ሌሎች ሰዎች ፈጣሪያችንን እንዲያከብሩት መርዳት
1 መዝሙራዊው “አቤቱ፣ [ይሖዋ አዓት] . . . የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነውና” ብሎ ሲናገር እንደተሰማው ዓይነት ስሜት ይሰማናልን? (መዝ. 36:5, 9) እኛም በተራችን ሌሎች ሰዎች ለፈጣሪያችን ለይሖዋ አድናቆትና ክብር እንዲሰጡት ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው? ሕይወት እንዴት ተገኘ? — በዝግመተ ለውጥ ወይስ በፍጥረት? የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ በማበርከት ነው። ይህ መጽሐፍ የአምላክ ሕልውና እርግጠኛ መሆኑን የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ የያዘና ዝግመተ ለውጥ ሐሰት የሆነበትን ምክንያት የሚያቀረብ ልዩ መጽሐፍ ነው። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል እንደሆነ ያለንን እምነት ያዳብርልናል። ይሖዋ አምላክን የሚያስከብረው ዝግመተ ለውጥ ሳይሆን ፍጥረት መሆኑን ሁሉም ሰዎች እንዲያውቁ እንፈልጋለን።
2 እዚህ ላይ ቀላልና ቀጥተኛ የሆነ መግቢያ ቀርቧል።
ለባለቤቱ ሰላምታ ካቀረብክ በኋላ በገጽ 6 ላይ ያለውን ሥዕል አሳየውና እንዲህ ብለህ ጠይቀው፦
◼ “እዚህች ምድር ላይ ሕይወት የጀመረው እንዴት ነው? አንዳንዶች ይህ ሁሉ የመጣው በአጋጣሚ ነው ይላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ሕይወት እንዲገኝ ያደረገ አምላክ ነው ይላል። እርስዎስ ምን ይመስልዎታል? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ይህ መጽሐፍ ከመጽሐፍ ቅዱስና ከሳይንሳዊ እውነታዎች ጋር ሙሉ ስምምነት ያላቸው መልሶችን ይሰጣል። ሁሉንም ማስረጃዎች ተመልክተው ራስዎ መወሰን ይችሉ ዘንድ ይህ መጽሐፍ ቢኖርዎት ደስ ይለኛል።”
3 ራስህን ካስተዋወቅህ በኋላ እንዲህ ልትል ትችላለህ፦
◼ “በዚህ ዘመናዊ በሆነ ሳይንሳዊ ዓለም ውስጥ የተፈጠርነው በአምላክ ነው ብሎ ማመን ትክክል ይመስልዎታል? ወይስ የተፈጠርነው በአጋጣሚ ነው ብለው ያምናሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በተመለከተ የሚሰጠውን ማስረጃ እስቲ ይመልከቱ። [ዕብራውያን 3:4ን አንብብ።] እያንዳንዱ ቤት ሠሪ አለው ቢባል አይስማሙን? ታዲያ አጽናፈ ዓለሙ ራሱ በራሱ ሊገኝ ይችላልን?” ፍጥረት በተባለው መጽሐፍ በገጽ 114 ላይ ያለውን ሥዕል አሳየውና በገጽ 115 አንቀጽ 2 ላይ በተገለጸው ሐሳብ ላይ እንዲያተኩር አድርግ። ሰውዬው ፍላጎት ካሳየና መጽሐፉን ከወሰደ በሚቀጥለው ጊዜ ተመልሰህ ስትሄድ የሰው ልጅና የምድር የወደፊት ተስፋ ምንድን ነው? በሚለው ጥያቄ ላይ እንደምትወያዩ ንገረው።
4 ወይም የቤቱን ባለቤት ሰላም ካልክ በኋላ እንዲህ ልትል ትችላለህ፦
◼ “የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን መልክ ምን ዓይነት የነበረ ይመስልዎታል? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ይህን ‘ሰው መሰል ጦጣ’ ይመስሉ ነበርን? [ፍጥረት የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 83ን አውጣ።] መጽሐፍ ቅዱስ በሥራ 17:26 ላይ የሚናገረውን ልብ ብለው ያስተውሉ። [አንብብ።] ታዲያ ‘የሰው መሰል ጦጣዎች’ ሥዕል በምን ላይ የተመሠረተ ነው?” በገጽ 89 ላይ ካለው ሥዕል በታች የቀረበውን መግለጫ እንዲመልከት አድርግ። ሰውዬው መጽሐፉን ቢያነብ እንደሚጠቀም እንዲሁም የዚህን ጥያቄ መልስ እንደሚያገኝ ንገረው።
5 ሌላው አቀራረብ ደግሞ “ ፍጥረት” የተባለውን መጽሐፍ ሽፋን በማሳየት እንዲህ ልትል ትችላለህ፦
◼ “ዛሬ ጎረቤቶቻችንን ሰው እዚህ ምድር ላይ የተገኘው በዝግመተ ለውጥ ነው? ወይስ በፍጥረት? እያልን እየጠየቅናቸው ነው። እርስዎስ ምን ያስባሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ምንም እንኳ ከፍተኛ ትምህርት ያላቸው ሰዎች ዝግመተ ለውጥን እውነት እንደሆነ አድርገው ቢቀበሉትም ከፍተኛ ትምህርት ያላቸው ሌሎች ደግሞ በዝግመተ ለውጥ አያምኑም። ጠፈርተኛ የነበሩ አንድ ሰው የደረሱበትን ድምዳሜ ልብ ብለው ያስተውሉ። [በገጽ 122–3 ላይ ያሉትን ፍሬ ነገሮች አጉላ።] ዝግመተ ለውጥን ወይም ፍጥረትን ለማመን እንድንችል ማስረጃዎቹን በግል መመርመር አለብን።” ሰውዬው መጽሐፉን ከወሰደ በሚቀጥለው ጊዜ ተመልሰህ ስትሄድ የምትመልሰው አንድ ጥያቄ ልታነሣ ትችላለህ።
6 ስለ ፈጣሪያችን አስደናቂ እውነቶችና ፍጥረቶቹን በተመለከተ ያለውን ፍቅራዊ ዓላማ ሌሎችም እንዲያውቁ ለመርዳት ትጓጓለህን? ፍጥረት የተባለው መጽሐፍ ይህን እንድታደርግ ሊረዳህ ይችላል። መጽሐፉ የአጽናፈ ዓለሙን ጌታ የእጅ ሥራዎች በማሞገስ ስለሚናገር ታላቁን ፈጣሪያችንን ይሖዋን ያስከብራል። እንዲሁም በክርስቶስ መንግሥት አማካኝነት ስሙን ለመቀደስና የሰውን ዘር ለመባረክ ያለውን ግሩም ዓላማ ያሳውቃል።