“መለኮታዊ ትምህርት” ብሔራት አቀፍ ስብሰባ በናይሮቢና በአዲስ አበባ
1 በምሥራቅ አፍሪካ ለሚገኙ የይሖዋ ሕዝቦች በሙሉ አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፈት ያለጥርጥር በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን። የ1993/94 “መለኮታዊ ትምህርት” ብሔራት አቀፍ ስብሰባ በናይሮቢ እንዲሁም በአዲስ አበባ የሚደረገው ልዩ የወረዳ ስብሰባችን ሊደረጉ የቀራቸው ጊዜ ጥቂት ሳምንታት ያህል ብቻ ነው። እንዴት ያለ ልዩ በረከት ይጠብቀናል!
ከውጭ አገር የሚመጡ የስብሰባው ተካፋዮች
2 ባለፈው ዓመት በማስታወቂያ እንደተነገረው ከ25 የሚበልጡ የተለያዩ ቅርንጫፍ ቢሮዎች በምናደርጋቸው ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎቻችን የሚገኙ ልዑካንን እንደሚልኩ እንጠባበቃለን። ከጃፓን፣ ከአውስትራሊያ፣ ከኒው ዚላንድ፣ ከናይጄርያ፣ ከአውሮፓ፣ በሕንድ ውቅያኖስ ከሚገኙ ደሴቶችና ከዩናይትድ ስቴትስ በድምሩ ከ5,000 በላይ የሚሆኑ ወንድሞች በናይሮቢ በሚደረገው ስብሰባ እንደሚገኙ ሲጠበቅ በአዲስ አበባ ደግሞ ከሰሜን አሜሪካና ከአውሮፓ የሚመጡ ወንድሞች እንደሚኖሩ ይታመናል። ከሩቅ የመጡና የኛው ዓይነት የተወደደ እምነት ካላቸው ብዙ ወንድሞች ጋር መሆን በጣም ደስ ይላል። የሚያበረታቱ እውነተኛ ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ የሚያስችል እንዴት ያለ ትልቅ አጋጣሚ ነው!—ሮሜ 1:12
3 ከተለያዩ አገሮች ከሚመጡት ተሰብሳቢዎች በተጨማሪ አምስት የአስተዳደር አካል አባላት በወረዳ ስብሰባዎቻችን ላይ እንዲገኙ መመደባቸውን ስናስታውቃችሁ ታላቅ ደስታ ይሰማናል። ከእነዚህ ወንድሞች መካከል ሁለቱ ወንድም ጄ ኢ ባርና ወንድም ሲ ደብልዩ ባርበር እንዲሁም ሚስቶቻቸው ወደ ምሥራቅ አፍሪካ ሲመጡ የመጀመሪያቸው ይሆናል። ወንድም ኤል ኤ ስዊንግል፣ ወንድም ደብልዩ ኤል ባሪና ወንድም ዳንኤል ሲድሊክ እንዲሁም ሚስቶቻቸው በክልላችን ሲገኙ የመጀመሪያቸው አይደለም። ወንድም ደብልዩ ኤል ባሪ እና ወንድም ዳንኤል ሲድሊክ በአዲስ አበባ ከእኛ ጋር እንዲሆኑ ተመድበዋል።
4 ከዋናው መሥሪያ ቤት ከብሩክሊንና ከሌሎች ቅርንጫፍ ቢሮዎች የሚመጡ ወንድሞች በወረዳ በስብሰባዎቻችን እንዲገኙና በስብሰባው ፕሮግራሞች እንደሚሳተፉ ማወቃችን አስደስቶናል። በእውነትም ይህ ልዩ ፕሮግራም ይሆናል።
ስለ ፕሮግራሙ የተሰጡ መረጃዎች
5 በአዲስ አበባ የሚደረገው ልዩ የወረዳ ስብሰባ ፕሮግራም የሚጀምረው ሐሙስ ጠዋት እንደሆነ አስታውሱ። የመክፈቻው መዝሙር ከጠዋቱ በ2:50 ይጀምራል። ሙዚቃው የሚጀምረው በ2:45 ይሆናል። ስለዚህ ሁሉም ከቀኑ ፕርግራም ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም እንዲችሉ ሐሙስ ጠዋት ቀደም ብለው ለመድረስ እንደሚፈልጉ አያጠራጥርም።
ማሳሰቢያዎች
6 በታኅሣሥ ወር ወደ ሌላ ቦታ የሚጓዙ አስፋፊዎች የመስክ አገልግሎት ሪፖርታቸውን ለጉባኤያቸው መመለስ አለባቸው።
7 በክልላችን ለሚካሄዱት የወረዳ ስብሰባዎች ሁሉ የይሖዋን በረከት እንድናገኝ እንጸልያለን። በናይሮቢ የሚደረጉትን ሁለት ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎችና በአዲስ አበባ የሚደረገውን ልዩ የወረዳ ስብሰባ በጉጉት እንጠብቃለን።