የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • km 2/97 ገጽ 7
  • የጥያቄ ሣጥን

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የጥያቄ ሣጥን
  • የመንግሥት አገልግሎታችን—1997
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የተፈጥሮ አደጋ ቢደርስ ዝግጁ ናችሁ?
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2007
  • አደጋ ከደረሰ በኋላ እርዳታ ማበርከት የሚቻለው እንዴት ነው?
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2023
  • ወንድሞቻችሁ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በጽናት እንዲቋቋሙ እርዷቸው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
  • የእርዳታ አገልግሎት
    የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው!
ለተጨማሪ መረጃ
የመንግሥት አገልግሎታችን—1997
km 2/97 ገጽ 7

የጥያቄ ሣጥን

◼ የተፈጥሮ አደጋ ሲከሰትና በወንድሞቻችን ላይ ጉዳት ሲያደርስ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

የተፈጥሮ አደጋ በእናንተ አካባቢ ቢከሰት፦ አትሸበሩ። ረጋ ብላችሁ ንብረት ሳይሆን የበለጠ ዋጋ ያለውን ሕይወት ለማዳን ተረባረቡ። ቤተሰባችሁ በአስቸኳይ የሚያስፈልገውን ቁሳዊ እንክብካቤ አድርጉለት። ከዚያም በምን ሁኔታ ላይ እንዳላችሁና የት እንደምትገኙ ለሽማግሌዎች አሳውቁ።

ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች እርዳታ በማቅረቡ ሥራ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ከፍተኛ አውሎ ነፋሶችን የመሳሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎች እንደሚደርሱ አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ ተነግሮ ከነበረ ሁሉም ወንድሞች አደጋው ወደማይደርስበት አካባቢ ሸሽተው መሄዳቸውን እነዚህ ወንድሞች ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፤ በተጨማሪም ጊዜ የሚፈቅድላቸው ከሆነ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች አግኝተው ለሌሎች ማከፋፈል ይኖርባቸዋል።

ከዚያም በኋላ የመጽሐፍ ጥናት መሪዎች እያንዳንዱን ቤተሰብ ፈልገው ስለ ደህንነታቸው መጠየቅ ይኖርባቸዋል። ለሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹ ወይም ለሌላ ሽማግሌ የእያንዳንዱን ቤተሰብ ሁኔታ፣ ደህና ቢሆንም እንኳ ማሳወቅ ይገባል። አንድ ሰው አደጋ ከደረሰበት ሽማግሌዎች ሕክምና እንዲያገኝ ዝግጅት ለማድረግ ይጥራሉ። በተጨማሪም እንደ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ የመሳሰሉ ማናቸውንም አቅርቦቶች ወይም አስፈላጊ የሆኑ የቤት ቁሳቁሶችን ያቀርባሉ። (ዮሐ. 13:​35፤ ገላ. 6:​10) የጉባኤ ሽማግሌዎች መንፈሳዊና ስሜታዊ እርዳታዎችን ለጉባኤው ይሰጣሉ። በተቻለ ፍጥነት የጉባኤ ስብሰባዎች መደረጋቸውን እንዲቀጥሉ ዝግጅት ያደርጋሉ። ስለደረሰው ሁኔታ የተሟላ ግምገማ ከተደረገ በኋላ ማንኛውንም የመቁሰል አደጋና በመንግሥት አዳራሹም ሆነ በወንድሞች ቤት ላይ የደረሰውን ጉዳት እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች ነገሮችን አስመልክቶ የሽማግሌዎችን አካል በመወከል አንድ ሽማግሌ ለወረዳ የበላይ ተመልካቹ ማሳወቅ ይኖርበታል። የወረዳ የበላይ ተመልካቹም የደረሰውን ዘገባ ለቅርንጫፍ ቢሮው በስልክ ያሳውቃል። የወረዳ የበላይ ተመልካቹን ማግኘት የማይቻል ከሆነ ሽማግሌዎቹ ከቅርንጫፍ ቢሮው ጋር በቀጥታ ሊገናኙ ይችላሉ። ቅርንጫፍ ቢሮው አስፈላጊ የሆነውን ማንኛውንም መጠነ ሰፊ እርዳታ ያስተባብራል።

የተፈጥሮ አደጋ በሌላ አካባቢ ሲከሰት፦ በአደጋው አካባቢ የሚኖሩትን ወንድሞችና እህቶች በጸሎታችሁ አስቧቸው። (2 ቆ⁠ሮ. 1:​8-11) የገንዘብ እርዳታ ለመላክ የምትፈልጉ ከሆነ እርዳታችሁን (የይሖዋ ምሥክሮች፣ ፖ.ሣ.ቁ. 5522፣ አዲስ አበባ) ብላችሁ ወደ ማኅበሩ መላክ ትችላላችሁ። ማኅበሩም የተላኩለትን እርዳታዎች ለዚህ ዓላማ ያውላቸዋል። (ሥራ 2:​44, 45፤ 1 ቆ⁠ሮ. 16:​1-3፤ 2 ቆ⁠ሮ. 9:​5-7፤ የታኅሣሥ 1, 1985 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ገጽ 20-22 ተመልከት።) ጉዳት የደረሰባቸው ወንድሞች በቀጥታ እስካልጠየቋችሁ ድረስ ቁሳዊ ወይም ሌሎች እርዳታዎችን አደጋ ወደ ደረሰበት አካባቢ አትላኩ። ይህም የእርዳታ ቁሳቁሶች ሥርዓት በጠበቀና ተገቢ በሆነ መንገድ እንዲከፋፈል ያስችላል። (1 ቆ⁠ሮ. 14:​40) እባካችሁ አደጋ ከደረሰበት አካባቢ የሚመጡትን የስልክ መልእክቶች ለማስተናገድ እንዲቻል ለጥቃቅን ምክንያቶች ብላችሁ ወደ ማኅበሩ ስልክ አትደውሉ።

ተገቢ የሆነ ምርመራ ከተደረገ በኋላ የእርዳታ ኮሚቴ ማቋቋም አስፈላጊ ስለመሆኑ ማኅበሩ ይወስናል። ኃላፊነት ላላቸው ወንድሞች ይነገራቸዋል። ሁሉም ወንድሞች በአጣዳፊ የሚያስፈልጓቸው ነገሮች ሁሉ ሳይዘገይ እንዲደርሳቸው ሁሉም የመሪነቱን ቦታ ከያዙት ወንድሞች ጋር መተባበር ይኖርባቸዋል።​— የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪ የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች የተሰኘውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ከገጽ 310-15 ተመልከት።

የቀብር ንግግር በሚሰጥበት ጊዜ አንዳንድ ሰዎች የሚፈጥሩትን ሁከት ለማስወገድ ምን ተግባራዊ እርምጃዎች መውሰድ ይቻላል?

ምንም እንኳ በእኛ አካባቢ የቀብር ንግግር የሚሰጠው የቀብር ሥነ ሥርዓቱ በሚፈጸምበት ቦታ ቢሆንም ንግግሩን ለማቅረብ የሚቻልባቸው ሌሎች አማራጮችም አሉ። ለምሳሌ ያህል የቀብሩ ንግግር በቤት፣ በግቢ ወይም በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ከተሰጠ በኋላ በቀብር ቦታው ንግግር ሳይሰጥ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ሊፈጸም ይችላል። በመቃብሩ አካባቢ ንግግር የሚሰጥ ከሆነ ቀደም ብሎ እቅድ ማውጣት አስፈላጊ ይሆናል። ይህ ሁኔታ በአብዛኛው የሚወሰነው በሟቹ ቤተሰቦች ምርጫ ስለሆነ ፍላጎታቸውን ወይም መደረግ ያለበትን ነገር ለዘመዶቻቸውና ለወዳጆቻቸው ሊያሳውቁ ይችላሉ።

አንድ ክርስቲያን ቤተሰብ በ1 ቆ⁠ሮንቶስ 14:​33 እና 10:​31 ላይ የሚገኙትን ሁሉም ነገር በአገባብና በሥርዓት ይሁን እንዲሁም ሁሉንም ለአምላክ ክብር አድርጉት የሚሉትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮች ለመከተል እንደሚፈልጉ እሙን ነው። ስለዚህ የቀብር ንግግሩን የሚያቀርበው ወንድም ወይም ሌላ የጎለመሰ ወንድም በቀብሩ ቦታ የሚፈጸሙትን አጠቃላይ ሁኔታዎች እንዲቆጣጠር ማድረግ ይቻላል። እንዲሁም አንድ ሌላ ወንድም አስተናጋጅ ሆኖ እንዲሠራ መመደብ ይቻላል። በቀብሩ ቦታ ምን ያህል ሰዎች ሊመጡ እንደሚችሉ አስቀድሞ በመገመት ተጨማሪ አስተናጋጆች ሊመደቡ ይችላሉ። አንድ እንግዳ ሰው ችግር ለመፍጠር ቢሞክር የሟቹና የቤተሰቡ ፍላጎት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትንሣኤ የሚሰጠውን ተስፋ የሚያጎላ የቀብር ሥነ ሥርዓት በዚያ ቦታ እንዲካሄድ እንደሆነና እርሱም ይህን ፍላጎታቸውን እንዲያከብርላቸው ሊጠየቅ ይችላል። አለበለዚያ ከዚያ ቦታ እንዲሄድ ሊጠየቅ ይችላል። ሌላው አማራጭ ደግሞ የቀብሩ ሥነ ሥርዓት ቀደም ብሎ ከተጠናቀቀ በኋላ አጽናኝ የሆነውን የቀብር ንግግር ለማዳመጥ የሚፈልጉትን ሰዎች ወደ ኋላ እንዲቀሩ መጋበዝ ነው። እነዚህ ጥቂት አማራጮች የቀብር ሥነ ሥርዓታችን አግባብ ባለው መንገድና ለይሖዋ ክብር በሚያመጣ መንገድ እንዲከናወን የሚያስችሉ ናቸው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ