መጽሔት ለማበርከት የሚያስችል አቀራረብ መዘጋጀት የሚቻልበት መንገድ
1 በዛሬው ጊዜ ያሉትን ችግሮች ተቋቁሞ መኖር እንዴት እንደሚቻል ለአንድ ሰው መግለጽ ብትፈልግ መሣሪያ አድርገህ የምትጠቀምበት ጽሑፍ ምንድን ነው? በፖለቲካ ጉዳይ ገለልተኝነትህን እንደያዝህና አንዱን ዘር ከሌላው ሳታስበልጥ በዛሬው ጊዜ ካሉት ክስተቶች በስተጀርባ ያለውን ትክክለኛ ትርጉም ለማስረዳት ብትፈልግ ምን ነገር ሊረዳህ ይችላል? አንድ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ የሆኑትን በዓለም ላይ ያሉ ክስተቶች ነቅቶ እንዲከታተል ለመርዳት ብትፈልግ በቀላሉ የትኛውን ጽሑፍ ልትጠቅስለት ትችላለህ? በአሁኑ ጊዜ ሰዎች በመግዛት ላይ ባለው ንጉሥ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እምነት እንዲኖራቸው የሚያበረታታና ይሖዋ አምላክ የአጽናፈ ዓለሙ የበላይ ገዥ መሆኑን ጎላ አድርጎ የሚገልጽ አንድ ሐሳብ መስጠት ብትፈልግ ከሁሉ የተሻለ ሆኖ የምታገኘው ጽሑፍ የትኛው ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልሱ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ናቸው የሚል ነው።
2 በእርግጥም በዛሬው ጊዜ የሰው ዘር ማንበብ የሚኖርበት ቁም ነገር በእነዚህ ሁለት መጽሔቶች ውስጥ ይገኛል። በእነዚህ መጽሔቶች ላይ ጠንካራ እምነት አድሮብን፣ በጋለ ስሜትና በቅንዓት እያበረከትናቸው ነውን? ጊዜያችንን በጥበብ ለመጠቀም በአግባቡ እንዘጋጃለንን? አቀራረባችንን ለማሻሻል እንችላለንን?
3 አስቀድሞ መዘጋጀት፦ እያንዳንዱ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! እትም የያዘውን ትምህርት ወዲያውኑ ለማወቅ የሚረዳን አንዱ የተሻለ ዘዴ በገጽ 2 ላይ ያለውን “በዚህ እትም ውስጥ” የሚለውን ክፍል ማንበብ ነው። ብዙ አስፋፊዎች ይህን አጭር መግለጫ ብቻ በማንበብ የትኛውን ሐሳብ ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ጥሩ ፍንጭ ያገኛሉ። ሆኖም ይህ የመጀመሪያ እርምጃ ብቻ ነው።
4 ቀጥሎም የእያንዳንዱን እትም ገጾች ገልጠህ እየተመለከትህ ርዕሶቹንና ንዑስ ርዕሶቹን አንብብ። ከዚያም እነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች በአገልግሎት ክልሉ ውስጥ የሚገኙትን የየትኞቹን ሰዎች ትኩረት ሊስቡ እንደሚችሉ ቆም ብለህ አስብ። ከዚህ በኋላ መጽሔቱ ውስጥ ያሉትን ትምህርቶች አንድ በአንድ እያነበብክ የሰዎችን ፍላጎት ለመቀስቀስ የሚያስችሉ የመነጋገሪያ ነጥቦችን ምልክት አድርግባቸው። አልፎ አልፎ ጽሑፉ ራሱ ዋና ዋናዎቹ ነጥቦች ጋደል ብለው ወይም ጎላ ብለው በተጻፉ ፊደላት ተለይተው እንዲታዩ ያደርጋል። መጽሔቱን ለሰዎች በምታስተዋውቅበት ጊዜ በእነዚህ ነጥቦች ተጠቀም።
5 እያንዳንዱን መጽሔት በምታነብበት ጊዜ በአገልግሎት ክልሉ ውስጥ የምታገኛቸውን የተለያዩ ሰዎች የትኞቹ ርዕሶች እንደሚማርኳቸው ለይተህ እወቅ። አንዳንዶቹ ርዕሶች አንድን የኅብረተሰብ ክፍል በቀጥታ የሚመለከቱ ናቸው። ከዚህ ቀደም ነጠላ ወላጆችን፣ ውርጃን፣ የኑክሊየር ጦርነትን፣ በሕፃናት ላይ የሚፈጸመውን በፆታ የማስነወር ድርጊትና ድንገተኛ አደጋዎችን የሚመለከቱ እንዲሁም በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ሌሎች ብዙ ርዕሶች ወጥተዋል። ስለዚህ የተለያየ ርዕስ ያላቸውን ጽሑፎች በምናነብበት ጊዜ በክልላችን ውስጥ ላሉት ሰዎች ይበልጥ የሚስማማውን ነጥብ ፈልገን ምልክት እናድርግበት።
6 ወደ መስክ አገልግሎት በምንወጣበት ጊዜ፦ ወደ መስክ አገልግሎት እስካልወጣን ድረስ አስቀድመን ያደረግነው ዝግጅት በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች ላይ ያሉት ትምህርቶች የሚያስፈልጓቸውን ሰዎች ሊረዳቸው አይችልም። እነዚህን መጽሔቶች የምናደንቅ ከሆነ መጽሔት በማበርከቱ ሥራ ተሳትፎ ማድረግ እንድንችል ዘወትር ጊዜ እንመድባለን። በየወሩ የመስክ አገልግሎት ዝግጅቶችን ለመደገፍ ልዩ ጥረት አድርጉ። በተቻለ መጠን የምታበረክቱትን የመጽሔት መጠን ከፍ የማድረግ ግብ ይኑራችሁ። እያንዳንዱ እትም የያዘውን መልእክት የማወቅን አስፈላጊነት አትዘንጉ። በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መጽሔቶቹን ለማበርከት አታመንቱ። አቅማችሁ በሚፈቅደው መጠን የእውነትን ቃል በትክክል ለመጠቀም እንድትችሉ ጥሩ ዝግጅት አድርጉ።—2 ጢሞ. 2:15 NW