የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 12/1 ገጽ 20-24
  • ወላጆቻችን አምላክን መውደድ አስተምረውናል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ወላጆቻችን አምላክን መውደድ አስተምረውናል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መማር
  • በተማሩት መሠረት እርምጃ መውሰድ
  • እውነትን አስተማሩን
  • በሴልማ የገጠመን ተቃውሞ
  • ጊልያድ የሚስዮናውያን ትምህርት ቤት ገባን
  • ከወላጆቼ ጋር በሚስዮናዊነት አገለገልኩ
  • ወላጆቻችንን መንከባከብ
  • ብርቅ የሆነ ክርስቲያናዊ ውርስ
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ውድ የሆነው መንፈሳዊ ቅርሳችን
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • አባቴ ወይም እናቴ ታማሚ ቢሆኑስ?
    የወጣቶች ጥያቄ
  • የወላጆቼን ፈለግ መከተል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 12/1 ገጽ 20-24

ወላጆቻችን አምላክን መውደድ አስተምረውናል

ኤሊዛቤት ትሬሲ እንደተናገረችው

የዚያኑ ዕለት ዓመፅ ቀስቅሰውብን የነበሩ መሣሪያ የታጠቁ ሰዎች እማዬንና አባዬን በግድ ከመኪና አስወጥተው ወሰዷቸው። እኔና እህቴ ኋለኛው ወንበር ላይ ብቻችንን ተቀምጠን ቀረን። ወላጆቻችንን እንደገና እናያቸው ይሆን ብለን አሰብን። በ1941 በዩ ኤስ ኤ አላባማ፣ ሴልማ አቅራቢያ ይህ አስደንጋጭ ገጠመኝ ሊደርስብን የቻለው እንዴት ነው? እንዲሁም ከወላጆቻችን የተማርናቸው ትምህርቶች ከዚህ ገጠመኝ ጋር ምን ዝምድና አላቸው?

አባቴ ዱዊ ፋውንቴን ገና ጨቅላ ሕፃን እያለ ወላጆቹ ስለሞቱበት ቴክሳስ ውስጥ በሚገኝ የእርሻ ቦታ ከዘመድ ጋር ነው ያደገው። ከጊዜ በኋላ በነዳጅ ማውጫ ሥራ ተሰማራ። በ1922 በ23 ዓመቱ ዊኒ የምትባል አንዲት ቆንጆ የቴክሳስ ወጣት አገባና የተመቻቸ ኑሮ መሥርተው ልጆች የማሳደግ ዕቅድ አወጡ።

ጋሪሰን ከተባለችው ትንሽ ከተማ አቅራቢያ በደን በተሸፈነው የምሥራቅ ቴክሳስ ክልል ውስጥ ቤት ሠራ። በዚያ ጥጥና በቆሎን ጨምሮ ልዩ ልዩ ሰብሎችን ያመርት ነበር። በተጨማሪም የማያረባው ዓይነት የግብርና እንስሳት አልነበረም። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ እኛ ተወለድን። ዱዊ ትንሹ በግንቦት 1924፣ ኤድዊና በታኅሣሥ 1925፣ እኔ ደግሞ ሰኔ 1929 ተወለድን።

የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መማር

እማዬና አባዬ የመካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን አባላት ስለነበሩ መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ የሚያውቁ ይመስላቸው ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ በ1932 ጂ ደብልዩ ኩክ ዴሊቨረንስ እና ገቨርንመንት የተባሉትን በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የተዘጋጁ መጻሕፍት ለአባዬ ወንድም ለሞንሮይ ፋውንቴን ሰጠው። ሞንሮይ የተማራቸውን ነገሮች ለወላጆቼ ለማካፈል ጓጉቶ ስለነበር አብዛኛውን ጊዜ በቁርስ ሰዓት ይመጣና ከመጠበቂያ ግንብ መጽሔት አንድ ጽሑፍ ካነበበልን በኋላ “እንዳጋጣሚ” መጽሔቱን ትቶት ይሄዳል። ከዚያ በኋላ እማዬና አባዬ መጽሔቱን ያነብባሉ።

አንድ ቀን እሁድ ጠዋት አጎቴ ሞንሮይ አባዬን በጎረቤታችን ቤት በሚደረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ እንዲገኝ ጋበዘው። ያሉትን ጥያቄዎች በሙሉ ሚስተር ኩክ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሊመልስለት እንደሚችል አጎቴ በእርግጠኝነት ነገረው። አባዬ ጥናቱን ጨርሶ ሲመለስ ለሁላችንም በደስታ እንዲህ አለን:- “የነበሩኝ ጥያቄዎች በሙሉ ተመለሱልኝ፤ ተጨማሪ ትምህርትም አገኘሁ! ሁሉንም ነገር የማውቅ ይመስለኝ ነበር። ሆኖም ሚስተር ኩክ ስለ ሲኦል፣ ስለ ነፍስ፣ አምላክ ለምድር ስላለው ዓላማ እና የአምላክ መንግሥት ይህን ዓላማ እንዴት እንደሚያስፈጽም ሲያብራራልኝ በእርግጥ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የማውቀው ነገር እንደሌለ ተረዳሁ!”

ቤታችን ብዙዎች የሚሰባሰቡበት ቦታ ነበር። ዘመዶቻችንና ጓደኞቻችን መጥተው ይጫወቱ ነበር። ከረሜላና ፈንዲሻ ያዘጋጁና እማዬ ፒያኖ ስትጫወት አብረው ይዘምሩ ነበር። ቀስ በቀስ በእነዚህ ነገሮች ፋንታ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ርዕሶች ላይ ውይይት ማድረግ ተጀመረ። ምንም እንኳ ልጆች የሆንነው ውይይት የሚደረግባቸውን ነገሮች ሙሉ በሙሉ መረዳት ባንችልም ወላጆቻችን ለአምላክና ለመጽሐፍ ቅዱስ የነበራቸው ጠንካራ ፍቅር በጣም ግልጽ ስለነበር እያንዳንዳችን ለአምላክና ለቃሉ ተመሳሳይ ፍቅር አዳብረናል።

ሌሎች ቤተሰቦችም በቤታቸው ሳምንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት እንዲደረግ ፈቃደኞች ሆኑ። አብዛኛውን ጊዜ ውይይቱ የሚያተኩረው በቅርብ በወጣ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ላይ በሚገኝ ርዕስ ነበር። ስብሰባው የሚደረገው አጎራባች በሆኑት በአፕልቢ እና በናከዶችስ ከተማዎች የሚኖሩ ቤተሰቦች ጋር ከሆነ የአየሩ ጠባይ ምንም ይሁን ምን ሞዴል ኤ ፎርድ መኪናችን ውስጥ ታጭቀን እንሄድ ነበር።

በተማሩት መሠረት እርምጃ መውሰድ

ወላጆቻችን እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ለመገንዘብ ብዙ ጊዜ አልፈጀባቸውም። ለአምላክ ያላቸው ፍቅር የተማሯቸውን ነገሮች ለሌሎች እንዲያካፍሉ ጠይቆባቸው ነበር። (ሥራ 20:​35) ይሁን እንጂ ወላጆቻችን በተፈጥሯቸው ራሳቸውን ዝቅ አድርገው የሚመለከቱ ዓይን አፋር ሰዎች ስለነበሩ እምነታቸውን በይፋ ለማሳወቅ የወሰዱት ይህ እርምጃ ፈታኝ ሆኖባቸው ነበር። ሆኖም ለአምላክ ያላቸው ፍቅር ለሥራ ያነሳሳቸው ሲሆን ይህ ደግሞ በይሖዋ ላይ ጥልቅ እምነት እንዲኖረን እኛን ለማስተማር ረድቷቸዋል። አባዬ ጉዳዩን እንዲህ ሲል ገልጾታል:- “ይሖዋ ገበሬዎች ሰባኪያን እንዲሆኑ አድርጓል!” በ1933 እማዬና አባዬ ቴክሳስ ውስጥ ሄንደርሰን አቅራቢያ በአንድ ኩሬ ውስጥ በመጠመቅ ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን አሳዩ።

በ1935 መጀመሪያ ላይ አባዬ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ደብዳቤ በመጻፍ ክርስቲያኖች ያላቸውን የዘላለም ሕይወት ተስፋ በተመለከተ በርካታ ጥያቄዎችን አቀረበ። (ዮሐንስ 14:​2፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:​11, 12፤ ራእይ 14:​1, 3፤ 20:​6) በወቅቱ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ከነበረው ከጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድ በቀጥታ መልስ ተላከለት። ወንድም ራዘርፎርድ ለጥያቄዎቹ መልስ ከመስጠት ይልቅ በግንቦት ወር ዋሽንግተን ዲ ሲ ውስጥ በሚደረገው የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ እንዲገኝ ጋበዘው።

‘በምርት የተሸፈነ 26 ሄክታር መሬት ያለን ገበሬዎች ነን። ስብሰባው ደግሞ የሚደረገው ሰብሉ ሁሉ ተሰብስቦ ለገበያ መቅረብ ባለበት ሰዓት ላይ ነው። መሄድ አንችልም!’ ሲል አሰበ። ሆኖም ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ጎርፍ መጣና ሰበብ ሆነውለት የነበሩትን ነገሮች ይኸውም ሰብሉን፣ የግቢ አጥሩንና ድልድዩን ሁሉ ጠራርጎ ወሰደው። ስለዚህ ከሌሎች ምሥክሮች ጋር ሆነን በተኮናተርነው የትምህርት ቤት አውቶቡስ ስብሰባው ወደሚደረግበት ቦታ ለመድረስ 1,600 ኪሎ ሜትር በስተ ሰሜን ምሥራቅ ተጓዝን።

አባዬና እማዬ ‘ታላቁን መከራ’ በሕይወት የሚያልፉት “እጅግ ብዙ ሰዎች” እነማን እንደሆኑ ስብሰባው ላይ የቀረበውን ግልጽ ማብራሪያ ሲሰሙ በጣም ተደሰቱ። (ራእይ 7:​9, 14) እማዬና አባዬ በቀሪው የሕይወት ዘመናቸው ግፊት ያሳደረባቸው ነገር ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የነበራቸው ተስፋ ነው። እንዲሁም ‘እውነተኛውን ሕይወት እንድንይዝ’ እኛን ልጆቻቸውን ያበረታቱን የነበረ ሲሆን ይህ ደግሞ ለእኛ ይሖዋ በምድር ላይ የሚሰጠንን የዘላለም ሕይወት ማግኘት ማለት ነው። (1 ጢሞቴዎስ 6:​19፤ መዝሙር 37:​29፤ ራእይ 21:​3, 4) ምንም እንኳ ገና የአምስት ዓመት ልጅ የነበርኩ ቢሆንም በዚህ አስደሳች ወቅት ከቤተሰቦቼ ጋር መሆኔ አስደስቶኝ ነበር።

ከስብሰባው ከተመለስን በኋላ እህሉን እንደገና ዘራንና መከር ሲደርስ ከዚህ በፊት አግኝተን የማናውቀውን ብዙ ምርት አስገባን። ይህ አጋጣሚ እማዬና አባዬ በይሖዋ ላይ ሙሉ ትምክህት መጣል ወሮታ እንደሚያስገኝ እንዲያምኑ ረድቷቸዋል። በአገልግሎት እያንዳንዳቸው በወር 52 ሰዓት ለማሳለፍ በመስማማት በስብከቱ ሥራ ለየት ያለ ተሳትፎ ማድረግ ጀመሩ። ከዚያም ቀጣዩ ዘር የሚዘራበት ወቅት ሲደርስ ያላቸውን ንብረት በሙሉ ሸጡ! አባዬ ለአምስታችንም መኖሪያ የሚሆን 6 በ2.4 ሜትር ስፋት ያለው ተጎታች ቤት አሠራና ቤቱን የሚጎትት አዲስ ባለ ሁለት በር ፎርድ መኪና ገዛ። አጎቴ ሞንሮይም ተመሳሳይ ነገር በማድረግ ከነቤተሰቡ በተጎታች ቤት ውስጥ መኖር ጀመረ።

እውነትን አስተማሩን

በጥቅምት 1936 አባዬና እማዬ አቅኚነት በመባል የሚታወቀውን የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመሩ። በቤተሰብ መልክ ሆነን የመንግሥቱ መልእክት ያን ያህል ባልተዳረሰባቸው በምሥራቅ ቴክሳስ በሚገኙ ወረዳዎች ውስጥ መስበክ ጀመርን። ለአንድ ዓመት ያህል ከቦታ ቦታ ብንዞርም በጥቅሉ ሲታይ ይህን ዓይነቱን አኗኗር በእርግጥ አስደሳች ሆኖ አግኝተነዋል። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች ለማዳረስ ራሳቸውን እንዳቀረቡት የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች እንድንሆን እማዬና አባዬ በቃልም ሆነ በተግባር አስተምረውናል።

በተለይ እናታችን ቤቷን በመተው ለከፈለችው መሥዋዕት አድናቆት ነበረን። ይሁን እንጂ ያልተወችው የልብስ ስፌት መኪናዋን ነበር። እንዲህ ማድረጓም ትክክል ነበር። ባላት ልብስ የመስፋት ችሎታ ተጠቅማ ሁልጊዜ ጥሩ ጥሩ ልብስ ታለብሰን ነበር። ለእያንዳንዱ የአውራጃ ስብሰባ አዲስ ቆንጆ ልብስ ይሰፋልን ነበር።

ኸርማን ጂ ሄንሼል ከቤተሰቡ ጋር ሆኖ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ንብረት በሆነ ድምፅ ማጉያ ባለው የጭነት መኪና እኛ በምንኖርበት አካባቢ የመጣበት ጊዜ በደንብ ትዝ ይለኛል። ብዙ ሕዝብ በሚኖርበት አካባቢ መኪናውን አቁመው የተቀዳ አጭር ንግግር ካሰሙ በኋላ ተጨማሪ ትምህርት ለመስጠት ወደ ሰዎቹ ቤት በመሄድ በግል ቀርበው ያነጋግሩ ነበር። ዱዊ ትንሹ በዚያን ጊዜ በአሥራዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ ከነበረው ከኸርማን ልጅ ከሚልተን ጋር መሆን ያስደስተው ነበር። አሁን ሚልተን የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት ነው።

በ1937 በኦሃዮ ኮለምበስ በተደረገ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ኤድዊና የተጠመቀች ሲሆን እማዬና አባዬ ደግሞ በልዩ አቅኚነት የማገልገል መብት ቀረበላቸው። በዚያን ጊዜ ይህ ሥራ በወር ቢያንስ 200 ሰዓት በስብከቱ ሥራ ማሳለፍ የሚጠይቅ ነበር። ወደኋላ መለስ ብዬ ሳስብ እማዬ የተወችልኝ ጥሩ ምሳሌ ባለቤቴን ባሉት ክርስቲያናዊ ሥራዎች በመርዳት ረገድ በጣም እንደጠቀመኝ እገነዘባለሁ።

አባዬ ለአንድ ቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት ሲጀምር ለልጆቻቸው ጥሩ ምሳሌ እንድንሆን እኛን ይዞን ይሄድ ነበር። የተጠቀሱትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አውጥተን እንድናነብና አንዳንድ መሠረታዊ የሆኑ ጥያቄዎችን እንድንመልስ ያደርግ ነበር። ከዚህ የተነሳ እናስጠናቸው የነበሩ አብዛኞቹ ልጆች እስካሁን ድረስ ይሖዋን በታማኝነት በማገልገል ላይ ናቸው። በእርግጥም እኛም ለአምላክ ያለንን ፍቅር ይዘን መቀጠል እንድንችል ጠንካራ መሠረት ተጥሎልን ነበር።

ዱዊ ትንሹ እያደገ ሲሄድ ከሁለት ታናናሽ እህቶቹ ጋር በእንዲህ ዓይነት የተጣበበ ቦታ መኖር አስቸጋሪ እየሆነበት መጣ። ስለዚህ በ1940 ከእኛ ተለይቶ ከሌላ የይሖዋ ምሥክር ጋር በአቅኚነት ለማገልገል መረጠ። በመጨረሻም ኦድሬ ባሮንን አገባ። በመሆኑም ወላጆቻችን ኦድሬንም ብዙ ነገሮች ያስተማሯት ሲሆን እርሷም እማዬና አባዬን በጣም ትወድዳቸው ነበር። በ1944 ዱዊ ትንሹ በክርስቲያናዊ ገለልተኝነቱ ምክንያት እስር ቤት ከገባ በኋላ ኦድሬ በተጣበበው ተጎታች ቤት ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ ከእኛ ጋር ለመኖር መጣች።

በ1941 ሚዞሪ ውስጥ በሴይንት ሉዊ በተካሄደ ትልቅ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ወንድም ራዘርፎርድ በተዘጋጀልን ወንበር ከፊት ለፊት ተቀምጠን ለነበርነው ከ5 እስከ 18 ዓመት ዕድሜ ያለን ልጆች ንግግር አቀረበ። እኔና ኤድዊና ረጋ ብሎ በግልጽ በሚሰማ ድምፅ ያቀረበውን ንግግር በጥሞና አዳመጥን። ቤት ውስጥ ለልጆቹ መመሪያ የሚሰጥ አፍቃሪ አባት ይመስል ነበር። ለወላጆች እንዲህ የሚል ማበረታቻ ሰጥቷል:- “ዛሬ ኢየሱስ ክርስቶስ የቃል ኪዳን ሕዝቡን በፊቱ ሰብስቧል። ልጆቻቸውንም በጽድቅ መንገድ ማስተማር እንዳለባቸው ጠንካራ ማሳሰቢያ ሰጥቷቸዋል።” በማከልም “ከእናንተ አይለዩ፤ እውነትንም አስተምሯቸው!” ሲል ተናገረ። ደስ የሚለው ነገር ወላጆቻችን ይህን በተግባር አውለዋል!

በዚህ ስብሰባ ላይ ጅሆቫስ ሰርቫንትስ ዲፌንድድ የተባለ ቡክሌት ያገኘን ሲሆን ቡክሌቱ የይሖዋ ምሥክሮች በዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተቀዳጅዋቸውን ድሎች ጨምሮ ድል ያገኙባቸውን ሌሎች የፍርድ ቤት ክሶች የያዘ ነበር። አባዬ ይህን መጽሐፍ በቤተሰብ መልክ አስጠናን። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ አላባማ፣ ሴልማ ውስጥ ለደረሰብን ነገር እየተዘጋጀን መሆናችንን አላወቅንም ነበር።

በሴልማ የገጠመን ተቃውሞ

ያ አስደንጋጭ ተሞክሮ በገጠመን ዕለት ጠዋት አባዬ በሴልማ ለሚገኘው ለወረዳው አዛዥ፣ ለከንቲባውና ለዋናው የፖሊስ አዛዥ በሕግ ጥላ ሥር አገልግሎታችንን የማከናወን ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዳለን የሚገልጽ የደብዳቤ ግልባጭ ሰጥቷቸው ነበር። የሆነ ሆኖ ከተማውን በኃይል ለቅቀን እንድንወጣ ለማድረግ ወሰኑ።

ከሰዓት በኋላ ረፋዱ ላይ መሣሪያ የታጠቁ አምስት ሰዎች ወደ ተጎታች ቤታችን መጥተው እናቴን፣ እህቴንና እኔን አገቱን። በመንግሥት ላይ የሸረብነው የሆነ ነገር እንዳለ ለማግኘት በቤቱ ውስጥ ያለውን ነገር ሁሉ መፈተሽ ጀመሩ። በዚህ ጊዜ አባዬ ውጭ የነበረ ሲሆን ተጎታች ቤቱን ከመኪናው ጋር እንዲያያይዝ ነገሩት። ጀምሮ እስኪጨርስ ድረስ ሽጉጥ ደግነውበት ነበር። በዚህ ጊዜ ምንም አልፈራሁም ነበር። እነዚህ ሰዎች አደገኛ እንደሆንን ማሰባቸው በጣም ስላስገረመን እኔና እህቴ በሳቅ መንፈቅፈቅ ጀመርን። ሆኖም አባዬ አየት ሲያደርገን ወዲያውኑ ሳቃችንን አቆምን።

አካባቢውን ለቅቀን ለመሄድ ስንነሳ ሰዎቹ እኔና ኤድዊና በእነርሱ መኪና አብረናቸው እንድንሄድ ፈለጉ። አባዬ “ሞቼ እገኛለሁ!” እንጂ አይሆንም ሲል ፈጽሞ የማይቻል ነገር መሆኑን ገለጸ። ጥቂት ከተነጋገሩ በኋላ ሰዎቹ በመኪናቸው እየተከተሉን ቤተሰባችን አንድ ላይ ሆኖ እንዲሄድ ፈቀዱ። ከከተማው ወደ 25 ኪሎ ሜትር ገደማ ከራቅን በኋላ መኪናችንን ዳር አስይዘን እንድናቆም ምልክት ሰጡን። ከዚያም እማዬንና አባዬን ወሰዷቸው። ሰዎቹ ተራ በተራ እነርሱን ለማግባባት በመሞከር እንዲህ አሏቸው:- “ይኼ ሃይማኖት ይቅርባችሁ። ወደ ግብርና ሥራ ተመልሳችሁ ልጆቻችሁን በሥርዓት ብታሳድጉ ይሻላችኋል!” አባዬ ሊያስረዳቸው ቢሞክርም ጥረቱ ምንም ውጤት ሳያስገኝ ቀረ።

በመጨረሻ አንደኛው እንዲህ አለን:- “በሉ ከዚህ ጥፉ፤ ካሁን በኋላ ወደ ዳላስ ዝር ብትሉ አንዳችሁም አትተርፉም!”

ከችግሩ ተገላግለንና እንደገና አንድ ላይ ሆነን ለረጅም ሰዓት ከተጓዝን በኋላ ሌሊቱን ለማሳለፍ መኪናችንን አቆምን። የመኪናቸውን የሰሌዳ ቁጥር ጽፈን ነበር። አባዬ ያጋጠመንን ነገር ሁሉ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ወዲያውኑ ሪፖርት አድርጎ ስለነበር ከጥቂት ወራት በኋላ ሰዎቹ ተይዘው ታሰሩ።

ጊልያድ የሚስዮናውያን ትምህርት ቤት ገባን

በ1946 ኤድዊና ኒው ዮርክ ውስጥ በደቡብ ላንሲንግ በሚገኘው የጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት በ7ኛው ክፍል እንድትካፈል ግብዣ ቀረበላት። ከአስተማሪዎቹ አንዱ የሆነው አልበርት ሽሮደር በወቅቱ በብሩክሊን ኒው ዮርክ በሚገኘው በዓለም አቀፉ የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ማለትም በቤቴል ያገለግል ለነበረው ለቀድሞው የአቅኚነት ጓደኛው ለቢል ኢልሮድ ስለ እርሷ መልካም ባሕርያት ነገረው።a ኤድዊና እና ቢል ተዋወቁና ከጊልያድ ከተመረቀች ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ተጋቡ። ለአምስት ዓመት በቤቴል አብረው ያገለገሉበትን ጊዜ ጨምሮ ለብዙ ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ ቆይተዋል። ከዚያም በ1959 ወንድም ሽሮደር ውድ ጓደኛው መንትዬ የሆኑ የአንድ ወንድና የአንዲት ሴት ልጅ አባት እንደሆነ ለ34ኛው የጊልያድ ክፍል አስታወቀ።

በ1947 ማብቂያ ላይ በሜሪዲያን፣ ሚሲሲፒ ከወላጆቼ ጋር እያገለገልኩ በነበረበት ወቅት ሦስታችንም በ11ኛው የጊልያድ ትምህርት ቤት እንድንካፈል ጥሪ ቀረበልን። ከሚጠየቀው መስፈርት አንጻር የእኔ ዕድሜ ገና ያልደረሰ ሲሆን የእማዬና የአባዬ ደግሞ በጣም አልፎ ስለነበረ ጥሪው ሲቀርብልን በጣም ተገረምን። ሆኖም ልዩ አስተያየት ተደረገልንና ይገባናል የማንለውን ከፍተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የማግኘት መብት አገኘን።

ከወላጆቼ ጋር በሚስዮናዊነት አገለገልኩ

በሚስዮናዊነት እንድናገለግል የተመደብነው በደቡብ አሜሪካ ኮሎምቢያ ነበር። ሆኖም ሌሎች ሦስት ሚስዮናውያን በሚኖሩበት በቦጎታ ወደሚገኘው የሚስዮናውያን ቤት የመጣነው ከተመረቅን ከአንድ ዓመት በላይ ቆይተን ታኅሣሥ 1949 ነበር። መጀመሪያ ላይ አባዬ እርሱ ስፓንኛ ከሚማር ይልቅ ሰዎቹን እንግሊዝኛ ማስተማር በጣም ይቀልላል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሶ ነበር! አዎን፣ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ነበሩ፤ ሆኖም ያገኘናቸው በረከቶች እንዴት ብዙ ናቸው! በ1949 ኮሎምቢያ ውስጥ የነበሩት ምሥክሮች መቶ እንኳ የማይሞሉ ሲሆኑ አሁን ግን ከ100,000 በላይ ሆነዋል!

እማዬና አባዬ ቦጎታ ውስጥ ለአምስት ዓመት ያህል ካገለገሉ በኋላ ካሊ ወደሚባል ከተማ ተላኩ። በመሀሉ በ1952፣ በኮሎምቢያ ከሚኖር ሮበርት ትሬሲ ከሚባል ሚስዮናዊ ጋር ተጋባን።b እስከ 1982 ድረስ ኮሎምቢያ ውስጥ የቆየን ሲሆን በዚያው ዓመት ወደ ሜክሲኮ ተልከን እስከ አሁን ድረስ በእዚያው እያገለገልን ነው። በመጨረሻ በ1968 ወላጆቼ ለሕክምና ወደ ዩናይትድ ስቴትስ መመለስ ነበረባቸው። ጤንነታቸው ከተመለሰላቸው በኋላ አላባማ ውስጥ ሞባይል አቅራቢያ በልዩ አቅኚነት ማገልገላቸውን ቀጠሉ።

ወላጆቻችንን መንከባከብ

ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ እማዬና አባዬ አቅም እያጡ በመምጣታቸው ከበፊቱ የበለጠ ድጋፍና እንክብካቤ ያስፈልጋቸው ጀመር። በጥያቄያቸው መሠረት በአላባማ፣ አቴንስ ውስጥ ኤድዊና እና ቢል በሚኖሩበት አቅራቢያ እንዲያገለግሉ ተመደቡ። ከጊዜ በኋላ ወንድማችን ዱዊ ትንሹ ቤተሰቡ ሳይራራቅ በደቡብ ካሮላይና እንዲኖር ማድረጉ ጥበብ እንደሚሆን አሰበ። ስለዚህ ቢል እማዬንና አባዬን ይዞ ከቤተሰቡ ጋር ወደ ግሪንዉድ ተዛወረ። ይህ ፍቅራዊ ዝግጅት መደረጉ ወላጆቼ ጥሩ እንክብካቤ እንደሚያገኙ እንድገነዘብ ስላስቻለኝ እኔና ሮበርት በኮሎምቢያ የሚስዮናዊነት አገልግሎታችንን ለመቀጠል ችለናል።

ከዚያም በ1985 አባዬ ስትሮክ በተባለ በሽታ ሳቢያ ልሳኑ ከመዘጋቱም በላይ የአልጋ ቁራኛ ሆነ። ወላጆቻችንን እንዴት በተሻለ ሁኔታ መንከባከብ እንደምንችል ለመነጋገር አንድ ላይ ተገናኝተን የቤተሰብ ስብሰባ አደረግን። በዋነኛነት አባዬን የምትንከባከበው ኦድሬ እንድትሆን፣ እኔና ሮበርት ደግሞ በየሳምንቱ የሚያበረታቱ ተሞክሮዎችን በደብዳቤ እየጻፍን መላካችንና አቅም በፈቀደልን መጠን ቶሎ ቶሎ እየመጣን መርዳታችን ጥሩ እንደሚሆን ተወሰነ።

ለመጨረሻ አባዬን ያየሁበት ጊዜ እስካሁን በደንብ ትዝ ይለኛል። እንደ ወትሮው አጥርቶ መናገር አቅቶት ነበር፤ ሆኖም ወደ ሜክሲኮ ልንመለስ መሆኑን ከነገርነው በኋላ በከፍተኛ ጥረትና በስሜት እንደምንም ብሎ “ይቅናችሁ!” ሲል አንዲት ቃል ተነፈሰ። እንዲህ ሲል በተመደብንበት የሚስዮናዊ ሥራ ለመቀጠል ያደረግነውን ውሳኔ እንደሚደግፍ አወቅን። እርሱ ሐምሌ 1987 ላይ የሞተ ሲሆን እማዬ ደግሞ ከዘጠኝ ወር በኋላ ሞተች።

መበለት ከሆነችው እህቴ የደረሰኝ ደብዳቤ ሁለታችንም ለወላጆቻችን ያለንን የአድናቆት ስሜት በጥሩ ሁኔታ ጠቅለል አድርጎ ይገልጸዋል። “ያገኘሁትን የላቀ ክርስቲያናዊ ቅርስ ከፍ አድርጌ እመለከተዋለሁ። ወላጆቻችን ከዚህ በተለየ ሁኔታ እኛን ለማሳደግ ቢመርጡ ኖሮ ይበልጥ ደስተኛ እሆን ነበር የሚል ስሜት መጥቶብኝ አያውቅም። ጠንካራ እምነት በመያዝ፣ የራስን ጥቅም በመሠዋትና በይሖዋ ላይ ሙሉ እምነት በማሳደር ረገድ የተዉልን ምሳሌ በሕይወቴ ውስጥ ያጋጠሙኝን አሳዛኝ አጋጣሚዎች እንድቋቋም ረድቶኛል።” ኤድዊና እንዲህ በማለት ደምድማለች:- “ሕይወታችን አፍቃሪ የሆነው አምላካችንን ይሖዋን በማገልገል ላይ እንዲያተኩር ካደረግን ልናገኘው የምንችለውን ደስታ በቃልም ሆነ በተግባር ያሳዩንን ወላጆች ስለሰጠን ይሖዋን አመሰግነዋለሁ።”

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a መጠበቂያ ግንብ 6-109 ከገጽ 4 እስከ 5 ተመልከት።

b የመጋቢት 15, 1960 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 189-91ን ተመልከት።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የፋውንቴን ቤተሰብ:- (ከግራ ወደ ቀኝ) ዱዊ፣ ኤድዊና፣ ዊኒ፣ ኤሊዛቤት፣ ዱዊ ትንሹ፤ ቀኝ:- ኤሊዛቤትና ዱዊ ትንሹ ድምፅ ማጉያ ያለው የሄንሼል የጭነት መኪና ፈረፋንጎ ላይ ተቀምጠው (1937)፤ ከታች በስተ ቀኝ:- ኤሊዛቤት በ16 ዓመቷ ከፊትና ከኋላ የሚንጠለጠል ማስታወቂያ አንግታ ስታገለግል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ