አቅኚዎች ሌሎችን ይረዳሉ
1 ኢየሱስ “መከሩስ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዴህ የመከሩን ጌታ ለመከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት” በማለት ተናግሯል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የመከሩ ሠራተኞች ጥቂት በመሆናቸውና የሚሸፍኑት ክልልም ሰፊ በመሆኑ ኢየሱስ በተቻለ መጠን በርካታ ሰዎች ምሥራቹን እንዲሰሙ ለማድረግ ሲል ለየብቻ ሊልካቸው ይችል ነበር። ከዚህ ይልቅ ግን “ሁለት ሁለትም አድርጎ . . . ላካቸው።” (ሉቃስ 10:1, 2) ሁለት ሁለት አድርጎ የላካቸው ለምን ነበር?
2 እነዚያ ደቀ መዛሙርት አዲሶችና ብዙ ተሞክሮ የሌላቸው ነበሩ። አንድ ላይ ሆነው በመሥራታቸው አንዳቸው ከሌላው ሊማሩና እርስ በርሳቸው ሊበረታቱ ይችሉ ነበር። ሰሎሞን እንዳለው “አንድ ብቻ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል።” (መክ. 4:9, 10) በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ ከፈሰሰ በኋላም እንኳን ቢሆን ጳውሎስ፣ በርናባስና ሌሎችም የእምነት ባልደረቦቻቸውን በአገልግሎት ያግዟቸው ነበር። (ሥራ 15:35) አንዳንዶች ከእነዚህ ብቃት ካላቸው ወንዶች በግል ሥልጠና ማግኘት መቻላቸው ምንኛ ግሩም መብት ነበር!
3 ግሩም የሆነ የማሠልጠኛ መርሐ ግብር፦ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበረው ጉባኤ ሁሉ ዛሬ ያለው የክርስቲያን ጉባኤም ሰባኪ ድርጅት ነው። ማሠልጠኛም እናገኝበታለን። የእያንዳንዳችን ልባዊ ምኞት ምሥራቹን በተቻለ መጠን ውጤታማ በሆነ መንገድ ማቅረብ መሆን አለበት። ተጨማሪ አስፋፊዎች ውጤታማነታቸውን ከፍ ማድረግ ይችሉ ዘንድ እርዳታ ማግኘት የሚቻልበት ዝግጅት ተደርጓል።
4 በቅርቡ በተካሄደው የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ላይ አቅኚዎች ሌሎችን በመስክ አገልግሎት የሚረዱበት መርሐ ግብር መነደፉን ማኅበሩ አስታውቆ ነበር። ይህ መርሐ ግብር አስፈላጊ ነውን? አዎን፣ አስፈላጊ ነው። ባለፉት ሦስት ዓመታት ከአንድ ሚልዮን የሚበልጡ አስፋፊዎች የተጠመቁ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ብዙዎቹ በስብከቱ ሥራ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ሥልጠና ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። ታዲያ ይህን ሥልጠና ማን ሊሰጥ ይችላል?
5 የሙሉ ጊዜ አቅኚዎች ይህን እርዳታ ሊሰጡ ይችላሉ። የይሖዋ ድርጅት ለአቅኚዎች ብዙ ምክርና ማሠልጠኛ ይሰጣቸዋል። አቅኚዎች ለሁለት ሳምንት በሚቆየው የአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት ወቅት ለእነርሱ የሚያስፈልጉ መመሪያዎችን ያገኛሉ። ከዚህም በተጨማሪ ከወረዳና ከአውራጃ የበላይ ተመልካቾች ጋር ከሚያደርጉት ስብሰባዎችና ሽማግሌዎች ከሚሰጧቸው መመሪያዎች ጥቅም ያገኛሉ። ሁሉም አቅኚዎች የጳውሎስንና የበርናባስ ያክል ተሞክሮ አላቸው ባይባልም ለሌሎች ለማካፈል የሚጓጉበትን ከፍተኛ ዋጋ ያለው ሥልጠና አግኝተዋል።
6 በዚህ ዝግጅት እነማን ይጠቀማሉ? በዚህ ፕሮግራም የመካፈል አጋጣሚ የሚሰጣቸው አዳዲስ አስፋፊዎች ወይም በቅርቡ የተጠመቁ ብቻ ናቸውን? በጭራሽ! እውነትን ካወቁ ዓመታት ያስቆጠሩ ሆኖም በአንዳንድ የአገልግሎት ዘርፎች እርዳታ ቢያገኙ ደስ የሚላቸው ወጣቶችና በዕድሜ የገፉ አስፋፊዎች አሉ። አንዳንዶቹ ጽሑፍ በማበርከቱ ሥራ እንከን የማይወጣላቸው ሲሆኑ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ይቸገራሉ። ሌሎች ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በቀላሉ ማስጀመር ቢችሉም ተማሪዎቻቸው እድገት አያደርጉላቸውም። እድገት እንዳያደርጉ ማነቆ የሆነባቸው ነገር ምን ይሆን? ተሞክሮ ያላቸው አቅኚዎች በእነዚህ አቅጣጫዎች እርዳታ እንዲሰጡ ሊጠየቁ ይችላሉ። አንዳንድ አቅኚዎች የሰዎችን ፍላጎት በመኮትኮት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማስጀመርና አዳዲስ ተማሪዎችን ወደ ድርጅቱ በመምራት በኩል የተዋጣላቸው ናቸው። ያካበቱት ተሞክሮ ለዚህ አዲስ መርሐ ግብር እጅግ ጠቃሚ ነው።
7 በጉባኤው ቋሚ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ላይ የምትፈልገውን ያክል ለመገኘት ፕሮግራምህ እንቅፋት ሆኖብሃል? አብሮህ የሚያገለግል አስፋፊ በማታገኝበት ጊዜ አንድ አቅኚ አብሮህ መሥራት ይችል ይሆናል።
8 ጥሩ የትብብር መንፈስ አስፈላጊ ነው፦ ሽማግሌዎች አቅኚዎች ሌሎችን ይረዳሉ በተባለው ፕሮግራም በመታቀፍ በግል እርዳታ እንዲደረግላቸው ለሚፈልጉ አስፋፊዎች በዓመት ሁለት ጊዜ ዝግጅት ያደርጋሉ። እንዲህ ዓይነቱ እገዛ እንዲደረግልህ ፈቃደኛ ከሆንክ አንተን እንዲረዳ ከተመደበልህ አቅኚ ጋር ሆነህ ለአገልግሎት ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ፕሮግራም አውጡ። ያወጣችሁትንም ፕሮግራም ጠብቁ። ሁለታችሁም ቀጠሮ አክብሩ። አብረህ በምትሠራበት ጊዜ ምሥራቹን ለማቅረብ የሚያስችሉ ውጤታማ መንገዶችን በንቃት ተከታተል። አንዳንዶቹ አቀራረቦች ውጤታማ የሚሆኑበትን ምክንያት ለማወቅ ጥረት አድርግ። አቀራረብህን እንድታሻሽል አቅኚው የሚሰጥህን ሐሳብ በቁም ነገር ተመልከተው። የተማርካቸውን ነገሮች በተግባር ላይ ባዋልክ መጠን በአገልግሎት የምታደርገው እድገት ለአንተም ሆነ ለተመልካቾች በግልጥ የሚታይ ይሆናል። (1 ጢሞቴዎስ 4:15ን ተመልከት።) መደበኛ ያልሆነውን አገልግሎትን ጨምሮ በሁሉም የአገልግሎት ዘርፎች በመካፈል የተቻላችሁን ያህል ብዙ ጊዜ አብራችሁ ሥሩ። ይሁን እንጂ በግል እርዳታ በሚያስፈልግህ አቅጣጫ ላይ ትኩረት አድርግ።
9 የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ በዚህ መንገድ የሚደረገውን እድገት ይከታተላል። አልፎ አልፎ ከፕሮግራሙ ምን ያክል ጥቅም እያገኘህ እንዳለህ ለማወቅ የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት መሪውን ያነጋግራል። የወረዳ የበላይ ተመልካቹም እንዲሁ ጉባኤውን በሚጎበኝበት ጊዜ እገዛ ያደርግልሃል።
10 ይሖዋ ሕዝቦቹ እንዲሰለጥኑና ‘ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጁ እንዲሆኑ’ ይፈልጋል። (2 ጢሞ. 3:16) አቅኚዎች ሌሎችን ይረዳሉ የተባለው ዝግጅት ቃሉን የመስበክ ችሎታቸውን ለማሻሻል የሚፈልጉትን ሰዎች ለመርዳት ተብሎ እንደተደረገ ዝግጅት አድርጋችሁ ተመልከቱት። በዚህ ዝግጅት የመካፈል መብት ካገኘህ በአመስጋኝነት፣ በትሕትናና በደስታ መንፈስ ተቀበለው።