የሚያበረታቱ ታሪኮችንና ተሞክሮዎቸን የያዘው የዓመት መጽሐፍ
1 ስለ ይሖዋ አስደናቂ ሥራዎች የሚቀርቡት ሪፖርቶችና ተሞክሮዎች የአምላክ አገልጋዮችን መንፈስ ምን ጊዜም ሲያነቃቁ ኖረዋል። (ኢዮብ 38:4, 7፤ ምሳሌ 25:25፤ ሉቃስ 7:22፤ ሥራ 15:31) የይሖዋ ምስክሮች የዓመት መጽሐፍ ማበረታቻ የሞላበት የሆነው ለዚህ ነው።
2 እያንዳንዱ የዓመት መጽሐፍ በዓለም ዙሪያ የይሖዋ ምስክሮች ያደረጓቸውን እንቅስቃሴዎችና ያከናወኗቸውን ሥራዎች በተመለከተ የሚያንጹ ሪፖርቶችን ያቀርባል። ሕዝቡን እንደመራ፣ እንደጠበቀና እንደባረከ የሚያረጋግጡ እምነትን የሚያጠነክሩት ተሞክሮዎች አጉልተው ያሳያሉ። የዓመት መጽሐፉ በሁሉም አህጉራትና ደሴቶች ለሚገኙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማዳረስ ሲሉ ቤተሰባቸውን፣ ጓደኞቻቸውንና የትውልድ አገራቸውን ትተው ስለሄዱት ቆራጥ ወንዶችና ሴቶች ይገልጻል።
3 የዓመት መጽሐፉ አንባቢዎቹ ለአምላክ የሚያቀርቡትን አገልግሎት ከፍ እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል። አንዲት አንባቢ እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “በፍጥነት አንብቤ መጨረስ አልቻልኩም። እስካሁን ያነበብኩት በጣም የሚያበረታታ ነው። ሌሎች ብዙ ችግር እያለባቸው እየሠሩ ያሉትን ስመለከት ምሥራቹን በመስበክ በኩል ብዙ ማድረግ እንዳለብኝ እንዲሰማኝ አድርጎኛል።”
4 ከ1927 ጀምሮ የይሖዋ ምስክሮች የዓመት መጽሐፍ መንፈስን የሚያነቃቁ እውነተኛ ሪፖርቶችንና ተሞክሮዎችን የሚያቀርብ መዝገብ ሆኖ ቆይቷል። ልዩ ከሆነው ከዚህ የማበረታቻ ምንጭ ሙሉ በሙሉ እየተጠቀምክ ነውን? ጥቅሙን ሙሉ በሙሉ ለማግኘት የዓመት መጽሐፉን መጀመሪያ እንዳገኘኸው አንብበው። ከዚያም አንተና ቤተሰብህ አስፈላጊውን ማበረታቻ እንድታገኙ ከመጽሐፉ የተወሰነውን ክፍል በዓመቱ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ከልሱ።