በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከተከሰቱት ነገሮች ሁሉ የላቀ ትርጉም ያለው ድርጊት
1 ኢየሱስ በአባቱ ትእዛዝ ወደ ምድር የመጣው እኛን ወደ ዘላለም ሕይወት ስለሚመራው እውነት ለመመሥከር ነው። (ዮሐ. 18:37) እስከ ሞት ድረስ ታማኝነትን ማሳየቱ ለይሖዋ ክብር አምጥቷል፣ የአምላክ ስም እንዲቀደስ አድርጓል እንዲሁም ቤዛ አስገኝቷል። (ዮሐ. 17:4, 6) የኢየሱስን ሞት በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከተከሰቱት ነገሮች ሁሉ የላቀ ትርጉም ያለው ድርጊት የሚያደርገው ይህ ነው።
2 ከአዳም መፈጠር ጀምሮ በምድር ላይ የኖሩት ሁለት ፍጹማን ሰዎች ብቻ ነበሩ። አዳም ከአብራኩ ለሚወጡት ልጆቹ አስደናቂ በረከቶችን ሊያስገኝላቸው በሚችልበት ሁኔታ ውስጥ ነበር። ሆኖም በራስ ወዳድነት በማመፁ ምክንያት በሞት ለሚያከትም አሳዛኝ ሕይወት ዳረጋቸው። ኢየሱስ ሲመጣ እምነት ያላቸው ሁሉ የዘላለም ሕይወት የሚያገኙበትን መንገድ በመክፈት ፍጹም ታማኝነትንና ታዛዥነትን አሳየ።— ዮሐ. 3:16፤ ሮሜ 5:12
3 ከኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት ጋር ሊወዳደር የሚችል ድርጊት የለም። የሰው ልጆችን የታሪክ ሂደት ለውጧል። በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ትንሣኤ የሚያገኙበትን መንገድ ከፍቷል። ክፋትን ወደ ፍጻሜው ለሚያመጣና ምድርን ወደ ገነትነት ለሚለውጠው ዘላለማዊ መንግሥት መሠረት ጥሏል። በመጨረሻ ሰዎችን በሙሉ ከማንኛውም ዓይነት ጭቆናና ባርነት ነፃ ያደርጋል።— መዝ. 37:11፤ ሥራ 24:15፤ ሮሜ 8:21, 22
4 ይህ ሁሉ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ የሞቱን መታሰቢያ በየዓመቱ እንዲያከብሩ ለምን እንዳዘዛቸው እንድንገነዘብ ይረዳናል። (ሉቃስ 22:19) በዓሉ ያለውን ትልቅ ትርጉም በመገንዘብ በዓለም በሙሉ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ዓርብ ሚያዝያ 14 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ ለመገኘት በጉጉት እንጠባበቃለን። ከበዓሉ በፊት ኢየሱስ በምድር ላይ ስላሳለፋቸው የመጨረሻ ቀኖቹና ለእውነት ስለነበረው ቆራጥ አቋም የሚተርኩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ከቤተሰብ ጋር ሆኖ ማንበብ ጥሩ ነው። (እንዲነበቡ የተመደቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በ1995 የቀን መቁጠሪያ እና ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ መመርመር በተባለው ቡክሌት ከሚያዝያ 9–14 ባሉት ቀናት ውስጥ ተጠቅሰዋል።) ኢየሱስ ለፈጣሪያችን በማደር ረገድ ምሳሌ ትቶልናል። (1 ጴጥ. 2:21) ወዳጆቻችንንና ቤተሰባችንን እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንንና ሌሎች ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች በዚህ ትልቅ ትርጉም ያዘለ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ የምንችለውን ሁሉ እናድርግ። ቀደም ብላችሁ ምን እንደሚደረግና የምሳሌያዊዎቹ ቂጣና ወይን ጠጅ ትርጉም ምን እንደሆነ ግለጹ።— 1 ቆሮ. 11:23–26
5 ሽማግሌዎች የመንግሥት አዳራሹ በሥርዓት መያዙንና ንጹሕ መሆኑን ለማረጋገጥ አስቀድመው እቅድ ማውጣት አለባቸው። ምሳሌያዊዎቹን ቂጣና ወይን ጠጅ እንዲያዘጋጅ አንድ ሰው መመደብ አለበት። ምሳሌያዊዎቹን ቂጣና ወይን ጠጅ የሚያዞሩት በጥሩ ሁኔታ የተደራጁ መሆን አለባቸው። ለጌታ ራት ተገቢውን አክብሮት የምናሳይባቸው አንዳንድ መንገዶች መጠበቂያ ግንብ 2–106 ገጽ 17 ላይ ተገልጸዋል። ጉባኤዎች ከመታሰቢያው በዓል ቀደም ብለው ባሉትና ከዚያ በኋላ ባሉት ጥቂት ቀናት ለመስክ አገልግሎት ተጨማሪ ዝግጅት ቢያደርጉ በጣም ጥሩ ነው።
6 ባለፈው ዓመት ይህን ከፍተኛ ትርጉም ያዘለ ድርጊት ለማስታወስ በመላው ዓለም በጠቅላላው 12,288,917 ሰዎች ተገኝተው ነበር። በቀን መቁጠሪያችን ላይ ከሰፈሩት ቀናት ከሁሉ የላቀ ትርጉም ያለው ቀን ይህ ስለሆነ ሁላችንም መገኘት አለብን።