በአገልግሎትህ በሙሉ ነፍስህ የምትሠራ ሁን
1 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደመሆናችን መጠን ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን ምሥራች እንድንሰብክና ሰዎችን የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ ታዘናል። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20) በዚህ ምድር ላይ በአጣዳፊነቱም ሆነ በአስፈላጊነቱ ከዚህ ሥራ ጋር የሚወዳደር ምንም ዓይነት ሥራ የለም። ይህ ሥራ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የሚነካ ነው። ሥራው የቻልነውን ያህል ልንጥርለት የሚገባው ነው። “ምንም ነገር ብታደርጉ ለይሖዋ እንደምታደርጉት ያህል በሙሉ ነፍስ አድርጉት” የሚለው የሐዋርያው ጳውሎስ ምክር እዚህ ላይ በሚገባ ይሠራል። (ቆላ. 3:23) “በሙሉ ነፍስ” የሚለው ቃል “በግለት ወይም አንድ ዓላማ ይዞ መሥራት” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። በአገልግሎትህ በሙሉ ነፍስህ የምትሠራ ነህን?
2 በሙሉ ነፍሳችን መሥራት ምን ይጠይቅብናል? ይሖዋ በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን አገልግሎት አሥራት ወይም አንድ አሥረኛ ሲል ይጠራው ነበር። (ሚል. 3:10) አንድ አሥረኛ የሚለው አነጋገር የተወሰነ መጠን ከመመደብ ይልቅ ለእርሱ ያለንን ፍቅርና ራሳችንን ለእርሱ የወሰንን መሆናችንን እንደምናስታውስ የምናሳይበት መግለጫ ለሆነው ለይሖዋ ለምናቀርበው አገልግሎት የምናውለውን ጊዜና ጉልበት ይወክላል። (መግ 92 12/1 ገጽ 15) አገልግሎታችን በምን ያህል ጥልቀት ለይሖዋ ያደርን መሆናችንንና ለእርሱ ያለንን ፍቅር ጥልቀት ማንጸባረቅ ይኖርበታል። በሙሉ ነፍሱ የሚሠራ ሰው ጤንነቱና ያለበት ሁኔታ እስከሚፈቅድለት ድረስ የቻለውን ያህል ይሖዋን ለማገልገል እንደተገፋፋ ያህል ይሰማዋል።
3 ጳውሎስ ተስፋቸውን ለማግኘት ሲሉ ‘በብርቱ የሚደክሙትን’ ክርስቲያኖችን አድንቋቸዋል። (1 ጢሞ. 4:10) በአጸፋው ‘ባለ ጠጋ የሚያደርገውን’ የይሖዋ በረከት ያገኛሉ። (ምሳሌ 10:22) በተቃራኒው ደግሞ ጉልበታቸውን የሚቆጥቡ ወይም ቅር እያላቸው የሚሠሩ ሰዎች ከመስጠት የሚገኘውን ደስታ ያጣሉ። (ሥራ 20:35) ምርጥ ምርጡን ለይሖዋ ከመስጠት ችላ ካልን ለእርሱ ልንሰጠው ከሚገባን “አሥራት” ላይ እንደ መስረቅ የሚቆጠር ነው። — ሚል. 3:8
4 ምርጣችንን መስጠት፦ በመስክ አገልግሎት ከተካፈልን በኋላ ሪፖርታችንን ስንመልስ የምንሰጠው ሪፖርት ትክክል ነውን? አገልግሎታችን የተባለው መጽሐፍ በገጽ 55 (በእንግሊዝኛው በገጽ 104) ላይ እንዲህ ይላል:- “የመስክ አገልግሎትህን ሰዓት የምትቆጥረው በእያንዳንዱ የምስክርነት ክፍለ ጊዜ ውስጥ የምስክርነቱን ሥራ ከጀመርክበት ጊዜ አንስቶ የመጨረሻውን ሰው አነጋግረህ እስከጨረስክበት ድረስ ያለውን ጊዜ ነው። በመስክ አገልግሎት ክፍለ ጊዜ ውስጥ አቋርጠህ ሻይ ለመጠጣት ወይም ምግብ ለመብላት የምታጠፋውን ጊዜ ትቀንሳለህ።” በመስክ አገልግሎት ላይ የምናሳልፈውን ጊዜ በተሻለ መንገድ እንድንጠቀምበት ጥሩ ዕቅድ ማውጣትና ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል።
5 ምርጡን መስጠት ማለት በአገልግሎት ላይ በምንሆንበት ጊዜ የምንችለውን ያህል መሥራት ማለት ነው። በሙሉ ነፍሱ የሚሠራ ሰው ከበር ወደ በር በመሄድ በሚደረገው የምስክርነት ሥራ ከመካፈል ይልቅ አልፎ አልፎ ሁኔታዎች ሲመቻቹለት ብቻ መደበኛ ባልሆነ መንገድ በሚያደርገው ምስክርነት ሆነ ብሎ የስብከት ሥራውን አይወስነውም። በሙሉ ነፍሱ የሚሠራ አንድ ያልተጠመቀ ወጣት አስፋፊ ከበር ወደ በር ለመሄድ ወይም መልዕክቱን በማቅረቡ ሥራ ለመካፈል ምንም ያህል ፍላጎት ስለሌለው ለመስበክ የሚወጣው በወላጆቹ ጉትጎታ ብቻ አይሆንም።
6 ጳውሎስ ዳተኞች በመሆን ፈንታ ትጉዎች ሆነን እንድንቀጥል አጥብቆ አሳስቦናል። (ዕብ. 6:11, 12) በግላችን ያደረግነውን አገልግሎት መለስ ብለን በምንመረምርበት ጊዜ ምንም የምናፍርበት ምክንያት ከሌለን እንዴት የሚያስደስት ይሆናል! ይህ ሊሆን የሚችለው በሙሉ ነፍሳችን እንሠራ ከነበረ ነው። (2 ጢሞ. 2:15) እኛ በግላችን የረዳናቸው ሰዎች ከታላቁ መከራ ተራፊዎች መካከል ሆነው ስናያቸው ደስታችን እጥፍ ድርብ ይሆናል። ይሖዋ በሙሉ ነፍሳቸው ለሚያገለግሉት ሰዎች ዋጋቸውን አብዝቶ እንደሚከፍላቸው የተረጋገጠ ነው።