መጽሔቶችን በማንኛውም አጋጣሚ አበርክቱ
1 መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን የምናደንቅበት ጥሩ ምክንያት አለን። የእነዚህን ያህል ዓለም አቀፋዊ ተወዳጅነት ያለው ሌላ መጽሔት ይኖራልን? በዚህ ወር በምናከናውነው የስብከት ሥራ መጽሔቶች እናበረክታለን። ብዙውን ጊዜ አብዛኞቹን መጽሔቶቻችንን የምናበረክተው ከቤት ወደ ቤት በምናደርገው አገልግሎት ቢሆንም በሌላ በማንኛውም ተስማሚ አጋጣሚ ለማበርከትም ዝግጁ መሆን እንፈልጋለን።
2 የጥቅምት 1 “መጠበቂያ ግንብ” ስታበረክት እንደሚከተለው በማለት “ጦርነት የማይኖርበት ዓለም የሚመጣው መቼ ነው?” ለሚለው ርዕስ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ማድረግ ትችላለህ:-
◼ “ሰዎች ብዙ ጥረት ያደረጉ ቢሆንም ጦርነት የሌለበት ዓለም ይመጣል የሚል ተስፋ አለመኖሩ በርካታ ሰዎችን ያስገርማቸዋል። በጥቅምት 1 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 5 ላይ ስለሚገኙት ስለ እነዚህ ሐሳቦች ምን አስተያየት አለዎት? [“ሃይማኖት ትልቅ እንቅፋት ሆኗል” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር ያሉትን የመጀመሪያዎቹን ሁለት አንቀጾች የመጀመሪያ ዓረፍተ ነገር አንብብና መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] እርግጥ ይህ ማለት ጦርነቶች ሁልጊዜ ይኖራሉ ማለት አይደለም። አምላክ በኢሳይያስ 9:6, 7 ላይ የሰጠውን ተስፋ ልብ ይበሉ።” ይህንን ጥቅስ ከመጽሐፍ ቅዱስህ ወይም መጠበቂያ ግንብ መጽሔቱ ላይ ከተጠቀሰው ልታነብ ትችላለህ። መጠበቂያ ግንብ ሰላማዊ ዓለም ያስገኛል ተብሎ ብቸኛ ተስፋ የሚጣልበት የአምላክ መንግሥት እንደሆነ በግልጽ እንደሚናገር አጠር አድርገህ ግለጽለትና ርዕሱን እንዲያነብ አበረታታው።
3 የአማርኛውን ከሐምሌ–መስከረም “ንቁ!” መጽሔት ስታበረክት እንዲህ ማለት ትችላለህ:-
◼ “በዚህ መጽሔት ሽፋን ላይ ያለውን ‘ኤድስ በአፍሪካ— ማቆሚያው ምን ይሆን?’ የሚለውን ጥያቄ በተመለከተ የእርስዎ አመለካከት ምንድን ነው? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] እነዚህ ተከታታይ ርዕሶች በጊዜያችን በጣም አስፈሪ ስለሆነው በሽታ ይናገራሉ። እንደሚያውቁት ኤድስ አስደንጋጭ በሆነ ፍጥነት እየተሰራጨ ነው። ማቆሚያው ምን ይሆን? ለመልሱ ይህንን ቅጂ ትቼልዎት ብሄድ ደስ ይለኛል፤ እንዲያነቡት ሐሳብ አቀርብልዎታለሁ።”
4 የመስከረም 1, 1995 “መጠበቂያ ግንብ” ስታበረክት ቀጥሎ ባለው መግቢያ ልትጠቀም ትችላለህ:-
◼ “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሁለት ዓይነት መንገዶች ተናግሮ እንደነበረ ያስታውሳሉን? እዚህ ማቴዎስ 7:13, 14 ላይ እንዲህ ብሏል . . . [አንብብ] ጠባቡ መንገድ የነፃነት መንገድ ነው ቢባል አይስማሙምን? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት] ይህችን መጽሔት በማንበብ ወደ ነፃነት ስለሚወስደው ጠባብ መንገድ ይበልጥ ቢመራመሩ ከፍተኛ ጥቅም ያገኛሉ።”
5 ከቤት ወደ ቤት ስትሠራ ትንንሽ መደብሮችንና ሱቆችን አትለፋቸው። ዘወትር በሱቆች የሚመሠክሩ አስፋፊዎች ይህ ሥራ አስደሳችና ፍሬያማ እንደሆነ ተናግረዋል። “ንቁ!” መጽሔትን ስታበረክት እንደሚከተለው ያለ ቀላል አቀራረብ ልትጠቀም ትችላለህ:-
◼ “የንግድ ሰዎች የሚኖሩበትን ማኅበረሰብ የሚነኩ ወቅታዊ ጉዳዮችን መከታተል እንደሚፈልጉ እናውቃለን። እነዚህ ርዕሶች እንደሚያስደስቱዎት እርግጠኛ ነኝ።” ከዚያም ከርዕሱ ውስጥ አንድ ነጥብ አጠር አድርገህ ንገረው።
6 ልታነጋግረው የቀረብከው ሰው በሥራ የተወጠረ ከሆነ መጽሔቶቹን አሳይተህ እንዲህ ማለት ትችላለህ:-
◼ “ዛሬ እንግዳ ይመጣብኛል ብለው እንዳልጠበቁ እርግጠኛ ነኝ፤ ስለዚህ የመጣሁበትን ጉዳይ አጠር አድርጌ ለመግለጽ እሞክራለሁ። አንድ ትልቅ ቁም ነገር የያዘ ጽሑፍ እንዲያነቡ ይዤልዎት መጥቻለሁ።” የመርጥከውን ርዕስ አሳየውና መጽሔቶቹን አበርክትለት።
7 ሁልጊዜ ከቤት ወደ ቤት መመዝገቢያ ቅጽህ ላይ መዝግብ። እንዲሁም ያበረከትክላቸውን ሰዎች ሁሉ ተመልሰህ አነጋግራቸው። ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርግ ልባዊ ፍላጎት ካሳዩ ኮንትራት እንዲገቡ ሐሳብ አቅርብላቸው። መጽሔቶቻችንን በማንኛውም ተስማሚ አጋጣሚ ለማበርከት ዝግጁና ንቁ እንሁን።