የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w02 11/1 ገጽ 20-25
  • በተመደብንበት ቦታ በጽናት አገልግለናል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በተመደብንበት ቦታ በጽናት አገልግለናል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • እውነትን አገኘሁ
  • በይሖዋ ምሥክሮች የእርሻ ቦታ መሥራት
  • ያልተጠበቀ አጋጣሚ
  • ወደ እስር መመለስ
  • “እባክዎ ይህን ካርድ ያንብቡት”
  • ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ሥራ
  • በተመደብንበት ቦታ በመጽናታችን ተባርከናል
  • በይሖዋ ላይ ያለኝ ትምክህት ደግፎ አቁሞኛል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • መጽናት ደስታ ያስገኛል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
  • በይሖዋ ፍቅራዊ እንክብካቤ መታመን
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2004
  • የይሖዋን ግብዣዎች መቀበል በረከት ያስገኛል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
w02 11/1 ገጽ 20-25

የሕይወት ታሪክ

በተመደብንበት ቦታ በጽናት አገልግለናል

ሄርማን ብሩደ እንደተናገረው

የቀረበልኝ ምርጫ በባዕድ አገር በተሠማራው የፈረንሳይ ክፍለ ጦር ውስጥ ለአምስት ዓመት ማገልገል አለዚያ ደግሞ በሞሮኮ እስር ቤት መታሰር ነበር። እንዲህ ያለ አጣብቂኝ ውስጥ እንዴት እንደገባሁ ልንገራችሁ።

አንደኛው የዓለም ጦርነት ከመፈንዳቱ ከሦስት ዓመት በፊት በ1911 በኦፔኖ ጀርመን ተወለድኩ። ወላጆቼ ዮዜፍና ፍሪዳ ብሩደ ከወለዷቸው 17 ልጆች መካከል 13ኛ ልጅ ነበርኩ።

በልጅነቴ እንኖርበት በነበረው ከተማ ውስጥ አንድ የሙዚቃ ጓድ ወታደራዊ የሙዚቃ ማርሽ እያሰማ በአውራ ጎዳናው ላይ ሲጓዝ መመልከቴን አስታውሳለሁ። ሙዚቀኞቹን ተከትዬ ባቡር ጣቢያ ስደርስ አባቴና ሌሎች ሰዎች ወታደራዊ መለዮ ለብሰው ሲሳፈሩ ተመለከትሁ። ባቡሩ ሲሄድ በጣቢያው የነበሩ አንዳንድ ሴቶች ያለቅሱ ነበር። ጥቂት ቆይቶ እናት አገራቸውን ለማስከበር ሲሉ ሕይወታቸው ያለፈ አራት ሰዎችን አስመልክቶ የሰፈራችን ቄስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ረዘም ያለ ንግግር የሰጡ ሲሆን “በዚህ ሰዓት እነሱ በሰማይ ናቸው” ብለው ሲናገሩ አጠገቤ ያለችው ሴት ራሷን ሳተችና ወደቀች።

አባቴ በሩስያ ግንባር ተሰልፎ ሳለ የታይፎይድ በሽታ ያዘው። ቤት ሲደርስ በጣም ደክሞ ስለነበር በአቅራቢያ ወዳለው ሆስፒታል ወስደነው እንዲተኛ ተደረገ። ቄሱ “አባትህ እንዲድን ከመቃብር ቦታ አጠገብ ወዳለችው ጸሎት ቤት ገብተህ 50 ጊዜ አባታችን ሆይ፣ 50 ጊዜ ደግሞ እመቤታችን ማርያም ሆይ የሚለውን ጸሎት ድገም” አሉኝ። እንዳሉኝ ባደርግም አባቴ በነጋታው ሞተ። ገና ልጅ የነበርኩ ቢሆንም ጦርነቱ መጥፎ ጠባሳ ጥሎብኝ አልፏል።

እውነትን አገኘሁ

በጦርነቱ ምክንያት ጀርመን ውስጥ ሥራ ማግኘት አስቸጋሪ ነበር። ሆኖም በ1928 ትምህርት ከጨረስኩ በኋላ በስዊዘርላንድ ባዘል ከተማ ውስጥ በአትክልተኝነት ተቀጠርኩ።

ልክ እንደ አባቴ አጥባቂ ካቶሊክ ስለነበርኩ በሕንድ አገር መነኩሴ ሆኜ የማገልገል ከፍተኛ ፍላጎት ነበረኝ። በወቅቱ የይሖዋ ምሥክር የነበረው ታናሽ ወንድሜ ሪቻርት ይህን ሲሰማ ሐሳቤን ለማስለወጥ ሲል ስዊዘርላንድ ድረስ መጣ። በሰዎች በተለይም ደግሞ በቀሳውስት መታመን አደገኛ መሆኑን ካሳሰበኝ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን እንዳነብና በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ እንድታመን አበረታታኝ። የሰጠኝ ምክር ብዙም ባይዋጥልኝም አዲስ ኪዳንን ማንበብ ጀመርኩ። ቀስ በቀስ ብዙዎቹ የማምንባቸው ነገሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር የማይጣጣሙ መሆናቸው ግልጽ እየሆነልኝ መጣ።

በ1933 እሁድ ቀን ሪቻርት ቤት ሳለሁ የይሖዋ ምሥክር ከሆኑ ባልና ሚስት ጋር አስተዋወቀኝ። መጽሐፍ ቅዱስ እንደማነብ ሲሰሙ ዘ ክራይስስa የሚል ርዕስ ያለው ቡክሌት ሰጡኝ። ቡክሌቱን እኩለ ሌሊት ድረስ ሳነብ ከቆየሁ በኋላ እውነትን እንዳገኘሁ እርግጠኛ ሆንኩ።

በባዘል የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናትb የሚል ባለ ሁለት ጥራዝ መጽሐፍ እንዲሁም ሌሎች ጽሑፎችና መጽሔቶች ሰጡኝ። ያነበብኩት ነገር በጣም ስለነካኝ በአካባቢው የሚገኘውን ቄስ ከቤተ ክርስቲያኑ አባላት ስም ዝርዝር ውስጥ እንዲሰርዘኝ ነገርኩት። በጣም ስለተናደደ እምነት የለሽ ልሆን እንደምችል አስጠነቀቀኝ። ይሁን እንጂ እሱ እንዳሰበው እምነት የለሽ አልሆንኩም። እንዲያውም በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ እውነተኛ እምነት ያዳበርኩት ያኔ ነበር።

በዚያው ሳምንት በባዘል የሚገኙ ወንድሞች ድንበር ተሻግረው ፈረንሳይ ውስጥ ለመስበክ ዕቅድ ነበራቸው። ከመካከላቸው አንዱ አብሬያቸው መሄድ ያልቻልኩት አዲስ ተሰብሳቢ ስለሆንኩ እንደሆነ በደግነት ነገረኝ። ተስፋ ሳልቆርጥ በስብከቱ ሥራ ለመካፈል ያለኝን ጽኑ ፍላጎት ነገርኩት። ከአንድ ሽማግሌ ወንድም ጋር ከተወያዩበት በኋላ በስዊዘርላንድ እንዳገለግል ክልል ተሰጠኝ። እሁድ ጠዋት 4 መጻሕፍት፣ 28 መጽሔቶችና 20 ብሮሹሮች በአገልግሎት ቦርሳዬ ይዤ በባዘል አቅራቢያ ወደምትገኘው ትንሽ መንደር በብስክሌት አቀናሁ። እዚያ ስደርስ ብዙዎቹ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን ሄደው የነበረ ቢሆንም እስከ 5 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ በቦርሳዬ ይዣቸው የነበሩትን ጽሑፎች በሙሉ አበረከትሁ።

ለወንድሞች መጠመቅ እንደምፈልግ ስነግራቸው በጉዳዩ ላይ በደንብ ካነጋገሩኝ በኋላ እውነት ምን ያህል እንደገባኝ ለማወቅ የሚያስችሉ ጥያቄዎች ጠየቁኝ። ለይሖዋና ለድርጅቱ ያላቸው ቅንዓትና ታማኝነት በጣም ነካኝ። ክረምት ስለነበረ በአንድ ሽማግሌ ወንድም ቤት በገንዳ ውስጥ ተጠመቅሁ። የተሰማኝን ደስታና ልዩ የሆነ ውስጣዊ ጥንካሬ በቃላት መግለጽ ይቸግረኛል። ይህ የሆነው በ1934 ነበር።

በይሖዋ ምሥክሮች የእርሻ ቦታ መሥራት

በ1936 ስዊዘርላንድ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች መሬት እንደገዙ ሰማሁ። በአትክልተኝነት ለመሥራት ራሴን በፈቃደኝነት አቀረብኩ። ከበርን 30 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ በምትገኘው ሽቴፊስበርግ ከተማ በይሖዋ ምሥክሮች የእርሻ ቦታ እንድሠራ ተጋበዝኩ። በምሠራበት የእርሻ ቦታ ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ ሌሎች ወንድሞችንም ለመርዳት ጥረት አደርግ ነበር። በቤቴል አገልግሎት ያሳለፍኩት ጊዜ የትብብር መንፈስ የማዳበርን አስፈላጊነት እንድገነዘብ አድርጎኛል።

በቤቴል ከቆየሁባቸው ዓመታት ውስጥ በ1936 ወንድም ራዘርፎርድ በእርሻው ጣቢያ ያደረገውን ጉብኝት መቼም አልረሳውም። ሰብሎቹ በደንብ መያዛቸውንና ቲማቲሞቹም ትልልቅ መሆናቸውን ሲመለከት ፈገግ በማለት የተሰማውን ደስታ ገለጸልን። በጣም የሚወደድ ወንድም ነበር!

በእርሻው ቦታ ለሦስት ዓመት ያህል ካገለገልኩ በኋላ አንድ ቀን ጠዋት ቁርስ ላይ ዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኘው ዋና ቢሮ የተላከ ደብዳቤ ተነበበልን። በዚህ ወቅት በእርሻው ቦታ ማገልገል ከጀመርኩ ሦስት ዓመት ሞልቶኝ ነበር። ደብዳቤው የስብከቱን ሥራ አጣዳፊነት ጎላ አድርጎ በመግለጽ በአቅኚነት ወደ ሌላ አገር ሄደን እንድናገለግል የሚጋብዝ ነበር። ያለ ምንም ማንገራገር ራሴን በፈቃደኝነት አቀረብኩ። ግንቦት 1939 በብራዚል እንዳገለግል ተመደብኩ!

በወቅቱ በእርሻ ቦታው አቅራቢያ በሚገኘው ቱን የተባለ ጉባኤ እሰበሰብ ነበር። በየሳምንቱ እሁድ በቡድን ሆነን ከቱን በብስክሌት ሁለት ሰዓት የሚፈጅ ጉዞ እያደረግን በአልፕስ አካባቢ እንሰብክ ነበር። ወደ አገልግሎት አብረውን ከሚሄዱት መካከል አንዷ ማርጋሪታ ሽታይነር ነበረች። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ሁለት ሁለት አድርጎ እንደላካቸው አሰብኩና በብራዚል እንዳገለግል መመደቤን በጨዋታ መሃል ስነግራት እሷም ተጨማሪ ሰባኪዎች ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄዶ የማገልገል ፍላጎት እንዳላት ነገረችኝ። ከዚያም ሐምሌ 31, 1939 ተጋባን።

ያልተጠበቀ አጋጣሚ

በ1939 ነሐሴ መጨረሻ ላይ ከለ ሃቭር ፈረንሳይ ተነስተን ወደ ሳንቶስ ብራዚል መጓዝ ጀመርን። በመርከቡ ውስጥ ያሉት ሁለት አልጋዎች ያሏቸው ክፍሎች በሙሉ ተይዘው ስለነበር በተለያዩ ክፍሎች ውስጥ ሆነን መጓዝ ነበረብን። በጉዞ ላይ እያለን ታላቂቱ ብሪታንያና ፈረንሳይ በጀርመን ላይ ጦርነት ማወጃቸውን የሚገልጽ ዜና ሰማን። በዚህ ጊዜ 30 የሚያህሉ ጀርመናውያን መንገደኞች የጀርመንን ብሔራዊ መዝሙር መዘመር ጀመሩ። ይህ አድራጎታቸው የመርከቡን ካፒቴን ስላናደደው አቅጣጫውን ቀይሮ መርከቧን በሞሮኮ ሳፊ ወደብ ላይ አቆማት። እኛን ጨምሮ የጀርመንን የይለፍ ወረቀት የያዘ ሰው ሁሉ ከመርከቧ በአምስት ደቂቃ ውስጥ እንዲወርድ ተደረገ።

ለአንድ ቀን ፖሊስ ጣቢያ ካቆዩን በኋላ በወላለቀች አውቶብስ ታጭቀን 140 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ማራኪሽ ከተማ ውስጥ ወዳለው እስር ቤት ተወሰድን። ከዚያ በኋላ በነበሩት ቀናት ብዙ እንግልት ደረሰብን። በጨለማ የተዋጡ ክፍሎች ውስጥ ወስደው አጎሩን። በጋራ የምንጠቀምበት መጸዳጃ ቤት ጉድጓድ ሁልጊዜ እንደሞላ ነበር። ለእያንዳንዳችን እንድንተኛበት የቆሸሸ ፍራሽ ተሰጠን። ሌሊት ሌሊት አይጦች እግራችንን ይነክሱን ነበር። ምግብ የሚሰጠን በቀን ሁለቴ ሲሆን እሱም በዛገ ጣሳ ነበር።

አንድ የጦር መኮንን በፈረንሳይ ክፍለ ጦር ውስጥ ለአምስት ዓመት ለማገልገል ከተስማማሁ እንደምለቀቅ ነገረኝ። ፈቃደኛ ሆኜ ባለመገኘቴ በሚያስፈራ ጨለማ ክፍል ውስጥ ለ24 ሰዓት ያህል ታሰርኩ። አብዛኛውን ጊዜ እየጸለይኩ ነበር ያሳለፍኩት።

የእስር ቤቱ ባለ ሥልጣናት ከስምንት ቀን በኋላ ከማርጋሪታ ጋር እንድገናኝ ፈቀዱልኝ። በጣም ከመክሳቷ ሌላ እንባዋን መቆጣጠር እስኪያቅታት ታለቅስ ስለነበር እሷን ለማበረታታት የምችለውን ሁሉ አደረግሁ። አንዳንድ ጥያቄዎችን ከተጠየቅን በኋላ በባቡር ወደ ካዛብላንካ ተዛወርን። እዚያ ስንደርስ ማርጋሪታን የለቀቋት ሲሆን እኔን ደግሞ 180 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ፖር ሊዮቴ (አሁን ኬኒትራ በመባል በምትታወቀው) ከተማ ውስጥ ወዳለው እስር ቤት ላኩኝ። የስዊዝ ቆንሲል ማርጋሪታን ወደ ስዊዘርላንድ እንድትመለስ ቢነግራትም በታማኝነት ትታኝ ላለመሄድ ወሰነች። በፖር ሊዮቴ ለሁለት ወር ታስሬ በነበረበት ጊዜ ከካዛብላንካ ድረስ በየቀኑ ምግብ ይዛ እየመጣች ትጠይቀኝ ነበር።

ከአንድ ዓመት በፊት የይሖዋ ምሥክሮች በናዚ አገዛዝ ውስጥ ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንደሌላቸው ለሕዝቡ ለማሳወቅ ክሮይትሱግ ጌይገን ዳስ ክርስተንቱም (በክርስትና ላይ የተደረገ ዘመቻ) የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ አውጥተው ነበር። እስር ቤት እያለሁ በበርን የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ለፈረንሳይ ባለ ሥልጣናት ናዚዎች አለመሆናችንን የሚገልጽ ደብዳቤና የመጽሐፉን ቅጂ ላከላቸው። ማርጋሪታም የመንግሥት ባለ ሥልጣናትን በምንም ነገር ውስጥ የሌለንበት መሆኑን ለማሳመን በመሞከር የሚደነቅ ሥራ ሠርታለች። በመጨረሻም በ1939 መገባደጃ ላይ ከሞሮኮ እንድንወጣ ተፈቀደልን።

የጀርመን ባሕር ሰርጓጅ መርከቦች በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ የሚጓዙትን መርከቦች እያጠቁ መሆኑን ያወቅነው ወደ ብራዚል ለመሄድ ከተሳፈርን በኋላ ነበር። እኛም ዋነኛ የጥቃት ዒላማ ነበርን። ምንም እንኳ የተሳፈርነው ዣማይክ በተባለች የንግድ መርከብ ቢሆንም በመርከቧ የፊትና የኋለኛ ክፍል ላይ የተገጠሙ መድፎች ነበሩ። ቀን ላይ ስንጓዝ ካፒቴኑ መርከቧን ወዲያና ወዲህ እያጥመዘመዘ በመንዳት ያለማቋረጥ የመድፍ ጥይት ይተኩስ ነበር። ሌሊት ላይ ደግሞ ጀርመናውያን እንዳያዩን ስንል መብራቱን ሁሉ አጥፍተን ነበር የምንጓዘው። ከአውሮፓ ከወጣን ከአምስት ወር በኋላ ብዙ ውጣ ውረድ አሳልፈን የካቲት 6, 1940 ሳንቶስ ብራዚል ስንደርስ በጣም ተደሰትን!

ወደ እስር መመለስ

በመጀመሪያ እንድናገለግል የተመደብነው የብራዚል ደቡባዊ ክፍለ ሀገር በሆነችው ሪዮ ግራንዲ ደ ሱል ውስጥ በምትገኘው በሞንቲኔግሩ ከተማ ነበር። የቤተ ክርስቲያን ባለ ሥልጣናት እዚያ መድረሳችን ተነግሯቸው ስለነበር ሁለት ሰዓት ያህል እንደሰበክን ፖሊሶች መጥተው ያዙን። የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር የያዙ የሸክላ ካሴቶቻችንንና ማጫወቻውን እንዲሁም ጽሑፎቻችንንና ሞሮኮ በነበርንበት ጊዜ የገዛነውን ከግመል ቆዳ የተሠራ የአገልግሎት ቦርሳ ሳይቀር ወሰዱብን። አንድ ቄስና ጀርመንኛ ቋንቋ መናገር የሚችል ዲያቆን ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ እየጠበቁን ነበር። የፖሊስ አዛዡ ከእኛ የወሰዱትን የወንድም ራዘርፎርድ ንግግር ከፈተውና አንድ ላይ አዳመጡት። ወንድም ራዘርፎርድ የሰጠው ንግግር ግልጽና ቀጥተኛ የነበረ ሲሆን ስለ ቫቲካን መናገር ሲጀምር ቄሱ በጣም ተናድደው ክፍሉን ጥለው ወጡ።

የሳንታ ማሪያ ጳጳስ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት የሪዮ ግራንዲ ደ ሱል ማዕከላዊ ከተማ ወደሆነችው ፖርቶ አሌግራ እንድንዛወር ተደረገ። ማርጋሪታ ወዲያው ተለቀቀችና የስዊስ ቆንሲል እንዲረዳት ጠየቀች። ቆንሲሉ ወደ ስዊዘርላንድ ብትመለስ እንደሚሻላት ቢነግራትም በድጋሚ እኔን ትታኝ የማትሄድ መሆኑን ገለጸች። ማርጋሪታ በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ በታማኝነት ከጎኔ ቆማለች። ከሠላሳ ቀናት በኋላ አንዳንድ ጥያቄዎች ጠየቁኝና ለቀቁኝ። ፖሊሱ በአሥር ቀናት ውስጥ ትወጣላችሁ ወይስ “የሚመጣባችሁን ሁሉ መቀበል ይሻላችኋል” ሲል ምርጫ አቀረበልን። ብሩክሊን ከሚገኘው ዋናው ቢሮ በቀረበልን ሐሳብ መሠረት ወደ ሪዮ ዲ ጀኔሮ ከተማ ሄድን።

“እባክዎ ይህን ካርድ ያንብቡት”

በብራዚል ያደረግነው የስብከት እንቅስቃሴ ከጅምሩ ተስፋ አስቆራጭ ቢመስልም በሕይወት መትረፋችን፣ የአገልግሎት ቦርሳችን አሁንም በጽሑፎች የተሞላ መሆኑና በመላው ሪዮ ዲ ጀኔሮ መስበክ የምንችልበት አጋጣሚ ማግኘታችን እጅግ አስደስቶናል። ይሁን እንጂ የፖርቱጋል ቋንቋ መናገር ሳንችል እንዴት አድርገን ነው የምንሰብከው? መጀመሪያ ላይ የተማርናቸውን ጥቂት የፖርቱጋል ቃላት በመጠቀም በአገልግሎት የምናገኛቸውን ሰዎች “ፖር ፋቮር ሌ ኤስታ ካርታው” (“እባክዎ ይህን ካርድ ያንብቡት”) እንላቸውና የምሥክርነት መስጫ ካርድ እናሳያቸዋለን። በካርዱ መጠቀማችን በስብከቱ ሥራ ስኬታማ እንድንሆን አስችሎናል። በአንድ ወር ውስጥ ከ1,000 በላይ መጻሕፍት አበረከትን። መጽሐፎቹን ከወሰዱት መካከል ብዙዎቹ እውነትን ተቀበሉ። እውነቱን ለመናገር ጽሑፎቻችን እኛ ልንሰጥ ከምንችለው በላይ ውጤታማ ምሥክርነት ሰጥተዋል። ይህ ደግሞ ጽሑፎቻችን ፍላጎት ባሳዩ ሰዎች እጅ እንዲገቡ ማድረግ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ እንድገነዘብ አድርጎኛል።

በዚያ ወቅት ሪዮ ዲ ጀኔሮ የብራዚል ዋና ከተማ የነበረች ሲሆን የምንናገረው መልእክት በተለይ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ጥሩ ተሰሚነት ነበረው። ለገንዘብ ሚንስትሩና ለመከላከያ ሚንስትሩ በግል የመመሥከር መብት አግኝቻለሁ። እነዚህ አጋጣሚዎች የይሖዋ መንፈስ የሚሠራ መሆኑን የሚያሳዩ ግልጽ ማስረጃዎች ናቸው።

አንድ ጊዜ በሪዮ ዲ ጀኔሮ ከተማ መሃል በሚገኝ አንድ አደባባይ ስሰብክ ቆየሁና እዚያው አካባቢ ወዳለ አንድ ፍርድ ቤት ገባሁ። የገባሁበት ክፍል ውስጥ ጥቁር ልብስ የለበሱ ብዙ ሰዎች ነበሩ። የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ያሉ ይመስል ነበር። ከመካከላቸው አንድ ትልቅ ቦታ ያላቸው የሚመስሉ ሰው አየሁና ወደሳቸው ቀርቤ የምሥክርነት መስጫ ካርዱን አሳየኋቸው። የነበርኩት የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ሳይሆን ችሎት መካከል ነበር። ያነጋገርኩትም ዳኛውን ነበር። ዳኛው እየሳቁ ዘበኞቹን ምንም እንዳያደርጉኝ ነገሯቸው። ልጆችc የተባለውን መጽሐፍ ደስ እያላቸው አስተዋጽኦ ከፍለው ወሰዱ። እየወጣሁ ሳለ ከዘበኞቹ አንዱ (ከሠራተኛ በቀር መግባት ክልክል ነው) የሚል ትርጉም ያለውን ፕሮአቢዳ ኣ ኤንትራዳ ደ ፒሶአስ ኤስትራንያስ የሚል በጉልህ የተጻፈ ጽሑፍ አሳየኝ።

ሌላው ውጤታማ ሆኖ ያገኘነው የስብከት ቦታ የባሕር ወደብ ነው። አንድ ጊዜ በወደቡ አካባቢ አንድ መርከበኛ አገኘሁና ጽሑፎች አበረከትኩለት። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ትልቅ ስብሰባ ላይ አገኘነው። ቤተሰቡ በሙሉ እውነትን ከመቀበሉም ሌላ እሱ ራሱ ጥሩ እድገት እያደረገ ነበር። ይህን ማወቃችን በጣም አስደስቶናል።

ሆኖም ምንም ችግር አላጋጠመንም ማለት አይደለም። ለስድስት ወር የተሰጠን ቪዛ ቀኑ ስላለቀ ከአገሪቱ ያስወጡናል የሚል ስጋት አደረብን። ያለንበትን ሁኔታ ለዋናው ቢሮ ስንጽፍ ወንድም ራዘርፎርድ በአገልግሎታችን እንድንጸና የሚያበረታታና በሥራችን ለመቀጠል እንድንችል ምን ማድረግ እንዳለብን የሚገልጽ ደብዳቤ ላከልን። ብራዚል መቆየት እንፈልግ ስለነበር በጠበቃችን እርዳታ በ1945 ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ አገኘን።

ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ሥራ

ይህ ከመሆኑ በፊት ግን በ1941 ዮናታንን፣ በ1943 ሩትን፣ በ1945 ደግሞ ኤስቴርን ወልደን ስለነበር እየጨመረ የሚሄደውን የቤተሰባችንን ፍላጎት ለማሟላት ሰብዓዊ ሥራ መሥራት ነበረብኝ። ማርጋሪታ ሦስተኛ ልጃችንን እስክንወልድ ድረስ በሙሉ ጊዜ የስብከቱ ሥራ ቀጥላለች።

ከልጅነታቸው ጀምሮ በቤተሰብ ሆነን በከተማው ውስጥ በሚገኙ አደባባዮች፣ በባቡር ጣቢያ፣ በመንገድ ላይና በንግድ ቦታዎች አካባቢ እንሰብክ ነበር። ዘወትር ቅዳሜ ማታ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶችን በቤተሰብ አንድ ላይ ሆነን እናበረክት የነበረ ሲሆን በተለይ እነዚህ ጊዜያት አስደሳች ነበሩ።

ቤት ውስጥ ሁሉም ልጆች በየቀኑ የሚሠሩት የሥራ ድርሻ ነበራቸው። ወጥ ቤቱንና ምድጃውን ማጽዳት የዮናታን ሥራ ሲሆን ሴት ልጆቻችን ደግሞ ማቀዝቀዣውን ያጸዱ፣ ግቢውን ይጠርጉና ጫማዎቻችንን ይወለውሉ ነበር። እንዲህ ዓይነቱን ሥልጠና ማግኘታቸው የተደራጁ እንዲሆኑና በራስ ተነሳሽነት የመሥራትን ልማድ እንዲያዳብሩ ረድቷቸዋል። ዛሬ ልጆቻችን ቤታቸውንና ንብረታቸውን በሚገባ የሚይዙ ትጉ ሠራተኞች ናቸው። ይህ ደግሞ ማርጋሪታንና እኔን በጣም ያስደስተናል።

በስብሰባዎችም ላይ ቢሆን ልጆቻችን ሥርዓታማ እንዲሆኑ እናሠለጥናቸው ነበር። ከስብሰባ በፊት መጸዳጃ ቤት እንዲሄዱና ውኃ እንዲጠጡ እናደርጋለን። ስብሰባ በሚካሄድበት ወቅት ሩትን በእኔና በማርጋሪታ መሃል፣ ዮናታንን ከእኔ በስተግራ ኤስቴርን ደግሞ ከማርጋሪታ በስተቀኝ እናስቀምጣቸው ነበር። እንዲህ ማድረጋችን ከልጅነታቸው ጀምሮ ሐሳባቸውን አሰባስበው መንፈሳዊ ምግብ እንዲመገቡ ረድቷቸዋል።

ይሖዋ ጥረታችንን ባርኮልናል። ሦስቱም ልጆቻችን ይሖዋን በታማኝነት በማገልገል በስብከቱ ሥራ በደስታ መካፈላቸውን ቀጥለዋል። በአሁኑ ጊዜ ዮናታን በሪዮ ዲ ጀኔሮ ከተማ በኖቮ ሜየር ጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ ያገለግላል።

በ1970 ልጆቻችን በሙሉ አግብተው ስለሄዱ ማርጋሪታና እኔ ተጨማሪ አገልጋዮች ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደን ለማገልገል ወሰንን። መጀመሪያ የሄድነው በሚና ዤራይስ ክፍለ ሃገር ወደምትገኘው የፖሱስ ዲ ካልዳስ ከተማ ነበር። በወቅቱ በከተማው 19 የመንግሥቱ አስፋፊዎችን ብቻ ያቀፈ አነስተኛ ቡድን ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰበሰቡበትን ቦታ ሳየው በጣም ነበር ያዘንኩት። የሚሰበሰቡት መስኮት በሌለውና ከፍተኛ እድሳት በሚያስፈልገው ምድር ቤት ውስጥ ነበር። ወዲያውኑ የተሻለ የመንግሥት አዳራሽ መፈለግ ጀመርን። ብዙም ሳይቆይ ጥሩ ቦታ ላይ የተሠራ ቆንጆ ሕንፃ አገኘን። ይህም ጥሩ ውጤት ያስገኘ ሲሆን በአራት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ የአስፋፊዎቹ ቁጥር ወደ 155 ከፍ አለ። በ1989 ሪዮ ዲ ጀኔሮ ውስጥ ወደምትገኘው አራሩአማ ከተማ ሄደን ዘጠኝ ዓመት ያህል ቆየን። በዚህ ቆይታችን ሁለት አዳዲስ ጉባኤዎች ሲመሠረቱ ማየት ችለናል።

በተመደብንበት ቦታ በመጽናታችን ተባርከናል

በ1998 የጤና ችግር ስላጋጠመን እንዲሁም ልጆቻችንን በቅርብ ማግኘት ስለፈለግን ሪዮ ዲ ጀኔሮ ውስጥ ወደምትገኘው ሳኦ ጎንሳሉ ከተማ ተዛወርን። እኔ አሁንም የጉባኤ ሽማግሌ ሆኜ በማገልገል ላይ ስሆን በስብከቱ ሥራ አዘውትረን ለመካፈል የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። ማርጋሪታ በአቅራቢያችን ባለው የገበያ አዳራሽ የምትሰብክ ከመሆኑም በላይ ጉባኤያችን በቤታችን አቅራቢያ የሚገኝ የአገልግሎት ክልል ስለሰጠን ጤናችን በሚፈቅድልን መጠን መስበክ እንድንችል ረድቶናል።

ማርጋሪታና እኔ ራሳችንን ወስነን ይሖዋን ማገልገል ከጀመርን ከ60 ዓመት በላይ ሆኖናል። “ግዛትም ቢሆን፣ ያለውም ቢሆን፣ የሚመጣውም ቢሆን፣ ኃይላትም ቢሆኑ፣ ከፍታም ቢሆን፣ ዝቅታም ቢሆን፣ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን” እንደማይችል በራሳችን ሕይወት ላይ ከደረሰው ሁኔታ አይተናል። (ሮሜ 8:​38, 39) ለኑሮ ፍጹም ተስማሚ በምትሆን ምድር ላይ ውብ በሆኑ የአምላክ ፍጥረታት ተከብበው የመኖር አስደናቂ የዘላለም ሕይወት ተስፋ የሚጠብቃቸው “ሌሎች በጎች” ሲሰበሰቡ ማየት በጣም ያስደስታል። (ዮሐንስ 10:​16) በ1940 ሪዮ ዲ ጀኔሮ ከተማ ስንገባ 28 አስፋፊዎች ያሉት አንድ ጉባኤ ብቻ ነበር። ዛሬ 250 የሚያክሉ ጉባኤዎችና 20, 000 የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይገኛሉ።

አውሮፓ ወደሚገኙት ቤተሰቦቻችን መመለስ የምንችልባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ። ነገር ግን ይሖዋ የመደበን ብራዚል ውስጥ እንድናገለግል ስለሆነ እዚህ በመቆየታችን በጣም ደስተኞች ነን!

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ፤ አሁን ግን ኅትመቱ ቆሟል።

b በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ፤ አሁን ግን ኅትመቱ ቆሟል።

c በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ፤ አሁን ግን ኅትመቱ ቆሟል።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1930ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ስዊዘርላንድ ሽቴፊስበርግ ውስጥ በይሖዋ ምሥክሮች እርሻ የተነሳነው ፎቶ (በስተግራ ጥግ ላይ ያለሁት እኔ ነኝ )

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1939 ከመጋባታችን ትንሽ ቀደም ብሎ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ካዛብላንካ በ1940ዎቹ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቤተሰብ ሆነን ስንሰብክ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዛሬም በአገልግሎት አዘውትረን እንካፈላለን

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ