የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት ለትምህርት መስጫ እንቅስቃሴዎች ድጋፍ ይሰጣል
1 የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት በይሖዋ ድርጅት የትምህርት መስጫ ፕሮግራም ውስጥ ትልቅ ሚና አለው። የመጽሐፍ ጥናት ቡድኖች በጉባኤው ክልል ውስጥ ራቅ ራቅ ብለው በሚገኙና ለሁሉም አመቺ በሆኑ ቦታዎች ላይ ይገኛሉ። ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች በአቅራቢያቸው ስላለ በዚያ እንዲገኙ ግብዣ ቢቀርብላቸው ቶሎ ሊቀበሉ ይችላሉ።
2 እያንዳንዱ የጥናት ቡድን ጥቂት ተሰብሳቢዎች እንዲኖሩት ጥረት ይደረጋል። ይህም ጥናቱን የሚመራው ወንድም በጥናት ቡድኑ ላሉት ለእያንዳንዳቸው በግል እርዳታ እንዲሰጥ ያስችለዋል። የሁሉም አእምሮ የመቀበል ችሎታ እኩል አይደለም። አንድ ሰው ትምህርቱን አስቀድሞ አጥንቶት እያለም ነጥቡን የመረዳት ችግር ካለበት ጥናቱን የሚመራው ወንድም ከጥናቱ በኋላ ተጨማሪ ገለጻ ሊያደርግለት ይችላል። ከዚህም በላይ ጥቂት ሰዎች ባሉት የጥናት ቡድን ሐሳብ ለመስጠትና ጥቅሶችን በማንበብ ይበልጥ የመሳተፍ አጋጣሚ ይኖራል። ሐሳብ በመስጠት አዘውትረህ በውይይቱ ትካፈላለህን? በራስህ አባባል ለመመለስ ትሞክራለህን? በጥናቱ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆንህ አንተንም ሆነ ሌሎችን ይጠቅማል። በምትዘጋጅበት ጊዜ በማመዛዘን ችሎታህ በመጠቀም በትምህርቱ ውስጥ ያሉትን አንዳንድ ነጥቦች በግልህ እንዴት ልትሠራባቸው እንደምትችል ለማስተዋል ሞክር። — ዕብ. 5:14 አዓት
3 የመጽሐፍ ጥናት መሪው የሚጠቀምባቸውን የማስተማሪያ መንገዶች ልብ ብለህ በማስተዋል የቤት መጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ይበልጥ አስደሳችና ትምህርት ሰጭ በሆነ መንገድ እንዴት መምራት እንደምትችል ትማራለህ። አንቀጾቹ ብቃት ባለው ወንድም ከተነበቡ በኋላ በጥያቄዎቹ ላይ ውይይት ይደረጋል። የጥናቱ መሪ ሁሉም ሐሳብ እንዲሰጡ ያበረታታቸዋል። ጊዜው በፈቀደለት መጠን ምዕራፍና ቁጥራቸው ብቻ የተጠቀሱት ጥቅሶች እንዴት እንደምንጠቀምባቸው እንዲገባን ለመርዳት ሲል ሐሳብ እንዲሰጥባቸው ለማድረግ ይጥራል። (ከነህምያ 8:8 ጋር አወዳድር።) አንዳንዴ ቁልፍ የሆነውን ነጥብ ለማስገንዘብ የራሱን አጠር ያለ የማብራሪያ ሐሳብ ሊጨምር ወይም አጋዥ ጥያቄ ሊያቀርብ ይችላል። ምሳሌ ወይም ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠቱ ትምህርቱን በሕይወታችን እንዴት እንደምንሠራበት ለመገንዘብ እንድንችል ይረዳናል።
4 በአንዳንድ የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት ቡድኖች የተሰብሳቢዎች ቁጥር ከሚጠበቀው በታች ነው። አዘውትረህ በመጽሐፍ ጥናት ትገኛለህን? አዘውትረህ የማትገኝ ከሆነ በጣም ጠቃሚ የሆነ ምግብ እያመለጠህ ነው። ይሖዋ ለእኛ እንደሚያስብ ከሚያሳይባቸው መንገዶች አንዱ የመጽሐፍ ጥናት ዝግጅት ነው። (1 ጴጥ. 5:7) ይሖዋ በመንፈሳዊ ጠንካሮች እንሆን ዘንድ በእውቀትና በጥበብ እንድናድግ ይፈልጋል። በሌላ በኩል ደግሞ ሰይጣን መንፈሳዊ እድገታችንን በማጓተትና እኛን በማዳከም ለይሖዋና ለድርጅቱ የምንሰጠው አገልግሎት እንዲቀንስ ይፈልጋል። የሰይጣን ምኞት እንዲሳካ አትፍቀድ! ልብህ የመጽሐፍ ጥናት ቡድንህ ባለው ሞቅ ያለ ስሜትና ፍቅር ተነክቶ ይሖዋን ማወደስህን እንድትቀጥል እንዲገፋፋህ ፍቀድለት። — ከመዝሙር 111:1 ጋር አወዳድር።
5 የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎች ለአስፋፊዎች አመቺ በሆኑት የመጽሐፍ ጥናት በሚደርግባቸው ቤቶች ይደረጋሉ። እነዚህ ስብሰባዎች በሳምንቱ መካከል፣ ቅዳሜና እሁድ ወይም በምሽት ምሥክርነት ለመስጠት የሚደረጉ ዝግጅቶች ሊሆኑ ይችላሉ። የመጽሐፍ ጥናት መሪው በቂ የአገልግሎት ክልል መኖሩንና የመስክ ስምሪቱን የሚመራ ሰው መኖሩን ያረጋግጣል። የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎች ከ10 እና 15 ደቂቃ በላይ መፍጀት የለባቸውም። የዕለት ጥቅሱ ከስብከት ሥራችን ጋር የሚዛመድ ከሆነ የስምሪት ስብሰባውን የሚመራው ወንድም አጠር ያለ ሐሳብ ሰጥቶ ለመስክ አገልግሎት የሚጠቅሙ አንድ ሁለት ሐሳቦችን ወይም አሁን እየተበረከተ ያለውን ጽሑፍ አስመልክቶ አጠር ያለ ትዕይንት ሊያቀርብ ይችላል።
6 የመጽሐፍ ጥናቱ መሪ በቡድኑ ውስጥ ካሉት ከእያንዳንዳቸው ጋር በግል በመሥራት ተገቢውን ማበረታቻና ሥልጠና ለመስጠት ጥረት ያደርጋል። — ከማርቆስ 3:14ና ከሉቃስ 8:1 ጋር አወዳድር።