ብርሃን አብሪዎች በመሆን ምሳሌያችንን መከተል
1 ኢየሱስ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” በማለት ስለ ራሱ ተናግሯል። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም የእርሱን ምሳሌ በመከተል “የዓለም ብርሃን” ነበሩ። (ማቴ. 5:14) ኢየሱስ “የዓለም ብርሃን” እንደመሆኑ መጠን እርሱን የሚከተሉት ሁሉ “የሕይወት ብርሃን” እንደሚያገኙ ለመናገር ችሎ ነበር። (ዮሐ. 8:12) ይህም መንፈሳዊ ብርሃን አብሪዎች ያደርገናል። ይህንንም ብርሃን ምንም ነገር እንዲሸፍነው ወይም እንዲጋርደው በጭራሽ መፍቀድ አይኖርብንም።
2 የይሖዋ ድርጅት እንዴት የተዋጣልን ብርሃን አብሪዎች መሆን እንደምንችል ለማሳየት ማሰልጠኛ ያቀርብልናል። የምናገኘውን ምክርና መመሪያ በቅርብ የምንከተል ከሆነ የመንግሥቱን እውነት በተመለከተ ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ግልጽ ማብራሪያ መስጠት እንችላለን። (1 ጢሞ. 4:6) ብርሃን አብሪ ሆኖ ማገልገል በማንኛውም አጋጣሚ እውነትን መናገር ብቻ ሳይሆን ክርስቲያን እንደመሆናችን መጠን ጥሩ ጠባይ ይዞ መመላለስንም ይጨምራል። ምሳሌያችን ምንም የሚያስነቅፍ ጠባይ አልነበረውም። እኛም የእርሱ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን ክርስትና የዕለት ተዕለት የሕይወታችን መንገድ መሆኑን ማሳየት አለብን። (ኤፌ. 5:9፤ ቲቶ 2:7, 8, 10) ሌሎች ሰዎች ሊያዩአቸው የሚችሉና አምላክን እንዲያከብሩ የሚገፏፏቸውን ጥሩ ሥራዎች መፈጸም አለብን።—ማቴ. 5:16
3 አንድ የይሖዋ ምሥክር ከቤት ወደ ቤት በሚሄድበት ጊዜ አንድ ያልተለመደ ጥያቄ ገጠመው። የቤቱ ባለቤትና ሚስቱ በጣም ታመው ስለነበር ጥቂት ገንዘብ ባንክ የሚያስገባላቸው ሰው አስፈልጓቸው ነበር። ይህንንም ምሥክሩ ሊያከናውንላቸው ይችል እንደሆነ ጠየቁት። እርሱም እሺ አላቸውና ባንክ እንዲያስገባላቸው 2,000 የአሜሪካን ዶላር ተቀበላቸው! ገንዘቡን ባንክ አስገብቶ ሲመለስ “ምንም ሳታውቁኝ እንዴት ልታምኑኝ ቻላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። “እምነት የሚጣልባቸው የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ እንደሆኑ እኛም ሆንን ሌሎች ሰዎች ያውቃሉ” በማለት መለሱለት። የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር መሠረታዊ ሥርዓቶች አጥብቀን በመከተላችን እንዲህ ያለ ለአምላክ ክብር የሚያመጣ ጥሩ ስም በማትረፋችን ምንኛ አመስጋኞች ልንሆን እንችላለን!
4 አንዲት የአንደኛ ክፍል አስተማሪ አንዲት የስድስት ዓመት ምሥክር ተማሪ የሃሎዊንን ሥዕሎች ቀለም በመቀባት ለምን እንዳልተካፈለች ለተማሪዎችዋ አብራርታለች። ተማሪዋ ባላት እምነት ምክንያት ከሌሎች ልዩ ለመሆን የሚያበቃትን ድፍረት በመያዟ በጣም እንደምትኮራባት አስተማሪዋ ተናግራለች። አንድን ነገር አጥብቀን የምናምንበት ከሆነ በእምነታችን ጸንተን ለመቆም የሚያስችል ድፍረት ሊኖረን ይገባል በማለት አስተያየቷን ሰጥታለች። በዚያው ምሽት አስተማሪዋ ስለራሷ እምነት ካሰላሰለች በኋላ እርሷ ለእምነቷ ተመሳሳይ የሆነ የድፍረት አቋም እንዳላሳየች አምና ለመቀበል ተገድዳለች። በሚቀጥለው ቀን የክፍሏን ተማሪዎች በማንኛውም የበዓል አከባበር ላይ ተካፋይ እንዲሆኑ እንደማታደርግ በግልጽ አሳወቀች። አንዳንዶቹ በዓላት ሯሷም የማታምንባቸው ነበሩ።
5 የይሖዋ ሕዝቦች በየትም ቦታ ይኑሩ ብርሃናቸውን ቦግ አድርገው ለማብራት ይፈልጋሉ። ወጣቶች በትምህርት ቤት በሚያሳዩት መልካም ጠባይ የተነሳ አብረዋቸው በሚማሩት ተማሪዎችና በአስተማሪዎች ዘንድ አድናቆትን አትርፎላቸዋል። ለጎረቤቶቻቸው ጥሩ ጠባይ የሚያሳዩ የይሖዋ ምሥክሮች ሌሎች ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት ጥሩ ነገር እንዲናገሩ አነሳስቷቸዋል። ብዛት ባላቸው አጋጣሚዎች የሚከናወነው መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ብዙ ለማወቅ ፍላጎት ያላቸውን ቅን ሰዎች ስቧል። ተቀጥረን በምንሠራባቸው መሥሪያ ቤቶች የምናሳየው ትጋትና ሐቀኛነት ምሥክርነት ይሰጣል። አዎን፣ የትም ቦታ እንኑር ወይም ምንም ዓይነት ሥራ እንሥራ ለእውነት የሰዎችን ፍላጎት ልናነሳሳ እንችላለን።
6 ታላቁ ምሳሌያችን በተወልን እንከን የለሽ የአኗኗር መንገድ ላይ ዓይናችን እንዲያተኩር በማድረግ የእርሱ ደቀ መዛሙርት መሆናችንን በሚያስመሰክር ሁኔታ ችሎታችንን ይበልጥ እያሻሻልን መሄድ እንችላለን። የእርሱን ምሳሌ መኮረጃችን ብርሃናችን ‘በሁሉም ላይ’ እንዲበራ ያደርጋል።— ማቴ. 5:15፤ 1 ጴጥ. 2:21