የገና በዓል በምሥራቃውያን ዘንድ ሳይቀር የሚከበረው ለምንድን ነው?
ከገና አባት ጋር የሚመሳሰል አንድ ጥንታዊ የምሥራቃውያን እምነት አለ። ይህ እምነት ቾዋንግሺን በመባል የሚታወቅ የኮሪያውያን እምነት ሲሆን አንዳንድ ቻይናውያንና ጃፓናውያንም ተመሳሳይ እምነት አላቸው።
ቾዋንግሺን በማዕድ ቤት የእሳት አምላክ እንደሆነ ተደርጎ ይታመን የነበረ ሲሆን ከጥንት የኮሪያውያን የእሳት አምልኮ ጋር ይዛመዳል። (ጥንት ኮሪያውያን እንዳይጠፋ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ የከሰል ፍም ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ይዘው ይሄዱ ነበር።) ይህ አምላክ ለአንድ ዓመት የቤተሰብ አባላትን ተግባር ሲከታተል ከቆየ በኋላ በማዕድ ቤቱ ምድጃና በጭስ ማውጫው በኩል ወደ ሰማይ ይሄዳል ተብሎ ይታመናል።
ከዚያም ቾዋንግሺን በታኅሣሥ ወር 23ኛ ቀን ላይ ለሰማይ ንጉሥ ሪፖርት ያቀርባል ተብሎ ይገመት ነበር። ለእያንዳንዱ የቤተሰብ አባል እንደየተግባሩ ሽልማትና ቅጣት ለማስረከብ በዓመቱ መጨረሻ ላይ በጭስ ማውጫውና በምድጃው በኩል ተመልሶ እንደሚመጣ ይጠበቃል። በሚመለስበት ዕለት የቤተሰቡ አባላት በማዕድ ቤትም ሆነ በቤቱ ውስጥ በማንኛውም ቦታ ሻማ ያበራሉ። ይህ የማዕድ ቤት አምላክ በተለያዩ ሥዕሎች ቀይ ልብስ እንደለበሰ ሆኖ መገለጹ ሌላው ከገና አባት ጋር የሚያመሳስለው ገጽታ ነው! በኮሪያውያን ባሕል መሠረት አንዲት ምራት የክረምቱ ወቅት በሚገባበት ቀን ላይ ባሕላዊ የኮሪያ የእግር ሹራቦችን ሠርታ ለአማቷ ትሰጣለች። ይህም ከዚያን ቀን ጀምሮ ቀኖቹ ስለሚረዝሙ አማቷ ረጅም ዕድሜ እንዲኖሩ ያላትን ምኞት የሚገልጽ ነው።
ከላይ በጠቃቀስናቸው ነገሮችና በገና በዓል መካከል አንዳንድ የሚመሳሰሉ ነገሮች እንዳሉ ትመለከታለህ? ጭስ ማውጫው፣ ሻማው፣ ስጦታ መለዋወጡ፣ የእግር ሹራቡ፣ ቀይ የለበሰው ሽማግሌና ቀኑ ይህ እምነትና የገና በዓል ተመሳሳይ ታሪክና ልማድ እንዳላቸው የሚያሳዩ ናቸው። የገና በዓል በኮሪያ በቀላሉ ተቀባይነት እንዲያገኝ ያደረጉት እነዚህ ተመሳሳይነቶች ብቻ አይደሉም። የገና በዓል ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኮሪያ በገባበት ወቅት የቾዋንግሺን እምነት ጨርሶ ጠፍቶ ነበር ለማለት ይቻላል። እንዲያውም ዛሬ ያሉ አብዛኞቹ ኮሪያውያን እንዲህ ዓይነት እምነት እንደነበረም እንኳ አያውቁም።
ያም ሆነ ይህ ከክረምቱ መግቢያና ከዓመቱ መጨረሻ ጋር የተያያዙ ልማዶች በተለያየ መንገድ በመላው ዓለም እንዴት ሊሠራጩ እንደቻሉ ያሳያል። በአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ በሮም ግዛት ተስፋፍቶ የነበረው ቤተ ክርስቲያን የፀሐይ አምላክ የልደት ቀን የሆነውን ሳተርናሊያ የተባለውን የሮማውያንን አረማዊ በዓል ስሙን በመቀየር የገና በዓል ክፍል አደረገው። በገና በዓል ስም እንደ አዲስ ብቅ ያሉት የአካባቢው ልማዶች ናቸው። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?
ስጦታ መለዋወጥ የተጫወተው ሚና
ሳይጠፋ እንዳለ የቀጠለ አንዱ ልማድ ስጦታ መለዋወጥ ነው። ኮሪያውያን ከጥንት ጀምሮ ስጦታ መለዋወጥ በጣም ያስደስታቸዋል። የገና በዓል በኮሪያውያን ዘንድ ተወዳጅ እንዲሆን አስተዋጽዖ ያደረገው አንዱ ምክንያት ይህ ነበር።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በኮሪያ ሰፍረው የነበሩ የአሜሪካ ወታደሮች ከሕዝቡ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ይፈልጉ የነበረ ሲሆን ስጦታና እርዳታ የሚያከፋፍሉት በአብያተ ክርስቲያናት ነበር። በተለይ ይህን የሚያደርጉት በገና በዓል ዕለት ነበር። ብዙ ልጆች ምን እየተደረገ እንዳለ ለማወቅ በመጓጓት ወደ ቤተ ክርስቲያኖች ብቅ ይሉ ነበር፤ እዚያም ለመጀመሪያ ጊዜ የቸኮላት ስጦታ አገኙ። ይህም ብዙዎቹ ልጆች መጪውን የገና በዓል በጉጉት እንደሚጠብቁ እንዳደረጋቸው የታወቀ ነው።
ለእነዚህ ልጆች የገና አባት ማለት ቀይ የሹራብ ቆብ ያጠለቀ የአሜሪካ ወታደር ነው። ምሳሌ 19:6 “ስጦታ ለሚሰጥም ሁሉ ወዳጅ ነው” ይላል። አዎን፣ ስጦታ መስጠት ትልቅ ውጤት አስገኝቷል። ከዚህ ጥቅስ መረዳት እንደሚቻለው እንዲህ ዓይነት ስጦታዎች ዘላቂ የሆነ ወዳጅነት ለመመሥረት ዋስትና አይሆኑም። በኮሪያም ቢሆን ብዙዎች ከቤተ ክርስቲያን ጋር በተያያዘ ትዝ የሚላቸው ነገር ቢኖር በልጅነታቸው የበሉት ቸኮላት ብቻ ነው። ያም ሆኖ ግን የገና በዓል አልተረሳም ነበር። የኮሪያ ኢኮኖሚ ፈጣን እድገት ሲያደርግ ንግዱም የዚያኑ ያህል አድጓል፤ በገና በዓል ወቅት የሚኖረው ስጦታ የመለዋወጥ ልማድ የሸማቹን ፍላጎት ከፍ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል። ነጋዴዎች ትርፍ ለማጋበስ የገናን ወቅት እንደ ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅመውበታል።
ይህም የገና በዓል በዛሬው ጊዜ በምሥራቃውያን ዘንድ ምን መልክ እንዳለው እንድታስተውል ይረዳሃል። በገና በዓል ወቅት ገበያ ስለሚደራ አዳዲስ ምርቶች እንደ አሸን ይፈላሉ። ከበጋው አጋማሽ ጀምሮ የንግድ ማስታወቂያዎች ዝግጅቶች ይጧጧፋሉ። የገና ስጦታዎች፣ ካርዶችና የሙዚቃ ክሮች በገፍ ስለሚሸጡ በዓመቱ መጨረሻ ላይ የሽያጩ መጠን ከምንጊዜውም ይበልጥ ከፍ ይላል። የንግድ ማስታወቂያዎች አንድ ወጣት ወይም አንዲት ወጣት በገና በዓል ዋዜማ ዕለት እቤታቸው ቁጭ ካሉና ምንም ዓይነት ስጦታ ካላገኙ ምስኪኖች እንደሆኑ እንዲሰማቸው ያደርጋሉ!
የገና በዓል ሲቃረብ በሴዉል የሚገኙ ሱቆችና የገበያ አዳራሾች ስጦታዎች በሚገዙ ሰዎች ይጨናነቃሉ። በሌሎች ምሥራቃውያን ከተሞችም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በየቦታው ከፍተኛ የሆነ የእግረኛና የተሽከርካሪ ትርምስ ይፈጠራል። ሆቴሎች፣ የንግድ አካባቢዎች፣ ምግብ ቤቶችና የምሽት ጭፈራ ቤቶች በሰዎች ይጥለቀለቃሉ። ጭፈራው፣ ዘፈኑ ይቀልጣል። የገና ዋዜማ ዕለት የሰከሩ ወንዶችና ሴቶች በቆሻሻዎች በተሞሉ ጎዳናዎች ላይ እየተወላገዱ ሲሄዱ ይታያሉ።
እንግዲህ ገና ማለት ይሄ ነው። በምሥራቃውያን ዘንድ የገናን በዓል በግንባር ቀደምትነት የሚያከብሩት ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች መሆናቸው ቀርቷል። እንደ ሌሎች ቦታዎች ሁሉ በኮሪያም በዚህ የሕዝበ ክርስትና በዓል ወቅት ዋነኛው ተጠቃሚ የንግዱ ዓለም ነው። ታዲያ የገና በዓል ጨርሶ የክርስቶስ መንፈስ የማይንጸባረቅበት እንዲሆን በማድረግ ረገድ ሙሉ በሙሉ ተጠያቂው የንግዱ ዓለም ነውን? እውነተኛ ክርስቲያኖች ከዚህ ጋር የተያያዘውን አሳሳቢ ጥያቄ ጠለቅ ብለው መመርመር አለባቸው።
የገና በዓል አመጣጥ
አንድ የዱር እንስሳ አራዊት በሚጠበቁበት ቦታ በሽቦ አጥር ውስጥ ተከልሎ ቢቀመጥም የአውሬነት ባሕርይው አይለቀውም። በተከለለበት የሽቦ አጥር ውስጥ ከግልገሎቹ ጋር ሲጫወት ስለታየ ብቻ ለማዳ የቤት እንስሳ ሆኗል ብሎ ማሰብ ትልቅ ስህተት ይሆናል። አራዊት በሚጠበቁበት ቦታ የሚሠሩ ሠራተኞች ጉዳት እንደደረሰባቸው የሚገልጹ ሪፖርቶች ሰምተህ ታውቅ ይሆናል።
በአንዳንድ ሁኔታ ሲታይ ስለ ገና በዓልም ተመሳሳይ ነገር ለማለት እንችላለን። በአንድ ወቅት የገና በዓል ከክርስትና ውጭ የሚኖር “አውሬ” ነበር። (በኮሪያ ቋንቋ የተዘጋጀው) ዘ ክርስቺያን ኢንሳይክሎፔዲያa “ከሮማውያን ሳተርናሊያ ጋር ያለው ዝምድና” በሚል ንዑስ ርዕስ ስር ስለ ገና የሚከተለውን አስፍሯል:-
“ሳተርናሊያ እና ብሩማሊያ የተባሉት አረማዊ በዓላት በሕዝቡ ዘንድ ሥር የሰደዱ ባሕሎች ስለነበሩ ክርስትና በቀላሉ ተጽእኖ ሊያሳድርባቸው አልቻለም። ሰንዴይ (የፎበስ እና የሚትራስ እንዲሁም የጌታ ቀን) በንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ እውቅና ማግኘቱ . . . በአራተኛው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች የግዑዟ ፀሐይና የአምላክ ልጅ የልደት ቀን እንዲገጣጠም ማድረጉ ተገቢ እንደሆነ እንዲሰማቸው ሳያደርግ አልቀረም። በሁከትና መረን በለቀቀ ፈንጠዚያ የተሞላው አረማዊ በዓል በሕዝቡ ዘንድ በጣም ተወዳጅ መሆኑ ክርስቲያኖች ይህን በዓል መንፈሱን ወይም ባሕሉን ብዙም ሳይለውጡ እንዳለ እንዲቀበሉት ጥሩ ሰበብ ሆኖላቸዋል።”
ይህ ድርጊት ምንም ተቃውሞ አልገጠመውም ብለህ ታስባለህን? ይሄው ኢንሳይክሎፔዲያ እንዲህ ይላል:- “ይህን አረማዊ በዓል እንደ ክርስትና በዓል አድርገው በመቀበላቸው በሜሶጶጣሚያ የሚገኙ ክርስቲያኖች ምዕራባውያን ወንድሞቻቸውን በጣዖት አምልኮና በፀሐይ አምልኮ ሲከሱ የምዕራብና የቅርብ ምሥራቅ ሰባኪያን ደግሞ የክርስቶስን ልደት ከአረማዊ በዓል ጋር ለማገጣጠም የተደረገውን ተገቢ ያልሆነ ሙከራ ተቃውመዋል።” እውነቱን ለመናገር ነገሩ የጠፋው ከመጀመሪያው ነው። ኢንሳክሎፔዲያው “ይህ በዓል በፍጥነት ተቀባይነት እያገኘ ስለመጣና በመጨረሻ በጣም ስር ስለሰደደ በአሥራ ስድስተኛው መቶ ዘመን የተካሄደው የፕሮቴስታንት አብዮት እንኳ ነቅሎ ሊጥለው አልቻለም” ሲል ገልጿል።
አዎን፣ ከእውነተኛ ክርስትና ውጭ የነበረው የፀሐይ አምላክ ክብረ በዓል በወቅቱ ገናና በነበረው ቤተ ክርስቲያን ተቀባይነት አገኘ። አረማዊ ልማዶቹን እንደያዘ ሌላ ስም ተሰጠው። በስመ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ አረማዊ አምልኮን ለማስረጽና የግለሰቦችን መንፈሳዊነት ለመበከል አገልግሏል። ሕዝበ ክርስትና እየሰፋች ስትሄድ ቀደም ሲል የነበረው “ጠላትህን ውደድ” የሚለው ዝንባሌ በሥነ ምግባር ውድቀትና በአስከፊ ጦርነቶች እየተተካ እንደሄደ ታሪክ ይመሰክራል።
የገና በዓል ምንም እንኳ የማስመሰያ ስም ቢሰጠውም ቅጥ ያጣ ፈንጠዚያው፣ አለ ልክ መጠጣቱ፣ ጭፈራው፣ ስጦታ መለዋወጡና ቤትን በጥድ ዛፍ ማሸብረቁ አረማዊ አመጣጥ ያለው መሆኑን እንደሚያሳይ ከጊዜ በኋላ ግልጽ ሆኗል። በንግዱ መስክ ከፍተኛ ገቢ ለማጋበስ እንደ ገና በዓል ያለ ወቅት አልተገኘም። መገናኛ ብዙሐን ስለ ገና በዓል ብዙ ይለፍፋሉ፤ ሕዝቡም እንደ ጥሩ መዝናኛ አድርጎ ይመለከተዋል። በሴዉል መሐል ከተማ የሚገኝ የውስጥ ሱሪዎችን የሚሸጥ አንድ ሱቅ በውስጥ ሱሪዎች ያሸበረቀ የገና ዛፍ በመስታወቱ ውስጥ አቁሞ በቴሌቪዥን አስተዋውቋል። የገና በዓል የሚከበርበት ወቅት እንደሆነ የሚያሳይ ብዙ ነገር ቢኖርም ‘ስለ ክርስቶስ እንድናስብ’ የሚያደርግ ምንም ነገር የለም።
ገና ከቅዱሳን ጽሑፎች አንጻር ሲመረመር
ከዚህ የገና በዓል ታሪካዊ አመጣጥና እድገት ምን እንማራለን? አንድን ቁልፎቹ ተዛብተው የተቆለፉ ሸሚዝ እንደገና አስተካክሎ ለመቆለፍ ያለው አማራጭ እንደገና ሀ ብሎ መቆለፍ መጀመር ነው። አይደለም እንዴ? ሐቁ ይህ ቢሆንም አንዳንዶች የገና በዓል ከፀሐይ አምልኮ ጋር የተያያዘ አረማዊ አመጣጥ ያለው ቢሆንም እንኳ በሕዝበ ክርስትና ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል ብለው ይከራከራሉ። ስለዚህ ይህ በዓል የክርስቶስ ልደት ቀን በመሆን ተቀድሷል እንዲሁም አዲስ መንፈስ ይዟል ብለው ያስባሉ።
በጥንቷ ይሁዳ ከደረሰ አንድ ታሪካዊ ሁኔታ ጥሩ ትምህርት ልንማር እንችላለን። በ612 ከዘአበ የይሁዳ ነዋሪዎች በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ አረማዊ የፀሐይ አምልኮ ማካሄድ ጀምረው ነበር። ይህ አረማዊ አምልኮ የይሖዋ ንጹህ አምልኮ በሚከናወንበት ቦታ ላይ የሚካሄድ መሆኑ ቅዱስ እንዲሆን አድርጎት ነበርን? በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ የሚካሄደውን የፀሐይ አምልኮ በተመለከተ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ሕዝቅኤል እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እነሆም፣ በእግዚአብሔር መቅደስ መግቢያ ፊት በወለሉና በመሠዊያው መካከል ሀያ አምስት የሚያህሉ ሰዎች ነበሩ . . . ፊታቸውም ወደ ምሥራቅ ነበረ፤ እነርሱም ወደ ምሥራቅ ለፀሐይ ይሰግዱ ነበር። እርሱም:- የሰው ልጅ ሆይ፣ ይህን አይተሃልን? በዚህ የሚያደርጉትን ይህን ርኩሰት ያደርጉ ዘንድ ለይሁዳ ቤት ጥቂት ነገር ነውን? ምድሪቱን በግፍ ሞልተዋታል ያስቆጡኝም ዘንድ ተመልሰዋል፤ እነሆም፣ ቅርንጫፉን ወደ አፍንጫው አቅርበዋል።”—ሕዝቅኤል 8:16, 17
አዎን፣ ይህ አረማዊ አምልኮ ቅዱስ ከመሆን ይልቅ መላውን ቤተ መቅደስ አደጋ ላይ ጥሏል። ይህ ዓይነቱ ድርጊት በይሁዳ መስፋፋቱ በዚያ ምድር ዓመፅና የሥነ ምግባር ውድቀት እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ አድርጓል። ሳተርናሊያ ከሚባለው የፀሐይ አምልኮ የመነጨውን ገናን በግንባር ቀደምትነት በምታከብረው በሕዝበ ክርስትና ውስጥም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ሕዝቅኤል ያን ራእይ ከተቀበለ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ኢየሩሳሌም በባቢሎናውያን እጅ በደረሰባት ጥፋት አማካኝነት የአምላክን ፍርድ ቀምሳለች።—2 ዜና መዋዕል 36:15-20
ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የቀረበው አንድ ኮሪያዊ ምሁር ልጅ ስለነበረው ኢየሱስ የሰጡት መግለጫ አስገርሞህ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ስለ ክርስቶስ ትክክለኛ እውቀት የሌላቸው ሰው የሰጡት አስተያየት ስለሆነ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። የገናን በዓል የሚያከብሩ ሰዎች በቁም ነገር እንዲያስቡበት የሚያደርግ ሊሆን ይችላል። ለምን? ምክንያቱም የገና በዓል በትክክል ኢየሱስን የሚወክል አይደለም። እንዲያውም ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ በትክክል በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ እንዳይታወቅ የሚያደርግ ነው። ኢየሱስ አሁንም በግርግም ውስጥ የሚገኝ ሕፃን አይደለም።
በአሁኑ ጊዜ ኢየሱስ መሲህ ማለትም ሰማያዊ የአምላክ መንግሥት ኃያል ንጉሥ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ ይገልጻል። (ራእይ 11:15) በገና ወቅት አንዳንድ ሰዎች ምጽዋት በማድረግ የተወሰነ ትኩረት ለሚሰጡት ድህነትና ጉስቁልና ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ኢየሱስ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።
ገና የሕዝበ ክርስትና አገሮችንም ሆነ ሌሎች አገሮችን (ምሥራቃውያን አገሮችንም ጭምር ማለት ነው) ምንም እንዳልጠቀመ ግልጽ ነው። ከዚያ ይልቅ ስለ አምላክ መንግሥትና አሁን ያለው ክፉ ሥርዓት ስለሚያከትምበት ሁኔታ ከሚናገረው እውነተኛ የክርስትና መልእክት የሰዎችን ትኩረት ዞር የሚያደርግ ነው። (ማቴዎስ 24:14) አሁን ያለው ክፉ ሥርዓት እንዴት እንደሚያከትም የይሖዋ ምሥክሮችን እንድትጠይቃቸው እንጋብዝሃለን። ከዚያም ይህ ሥርዓት ከጠፋ በኋላ በአምላክ መንግሥትና ንጉሥ ሆኖ በተሾመው በኢየሱስ ክርስቶስ አመራር ሥር በምድር ላይ ስለሚፈሱት ዘላቂ በረከቶች መማር ትችላለህ።—ራእይ 21:3, 4
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ዘ ኒው ሻፍ-ህርትሶክ ኢንሳይክሎፔዲያ ኦቭ ሪሊጂየስ ኖውሌጅ እንዳቀረበው።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
የገና በዓል በስመ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ አረማዊ አምልኮ እንዲሰርጽ አድርጓል
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብዙ ልጆች ምን እየተደረገ እንዳለ ለማወቅ በመጓጓት ወደ ቤተ ክርስቲያን ብቅ ይሉ የነበረ ሲሆን እዚያም የቸኮላት ስጦታ ይሰጣቸው ነበር። ስለሆነም መጪውን የገና በዓል በጉጉት ይጠብቁ ነበር
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኮሪያ ሴዉል መሐል ከተማ የገና በዓል ዋዜማ
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአሁኑ ጊዜ ክርስቶስ ሕፃን ሳይሆን የአምላክ መንግሥት ኃያል ንጉሥ ነው