ከ1996 ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ጥቅም ማግኘት— ክፍል 1
1 “የ1996 ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ፕሮግራም” ላይ የወጡትን መመሪያዎች አንብበሃቸዋልን? የተደረጉትን አንዳንድ ለውጦች አስተውለሃልን? ከጥር እስከ ሚያዝያ ድረስ ክፍል ቁ. 3 የሚወሰደው ማመራመር ከተባለው መጽሐፍ ሲሆን ከግንቦት እስከ ታኅሣሥ ደግሞ እውቀት ከተባለው አዲስ መጽሐፍ ነው። ክፍል ቁ. 4 ማመራመር ከተባለው መጽሐፍ ይወሰዳል።
2 የተማሪ ክፍሎች፦ ክፍል ቁ. 3 ለአንዲት እህት ይሰጣል። ክፍሉ የተመሠረተው ማመራመር በተባለው መጽሐፍ ላይ ከሆነ ከቤት ወደ ቤት ወይም መደበኛ ያልሆነ ምስክርነት ሲሰጥ የሚያሳይ መሆን አለበት። እውቀት በተባለው መጽሐፍ ላይ የተመሠረተ ከሆነ በተመላልሶ መጠየቅ ወይም በቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መልክ መቅረብ አለበት። ወደፊት እውቀት የተባለው መጽሐፍ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት በሰፊው የሚሠራበት ስለሆነ ክፍሉ በዚህ መንገድ መቅረቡ እጅግ ጠቃሚ ነው።
3 ክፍሉ በቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መልክ የሚቀርብ ከሆነ ክፍሉን የሚያቀርቡት እህቶች ሊቀመጡ ይችላሉ። ጥቂት የመግቢያ ሐሳቦች በማቅረብ ወደ ጥናቱ ከተሸጋገርሽ በኋላ በመጽሐፉ ላይ የሰፈረውን ጥያቄ ጠይቂ። እንደ ጥናት ሆና ክፍሉን የምታቀርበው እህት በተጋነነ ሁኔታ ድራማ ከማቅረብ ይልቅ እውነታውን ማሳየት ይኖርባታል። ጊዜ በፈቀደ መጠን የተጠቀሱትን ጥቅሶች አውጥቶ ማንበብ ይቻላል። ክፍሉን የምታቀርበው እህት ጥናቷ ሐሳብ እንድትሰጥ ጥያቄዎችን በመጠየቅና በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኙትን ጥቅሶች እየጠቀሰች በማመራመር የማስተማር ጥበብ ተጠቅማ ትምህርት መስጠት ይኖርባታል።
4 ለክፍሉ በተመደቡት አንቀጾች ውስጥ ያሉትን ጥቅሶች በአምስት ደቂቃ አንብቦ መጨረስ የማይቻል ከሆነ ምን መደረግ አለበት? ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች የሚያጎሉ ቁልፍ ጥቅሶች ምረጪና ሌሎችን እለፊያቸው። የተጠቀሱት ጥቅሶች ጥቂት ከሆኑ በትምህርቱ ውስጥ ያሉትን ዋና ዋና ነጥቦች በሰፊው ማብራራት ይቻላል። አልፎ አልፎ ከመጽሐፉ ውስጥ አንድ አንቀጽ ወይም አንድ ዓረፍተ ነገር አንብቦ ከሰውዬው ጋር መወያየት ይቻላል።
5 ተማሪዋ የምዕራፉን የመጨረሻ አንቀጽ የሚያጠቃልል ክፍል ከተሰጣት እውቀት በተባለው መጽሐፍ ውስጥ በእያንዳንዱ ምዕራፍ መጨረሻ ላይ የሚገኘውን “እውቀትህን ፈትሽ” የሚለውን ሣጥን አጠር አድርጋ መከለስ ትችላለች። በተሰጡት አንቀጾች ውስጥ ያሉትን ሣጥኖችም ጊዜ በፈቀደ መጠን መከለስ ይቻላል። ሣጥኑ በሁለት ክፍሎች መሃል የሚገኝ ከሆነ የመጀመሪያውን ክፍል የወሰደችው እህት ታቀርበዋለች። በመጽሐፉ ውስጥ ያሉት ሥዕሎች እየተጠና ካለው ትምህርት ጋር ተስማሚ በሚሆኑበት ጊዜ ሐሳብ ሊሰጥባቸው ይችላል።
6 እንደሌሎቹ ክፍሎች ክፍል ቁ. 4 በጣም ማራኪ በሆነና ተግባራዊ ጥቅም በሚያስገኝ መንገድ መቅረብ አለበት። በየሳምንቱ ክፍል ቁ. 4 ላይ ማመራመር ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ ለስብከት ሥራችን የሚጠቅም አንድ ጉዳይ ይቀርባል። እባካችሁ የራሳችሁን ቅጂ ይዛችሁ በመምጣት እየተከታተላችሁ መጽሐፉ ላይ ባሉት ተግባራዊ ነጥቦች ላይ ምልክት አድርጉ።
7 ትምህርት ቤቱ በሚሰጠው ሥልጠና ሙሉ በሙሉ ከተጠቀምንበት ጥሩ “የማስተማር ጥበብ” እንዳለን በሚያሳይ ሁኔታ በተሻለ መንገድ ‘ቃሉን መስበክ’ እንችላለን።— 2 ጢሞ. 4:2 አዓት