ለመንግሥት አዳራሻችሁ አክብሮት ታሳያላችሁ?
1 “ወንድሞች ተስማምተው በአንድነት ሲኖሩ፣ እንዴት መልካም ነው! ምንኛስ ደስ ያሰኛል!” (መዝ. 133:1) በመንግሥት አዳራሾቻችን ውስጥ የምናደርጋቸው ስብሰባዎች ከወንድሞቻችን ጋር አንድነት እንዲኖረን የሚያስችል አጋጣሚ ይከፍቱልናል፤ በመሆኑም እርስ በርስ በመበረታታት አንዳችን ሌላውን ለፍቅርና ለመልካም ሥራ ማነቃቃት እንችላለን።—ዕብ. 10:24, 25
2 የመንግሥት አዳራሽ በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ግምት የምንሰጠውን ነገር ለማከናወን የምንጠቀምበት ቦታ እንደመሆኑ መጠን ለመንግሥት አዳራሻችን በእርግጥ አክብሮት እንዳለን እናሳያለን? የመንግሥት አዳራሽ ለአካባቢው የእውነተኛ አምልኮ ስፍራ ሆኖ ያገለግላል። በመሆኑም በታላቅ አክብሮት ልንይዘው ይገባል። የመንግሥት አዳራሻችን ምንጊዜም ንጹሕና ጥሩ ይዞታ ያለው እንዲሆን ሁላችንም የበኩላችንን ድርሻ ማበርከት እንዳለብን ሊሰማን ይገባል። አንዳንድ ጊዜ የስምሪት ቡድናችን አዳራሹን እንዲያጸዳ ይመደባል። በዚህ ጊዜ አቅማችን እስከፈቀደ ድረስ በሥራው ለመካፈል መጣር ይኖርብናል፤ እንዲህ በማድረግ መሰብሰቢያ ቦታችን ንጹሕና ማራኪ ሆኖ እንዲታይ እንደምንፈልግ ማሳየት እንችላለን።
3 የጽዳት ተረኞች በሆንበት ወቅትም ሆነ በሌሎች ጊዜያት ለመንግሥት አዳራሹ ንጽሕና ትኩረት መስጠት እንችላለን። እንዴት? የአዳራሹን ወለል ላለማቆሸሽ ጫማችንን እንደመጥረግ ያሉ ቀለል ያሉ እርምጃዎችን መውሰድ እንችላለን። በተለይ በዝናብ ወቅቶች እንዲህ ማድረጋችን የተገባ ነው። መጸዳጃ ቤት ከተጠቀምን በኋላ የእጅ መታጠቢያውን ለሚቀጥለው ሰው ንጹሕ አድርገን መሄድ ይኖርብናል። በጽሑፍና በመጽሔት ክፍል የሚሠሩ ወንድሞች ደግሞ ባዶ ካርቶኖችን ቶሎ ቶሎ በማስወገድ አሳቢነታቸውን ማሳየት ይችላሉ። ማንኛውም ቆሻሻ ለዚያው ዓላማ በተዘጋጀው ቅርጫት ውስጥ መጣል ይኖርበታል። ወረቀት ወይም ሌላ ቆሻሻ መሬት ላይ ተጥሎ ካየን ሌሎች እንዲያነሱት ከመጠበቅ ይልቅ እኛ ራሳችን ልናነሳው ይገባል። የጥር 1989 የመንግሥት አገልግሎታችን የማስታወቂያ ሰሌዳዎችን በንጽሕና መያዝ የሚቻልበትን መንገድ አስመልክቶ አንዳንድ ምክሮችን ይሰጣል። እነዚህን ምክሮች በሥራ ላይ ለማዋል የሌሎች ትብብር አስፈላጊ ነው።—km-E 1/89 ገጽ 7
4 በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝም ይህንኑ መሠረታዊ ሥርዓት መከተል ይኖርብናል። ትልልቅ ስብሰባዎችን የምናደርግበት ቦታ ንብረትነቱ የእኛ ሆነም አልሆነ ቦታው የንጹሕ አምልኮ ማዕከል ሆኖ ስለሚያገለግል በአክብሮት ልንይዘው ይገባል። ከስብሰባው ስንወጣ በተቀመጥንበት አካባቢ ምንም ቆሻሻ እንዳልተውን ሁልጊዜ ማረጋገጣችን አስፈላጊ ነው። የመተጋገዝ መንፈስ ማዳበር የሚገባን ከመሆኑም ሌላ ለጽዳት የተመደቡት ወንድሞች እኛ የጣልነውን ቆሻሻ ማንሳት እንዳለባቸው ሊሰማን አይገባም።
5 አዳራሹን በጋራ መጠቀም፦ የመሬትና የግንባታ ወጪ በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ አብዛኞቹ የመንግሥት አዳራሾች ከአንድ በላይ ጉባኤዎችን ያስተናግዳሉ። እያንዳንዱ ጉባኤ የመንግሥት አዳራሹ የይሖዋ እንደሆነና እሱን ለማምለክ የሚያገለግል ቦታ እንደሆነ በመገንዘብ ለአዳራሹ ንጽሕና ትኩረት መስጠት አለበት። በመሆኑም ለመንግሥት አዳራሹ አክብሮት ለማሳየት የሚያነሳሳን ለይሖዋ ያለን ፍቅር ብቻ ሳይሆን አዳራሹን በሚጠቀሙ ሌሎች ጉባኤዎች ውስጥ ላሉት ወንድሞችም ያለን ፍቅር ነው።
6 በጥቅሉ ሲታይ የመንግሥት አዳራሽ የሚጸዳው በሳምንት አንዴ ነው። ከአንድ በላይ ጉባኤዎች በአዳራሹ የሚጠቀሙ ከሆነ ቀጣዩ ጉባኤ ንጹሕ መሰብሰቢያ ቦታ ማግኘት እንዲችል እያንዳንዱ ስብሰባ ካለቀ በኋላ ማጽዳቱ በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ደግሞ እሁድ እሁድ ጉባኤዎች ተፈራርቀው በሚሰበሰቡበት ጊዜም ይሠራል። ጊዜ በፈቀደ መጠን ለቀጣዩ ጉባኤ መጠነኛ ጽዳት ቢከናወን ጥሩ ይሆናል። በአንድ ቀን በርካታ ጉባኤዎች ስብሰባ የሚያከናውኑ ከሆነና ማናቸውም ቢሆኑ አዳራሹን የማያጸዱ ከሆነ መጨረሻ ላይ በጣም መቆሸሹ አይቀርም።
7 መንፈሳዊ ከሆኑ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ “በአስተሳሰብም ሆነ በዓላማ ፍጹም አንድነት” እንዳለን ሁሉ ለመንግሥት አዳራሾቻችን አክብሮት በማሳየት ረገድም አንድነት ሊኖረን ይገባል።—1 ቆሮ. 1:10