪያ ከሕጉ የተለየ መሆኑን አስተምሯል። (ማቴዎስ 19:​3-9) ይህ ግን የጋብቻንም ሆነ የመተጫጨትን ክብደት አቅልሎ ተመልክቶታል ማለት አይደለም። ታዲያ በክርስቲያኖች መካከል የሚፈጸመው መተጫጨት ምን ያህል ከፍ ተደርጎ ሊታይ የሚገባው ነው?

በብዙ አገሮች ግለሰቦች ማግባት የሚፈልጉትን ሰው ራሳቸው ይመርጣሉ። አንድ ወንድና አንዲት ሴት ለመጋባት ከተስማሙ እንደተጫጩ ይቆጠራል። አብዛኛውን ጊዜ መተጫጨታቸውን በይፋ ለማሳወቅ የሚያስችል ሊከተሉት የሚገባ የተወሰነ ደንብ የለም። በአንዳንድ ቦታዎች ግን ወንዱ ሚስት ለምትሆነው ሴት መተጫጨታቸውን የሚያሳይ ቀለበት መስጠቱ የተለመደ ነው። ወይም በቤተሰብ መልክ ሰብሰብ ብለው ወይም ጥቂት ሰዎች ጠርተው መተጫጨታቸውን በዘመድ ወዳጆቻቸው ፊት ይፋ ማድረግ የተለመደ ነው። ይህ የግል ምርጫ እንጂ ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታ አይደለም። ዋናው ተጫጭተዋል የሚያሰኘው ነገር በሁለቱ መካከል የሚደረገው ስምምነት ነው።a

አንድ ክርስቲያን መጠናናት ለመጀመር፣ ለመተጫጨት ወይም ለማግባት መቸኮል የለበትም። ነጠላ የሆኑ ግለሰቦች መጠናናት መጀመራቸው ወይም ደግሞ ለመተጫጨት አሊያም ለመጋባት አንዳንድ እርምጃ መውሰዳቸው ተገቢ መሆን አለመሆኑን ለመወሰን የሚረዷቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶች እናወጣለን።b ለዚህ ምክር መነሻ የሆነው አቢይ ጉዳይ ጋብቻ ዘላቂ ነገር መሆኑ ነው።​—⁠ዘፍጥረት 2:​24፤ ማርቆስ 10:​6-9

ሁለት ክርስቲያኖች ለመተጫጨት ከማሰባቸው በፊት በሚገባ መተዋወቅ ይኖርባቸዋል። እያንዳንዳቸው እንዲህ እያሉ ሊጠይቁ ይችላሉ:- ‘ስለ እርሱ ወይም ስለ እርሷ መንፈሳዊነትና ለአምላክ ያደረ ለመሆኑ ወይም ለመሆኗ እርግጠኛ ነኝን? ከእርሱ ወይም ከእርሷ ጋር አምላክን ለዘላለም ሳገለግል በዓይነ ሕሊናዬ ይታየኛል? አንዳችን የሌላውን የግል ባሕርይና ጠባይ በሚገባ አጥንተናል? እስከ ዘለቄታው ተስማምተን እንደምንቀጥል እርግጠኛ ነኝን? አንዳችን የሌላውን ያለፈ ድርጊትና አሁን ያለበትን ሁኔታ በሚገባ አውቀናል?’

ሁለት ክርስቲያኖች ለመጋባት አንዴ ቃል ከተገባቡ በኋላ እነርሱም ሆኑ ሌሎች ሰዎች የሚጋቡበትን ጊዜ መጠባበቃቸው ተገቢ ነው። ኢየሱስ “ቃላችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይሁን” ሲል አሳስቧል። (ማቴዎስ 5:​37 በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) የተጫጩ ክርስቲያኖች ቃላቸውን ማክበር አለባቸው። ይሁን እንጂ ብዙ ጊዜ የሚከሰት ነገር ባይሆንም አንድ የታጨ ክርስቲያን ለማግባት ቃል ከመግባቱ በፊት ሳይነገረው የቀረ ወይም የተደበቀው ከበድ ያለ ነገር እንዳለ ይገነዘብ ይሆናል። የሌላኛውን ወገን የኋላ ታሪክ የሚመለከት ምናልባትም የወንጀል ወይም የብልግና ድርጊትን የመሰለ ከበድ ያለ ግምት የሚሰጠው ጉዳይ ሊሆን ይችላል። ይህንን ያወቀው ክርስቲያን ምን ማድረግ እንዳለበት ሊወስን ይገባል። ምናልባትም ሁለቱ በጉዳዩ ላይ በጥልቀት ተወያይተው እንደተጫጩ ለመቀጠል ይስማሙ ይሆናል። ወይም ደግሞ መተጫጨታቸው እንዲቀር በጋራ ስምምነት ላይ ይደርሱ ይሆናል። ይህ ሌሎች ሐሳብ ለመስጠት በመሞከር ወይም ፍርድ በመስጠት እጃቸውን የሚያስገቡበት ሳይሆን የሁለቱ የግል ጉዳይ ብቻ ቢሆንም ውሳኔው ቀላል አይደለም። በሌላ በኩል ደግሞ ይህን ከበድ ያለ ጉዳይ የሰማው ወገን ሌላኛው ወገን መቀጠል ቢፈልግም እንኳ እርሱ መተጫጨታቸው የግድ ማክተም እንዳለበት ይሰማው ይሆናል።​—⁠በሰኔ 15, 1975 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ላይ የወጣውን “የአንባብያን ጥያቄዎች” ተመልከት።

በጋብቻ ከመተሳሰራቸው በፊት እንዲህ ያሉት ጉዳዮች መፍትሔ እንዲያገኙ ማድረጋቸው አስፈላጊ የሚሆንበት ምክንያት አለ። ኢየሱስ አንድ ሰው ፍቺ ፈጽሞ ሌላ እንዲያገባ ነፃ የሚያደርገው ምክንያት ፖርኒያ ብቻ እንደሆነ ማለትም ሌላኛው የትዳር ጓደኛ ከባድ የጾታ ብልግና ከፈጸመ ብቻ እንደሆነ ገልጿል። (ማቴዎስ 5:​32፤ 19:​9) ከጋብቻቸው በፊት የተከሰተ ከባድ ችግር ከነበረ ወይም ከባድ ኃጢአት ተፈጽሞ ከነበረ ሕጋዊው ጋብቻ ፈርሶ በፍቺ ሊለያዩ ይችላሉ አላለም።

ለምሳሌ ያህል በኢየሱስ ዘመን አንድ ሰው በቀላሉ በሥጋ ደዌ በሽታ ሊያዝ የሚችልበት አጋጣሚ ነበር። አንድ አይሁዳዊ ባል ሚስቱ እርሱን ስታገባ (ትወቅም አትወቅ) የሥጋ ደዌ በሽታ እንደነበረባት ከጊዜ በኋላ ማወቁ ለፍቺ የሚያበቃ መሠረት ይሆነው ነበርን? አንድ በሕጉ ሥር የነበረ አይሁዳዊ ሊፈታት ይችል ይሆናል። ኢየሱስ ግን ተከታዮቹ እንደዚያ ማድረግ እንደማይገባቸው ገልጿል። ዛሬ ሊከሰቱ የሚችሉ አንዳንድ ሁኔታዎችን ተመልከት። ቂጥኝ፣ ከርክር፣ ኤች አይ ቪ ወይም ሌላ ከበድ ያለ ተላላፊ በሽታ ያለበት አንድ ሰው ስለ ጉዳዩ ምንም ሳይናገር ያገባ ይሆናል። ምናልባት ያለበት በሽታ ከመተጫጨታቸው በፊት ወይም ተጫጭተው እያሉ የጾታ ብልግና በመፈጸሙ የያዘው ሊሆን ይችላል። ሚስትየዋ ስለ በሽታው ወይም ስለፈጸመው የብልግና ድርጊት ከጊዜ በኋላ ብታውቅ (መካንነት ወይም ሌሎች የጾታ ችግሮች ሊሆኑ ይችላሉ) ይህ የተጋቡ መሆናቸውን አይሽረውም። ከጋብቻው በፊት የተፈጸመ አሳዛኝ ድርጊት መኖሩ እንዲሁም በሚስት በኩል የያዛት በሽታ አልፎ ተርፎም ስታገባው ደብቃው የያዘችው የሌላ ሰው ጽንስ እንዳለ መታወቁ ጋብቻውን ለማፍረስ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት አይሆንም። አሁን ተጋብተው በቃል ኪዳን ተሳስረዋል።

እንዲህ ዓይነት አሳዛኝ ሁኔታዎች የሚከሰቱት ከስንት አንድ ጊዜ ቢሆንም እነዚህ ምሳሌዎች መተጫጨት በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ አይደለም የሚለውን መሠረታዊ ነጥብ የሚያጠናክሩ እንደሆኑ ግልጽ ነው። ክርስቲያኖች ከመተጫጨታቸው በፊትና ተጫጭተውም እያሉ እርስ በርሳቸው በደንብ ለመተዋወቅ ሊጥሩ ይገባል። ሌላኛው ወገን ሊያውቃቸው የሚፈልጋቸውን ወይም የሚገባቸውን ጉዳዮች በተመለከተ ሐቀኞች መሆን ይገባቸዋል። (በአንዳንድ አገሮች ሕጉ ተጋቢዎች በትዳር ከመተሣሠራቸው በፊት የሕክምና ምርመራ እንዲያደርጉ ያዝዛል። አንዳንዶች ደግሞ ለራሳቸው ለማወቅ ሲሉ እንዲህ ያለውን ምርመራ ማድረግ ይፈልጉ ይሆናል።) ደስታም ኃላፊነትም የሆነው መተጫጨት ሁለቱም ሰዎች ይበልጥ አስደሳች ወደሆነውና ወደበለጠው የኃላፊነት ቀንበር ማለትም ወደ ትዳር ዓለም ሲጓዙ ክብራማ ዓላማውን ከዳር ያደርሳል።​—⁠ምሳሌ 5:​18, 19፤ ኤፌሶን 5:​33

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በአንዳንድ ኅብረተሰብ ዛሬም ቢሆን ለልጆቻቸው የትዳር ጓደኛ የሚያጩት ወላጆች ናቸው። ይህም የሚደረገው ሁለቱም ገና ለጋብቻ እድሜ ከመድረሳቸው በፊት ጥቂት ጊዜ ቀደም ብሎ ሊሆን ይችላል። እስከዚያው ግን እንደተጫጩ ወይም አንዳቸው ለሌላው ቃል እንደገቡ ተደርጎ ይታሰባል። ይሁን እንጂ ይህ ተጋብተዋል ማለት አይደለም።

b ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የተዘጋጁትን ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 28-32 እንዲሁም ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 2 ተመልከት።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ