የጥያቄ ሣጥን
◼ ከአገልግሎታችን ጋር በተያያዘ ከተቃራኒ ጾታ ጋር በምንሆንበት ጊዜ ምን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልገናል?
ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በአኗኗራቸው ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃን በጥብቅ ይከተላሉ ብለን የምንጠብቅበት በቂ ምክንያት አለን። ሆኖም የምንኖረው ርኩስና በሥነ ምግባር በኩል ልቅ በሆነ ዓለም ውስጥ ነው። ጥሩ ዓላማ ያለን ቢሆንም እንኳ ነቀፋ የሚያመጣ ነገር ከማምጣት ወይም ተገቢ ባልሆነ ድርጊት ከመካፈል እንድንርቅ ዘወትር ጠንቃቆች መሆን አለብን። ይህም አገልግሎት በምንሰማራበት ጊዜ ጥንቃቄ ማድረግንም ይጨምራል።
በመስክ አገልግሎት ላይ ለእውነት ልባዊ ፍላጎት ያላቸው የሚመስሉ ከእኛ ተቃራኒ ጾታ ያላቸው ሰዎች ዘወትር እናገኛለን። ለብቻችን ሆነን በር ስናንኳኳ በሩን ከከፈተልን ተቃራኒ ጾታ ካለው ሰው በቀር በቤት ውስጥ ሌላ ማንም ሰው ከሌለ ብዙውን ጊዜ ወደ ውስጥ ዘልቀን ከመግባት ይልቅ በር ላይ ሆነን ምሥክርነቱን ብንሰጥ የተሻለ ይሆናል። ያነጋገርነው ሰው ፍላጎት ካሳየ ሌላ አስፋፊ ይዘን ወይም ቤት ውስጥ ሌላ ሰው በሚኖርበት ጊዜ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ እንችላለን። ይህም የማይሆን ከሆነ ከቤቱ ባለቤት ጋር ተመሳሳይ ጾታ ያለው አስፋፊ በተመላልሶ መጠይቅ እንዲሄድ ማድረጉ ጥበብ ይሆናል። ይህ ተቃራኒ ጾታ ያለውን ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናትንም በተመለከተ የሚሠራ ይሆናል።— ማቴ. 10:16
በአገልግሎት አብሮን የሚያገለግል ሰው በምንመርጥበትም ጊዜ ጠንቃቆች መሆን ያስፈልገናል። አልፎ አልፎ ተቃራኒ ጾታ ካላቸው አስፋፊዎች ጋር አብሮ ማገልገል የሚቻል ቢሆንም ይህ የቡድን ምሥክርነት በሚሰጥበት ጊዜ ቢሆን ይመረጣል። በመሠረቱ በአገልግሎት ላይም ቢሆን የትዳር ጓደኛችን ካልሆነ ሰው ጋር ለብቻችን ረዘም ያለ ጊዜ ማሳለፉ ጥበብ አይደለም። ስለዚህ የአገልገሎት ቡድኑን የሚመራው ወንድም በአሥራዎቹ እድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶችን ጨምሮ አስፋፊዎችን ለአገልግሎት በሚመድብበት ጊዜ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ መጠቀም ይኖርበታል።
ዘወትር ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ኖሮን በመመላለስ ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች “በአንዳች ነገር ማሰናከያ ከቶ አንሰጥም።”— 2 ቆሮ. 6:3
◼ በወላጆቻቸው ቤት የሚኖሩ ያላገቡ ትልልቅ ልጆች ያሉባቸውን ቤተሰቦች ሊረዳ የሚችል ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር አለ?
በዓለም ዙሪያ በሚኖሩ በብዙ ሰዎች ዘንድ ትልልቅ ልጆች እስኪያገቡ ወይም ካገቡም በኋላ ቢሆን ከወላጆቻቸው ጋር መኖራቸው የተለመደና የሚጠበቅ ነገር ነው። ሥራ አጥነት በተስፋፋበትና ሌላ የመኖሪያ ቤት የማግኘት ችግር ባለበት ጊዜ ትልልቅ ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር አብረው እንዲኖሩ የበለጠ ይገደዳሉ። አንዳንድ ጊዜ ይህ ሁኔታ ግጭትና ውጥረት ይፈጥራል። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በተግባር ላይ በማዋልና የማሰብ ችሎታችንን በመጠቀም እንዲህ ያሉት ችግሮች በእጅጉ እንዲቀንሱ አሊያም ጨርሶ እንዲወገዱ ማድረግ ይቻላል።— መዝ. 119:105፤ ሮሜ 12:1
“አባትህንና እናትህን አክብር” ለሚለው ትእዛዝ ምንም ዓይነት የእድሜ ገደብ የለውም። (ማቴ. 19:19) ትልልቅ ልጆች ለብቻቸው የሚኖሩም ይሁኑ ወይም ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲህ ያለውን አክብሮት ለወላጆቻቸው መስጠት ይኖርባቸዋል። ወላጆች ‘ያረጁም እንኳን ቢሆን’ ይህ ዓይነቱ አክብሮት መሰጠት እንዳለበት ይገልጻል። (ምሳሌ 6:20፤ 23:22) ወላጆች ለልጆቻቸው ከፍተኛ ፍቅራዊ እንክብካቤ ሲያደርጉ ቆይተዋል፤ አሁንም ለልጆቻቸው ልዩ ትኩረት ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ። ይሖዋ ቤተሰብን የሚያስተዳድር የራስነት ዝግጅት በማድረግ መሠረታዊ ሥርዓት አውጥቷል። እርሱም አባት ነው። (1 ጢሞ. 3:4) እያንዳንዱ ሰው ሥራ መሥራትና ቁሳቁሶች ማቅረብ ሊጠይቅበት የሚችል ቢሆንም አምላክ ያወጣው ዝግጅት ከሁሉ የተሻለና በቤት ውስጥ ሰላምና ሥርዓት እንዲጠበቅ እንደሚያደርግ እርግጠኞች ነን። አንድ የጎለመሰ ትልቅ ልጅ በወላጆቹ ቤት የሚኖር ቢሆን እንኳን የተወሰኑ መመሪያዎችና ግዴታዎች ልክ በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት ተቋሞች ወይም በሌሎች መኖሪያ ቤቶች ውስጥ እንደሚያስፈልጉ ሁሉ በቤት ውስጥም አስፈላጊና ተገቢ እንደሆኑ ይገነዘባል።
ስለዚህ በቤት ውስጥ የሚኖሩ ወጣት ትልልቅ ልጆች ታጋሽና ለማማረር ችኩል ባለመሆን ጠቢብ መሆናቸውን ለማሳየት ይችላሉ። እንዲያውም መጠነኛ ገቢ ካላቸው ለቤት ወጪ በመስጠት እርዳታ ቢያበረክቱ ተገቢ ነው። እንዲህ በማድረግ በቤት ውስጥ ያለውን የሥራ ጫና አብረው ሊሸከሙ ይችላሉ። (ገላ. 5:22, 23፤ 2 ተሰ. 3:10፤ 1 ጢሞ. 6:11, 18፤ ያዕ. 3:3) ወጣትነትህን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት የተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 10 እና ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 2 ጠቃሚ ሐሳቦችን ይዘዋል። ከወላጆቻቸው ጋር አሁንም አብረው የሚኖሩ ትልልቅ ልጆች ቢከልሷቸው ጠቃሚ ሐሳቦች ያገኛሉ።
ብዙ ክርስቲያን ትልልቅ ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር አብረው በመኖር ረገድ ተሳክቶላቸዋል። ሆኖም አንዳንዶች ሁኔታው አስቸጋሪ ስለሆነባቸው ወደ ሌላ አገር መሄድ ወይም ማግባት ችግሮቻቸውን የሚያቃልልላቸው ሆኖ ተሰምቷቸዋል። ይሁን እንጂ ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች የተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 7 ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው ከቅርብ ዘመዶቹ ጋር ተስማምቶ መኖር ካልቻለ ከሌሎች ሰዎች ጋርም ተስማምቶ መኖር እንደማይችል ይጠቁማል። ስለዚህ እርሱ ወይም እርሷ ከራሳቸው ቤተሰቦች ጋር ጥሩ የተቀራረበ ግንኙነት መመሥረትን እንዲማሩ ይመክራል። ይህም ከጊዜ በኋላ የተሳካ ቤተሰብ ለማስገኘት ሥልጠና የሚሰጥ ይሆናል። ይህን መንገድ ከመከተል ይልቅ በችኮላ ወደ ሌላ አገር የሄዱ ወይም ጋብቻ የመሠረቱ አንዳንድ ሰዎች የኋላ ኋላ ጸጸት ውስጥ ይገባሉ።— ምሳሌ 14:15
እርግጥ ነው በዚህ ሁኔታ ሥር ላሉ ወላጆች የሚሆን ምክርም አለ። ወላጆች ልጆቻቸውን እንዳያስቆጧቸው ወይም እንዳያበሳጯቸው ቅዱሳን ጽሑፎች በጥብቅ ያሳስባሉ። ይህም በእድሜ የገፉ ትልልቅ ልጆቻቸውንም ያጠቃልላል። (ኤፌ. 6:4፤ ቆላ. 3:21) ምክንያታዊ የሆኑ ወላጆች በዕድሜ ትልልቅ የሆኑ ልጆቻቸው አሁንም ገና ሕፃናት ወይም ትንንሽ ልጆች እንዳልሆኑ ይገነዘባሉ። ወላጆች ቀደም ሲል የነበራቸው የተንከባካቢነት ሥራ በምክር ሰጪነት መተካት ይኖርበታል። (ምንም እንኳን ልጁ በትምህርት ደረጃውና በዓለም ባካበተው እውቀት ከወላጆቹ የላቀ ቢሆንም የወላጆች እድሜና ተሞክሮ ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠው ነው።) አንድ ትልቅ ልጅ የሚያደርጋቸው አንዳንድ ውሳኔዎች ምንም እንኳ ትልቅ ሰው የሚያደርገውን ውሳኔ ያክል ጥበብ የተሞሉ ባይሆኑም ትልልቅ ልጆች የተወሰነ የራሳቸው ነፃነት እንደሚፈልጉ ወላጆች መገንዘብ ይኖርባቸዋል። በየካቲት 8, 1983 የወጣው የእንግሊዝኛ ንቁ! መጽሔት ከዚህ ጋር ተዛማጅነት ያለው ትምህርት ይዞ ወጥቷል። ገጽ 8 ላይ አንድ ወላጅ የሰጠውን አስተያየት በመጥቀስ እንዲህ ይላል:- “በግል ምርጫቸው ውስጥ ጣልቃ አልገባም። . . . ይሁን እንጂ ከልጆቼ መካከል አንዱ በመንፈሳዊ ወይም በሥነ ምግባራዊ አደጋ ላይ ሊጥለው የሚችል አካሄድ ቢከተል አባታቸው እንደመሆኔ መጠን በግልጽ እመክራቸዋለሁ።” ይህ ከተገቢው በላይ ቁጥጥር የማድረግ ዝንባሌ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ለወጣቶች ካለን አክብሮት የተነሳ ነው። ስለዚህ ወላጆች ተገቢ በሆኑ ጉዳዮች ወይም ሁኔታዎች አሳቢነት በማሳየት ጥበበኛ መሆናቸውን ሊያሳዩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ በትልልቅ ልጆች ሕይወት ውስጥ ጣልቃ መግባት የለባቸውም።
በወላጆችና ባደጉ ልጆቻቸው መካከል የሚደረገው አክብሮት የሞላበት ጥሩ ውይይት ብዙ ችግሮችን ማስወገድና ታምቆ የቆየ ቁጣ አንድ ቀን በድንገት እንዲገነፍል ከሚያደርግ ሁኔታ መራቅ ይቻላል። ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ ቆላስይስ 3:12-14 ላይ የሰፈሩትን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ ምክሮች ቢሠሩባቸው “ስምም ሆነው በኅብረት” እንደሚኖሩ የተረጋገጠ ነው።— መዝ. 133:1 NW