ሰሚዎች ብቻ ሳይሆን አድራጊዎች ሁኑ
1 በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ እውነተኛ ክርስቲያኖች ሰሚዎች ብቻ ሳይሆኑ አድራጊዎች እንዲሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጣቸውን ምክር ይሠሩበታል። (ያዕ. 1:22) ይህም አምላክን በአፋቸው ብቻ ከሚያገለግሉት ክርስቲያን ነን ባዮች ፈጽሞ የተለዩ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። (ኢሳ. 29:13) ኢየሱስ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርጉ ሰዎች ብቻ እንደሚድኑ በግልጽ ተናግሯል።— ማቴ. 7:21
2 አምላካዊ ተግባራት ያልታከሉበት አምልኮ ከንቱ ነው። (ያዕ. 2:26) ስለዚህ ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቅ አለብን:- ‘የያዝኩትን እምነት ከልብ እንደማምንበት ተግባሬ የሚያረጋግጠው ምን ያህል ነው? ከማምንበት ነገር ጋር በእርግጥ ተስማምቼ እንደምኖር የሚያሳየው ምንድን ነው? ኢየሱስን ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ መምሰል የምችለው እንዴት ነው?’ ለእነዚህ ጥያቄዎች የምንሰጣቸው ሐቀኝነት የተሞላባቸው መልሶች እስካሁን ድረስ ምን እድገት እንዳደረግን ወይም የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ረገድ አሁንም ቢሆን የሚጎድለን ነገር እንዳለ ለመገንዘብ ያስችለናል።
3 የኢየሱስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን ዋንኛው ግባችን መዝሙራዊው “ቀኑን ሙሉ ለአምላክ ውዳሴ እናቀርባለን፣ ስምህንም ለዘላለም ከፍ ከፍ እናደርጋለን” በማለት የተናገረው ዓይነት መሆን አለበት። (መዝ. 44:8 አዓት) ክርስትና በየዕለቱ በምንሠራቸው በማናቸውም ተግባራት የሚታይ የአኗኗር መንገድ ነው። በምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ ይሖዋን ለማወደስ ያለንን ልባዊ ምኞት ስናሳይ እንዴት ያለ እርካታ ይሰማናል!— ፊልጵ. 1:11
4 ይሖዋን ማወደስ ጥሩ ሥነ ምግባር ከመያዝ የበለጠ ነገር ይጠይቃል፦ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ጥሩ ባሕርይ እንዲኖረን ብቻ ቢሆን ኖሮ ጠባያችንን በማሻሻል ተግባር ላይ ብቻ ማተኮር እንችል ነበር። ይሁን እንጂ አምልኮታችን የይሖዋን በጎነት በስፋት ማወጅንና ስሙን በሰዎች ፊት ማስታወቅን ይጨምራል!— ዕብ. 13:15፤ 1 ጴጥ. 2:9
5 ከምናከናውናቸው በጣም አስፈላጊ የሆኑ ሥራዎች አንዱ ምሥራቹን በሕዝብ ፊት ማወጅ ነው። ኢየሱስ የስብከቱ ሥራ ለሚሰሙት ሰዎች የዘላለም ሕይወት እንደሚያስገኝላቸው ያውቅ ስለነበር ሕይወቱን ለዚህ ሥራ አውሏል። (ዮሐ. 17:3) ዛሬም ቢሆን ‘ቃሉን የማገልገሉ’ አስፈላጊነት አልቀነሰም፤ ሰዎች ሊድኑ የሚችሉበት ብቸኛው መንገድ ይህ ነው። (ሥራ 6:4፤ ሮሜ 10:13) ስብከቱ የሚያስገኛቸውን ከፍተኛ ጥቅሞች ስንገነዘብ ጳውሎስ ‘ቃሉን እንድንሰብክ’ እና ይህንንም ‘በጥድፊያ ስሜት እንድናከናውን’ አጥብቆ የመከረን ለምን እንደሆነ ልናስታውስ እንችላለን።— 2 ጢሞ. 4:2
6 ሕይወታችን ይሖዋን በማወደሱ ሥራ ምን ያህል መጠመድ ይኖርበታል? መዝሙራዊው ይሖዋን የማወደሱ ጉዳይ ሁልጊዜ ከአእምሮው እንደማይጠፋ ተናግሯል። እኛስ እንደዚህ ይሰማናልን? አዎን ይሰማናል፣ ከቤት ወደ ቤት ከማገልገላችንም በተጨማሪ ከሌሎች ሰዎች ጋር በተገናኘን ቁጥር ስለ ይሖዋ ስም ለመናገር አጋጣሚ እንደተከፈተልን እናስባለን። ከሰዎች ጋር የምናደርገውን ውይይት ወደ መንፈሳዊ ጉዳዮች ለመቀየር ተስማሚ አጋጣሚዎችን እንፈልጋለን። ከዚህም በላይ ጉባኤው በሚያዘጋጃቸው የመስክ አገልግሎት እንቅስቃሴዎች ዘወትር ለመሳተፍ እንጥራለን። ጽሑፎች በማበርከትና ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ለማስጀመር አስበን ተመላልሶ በመጠየቅ ረገድ ንቁዎች መሆን አለብን። ሁኔታቸው የሚፈቅድላቸውና ተቀጥረው የማይሠሩ አስፋፊዎች የአቅኚነት አገልግሎትን በቁም ነገር ሊያስቡበት ይችላሉ። አቅኚነት በሕይወታችን ውስጥ ሁልጊዜ ለስብከቱ ሥራ የመጀመሪያውን ቦታ እንድንሰጠው ይረዳናል። የአምላክ ቃል የይሖዋን ፈቃድ ያለማቋረጥ ካደረግን ደስተኞች እንደምንሆን ያረጋግጥልናል።— ያዕ. 1:25