በየዕለቱ ስለ ይሖዋ ተናገሩ
1 ከልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ስለሚናገር ሰዎች ከልብ ስለሚወዱት ነገር ማውራት ያስደስታቸዋል። (ሉቃስ 6:45) ከልብ የምንወደው ነገር ምንድን ነው? መዝሙራዊው እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ምላሴ ጽድቅህን ሁልጊዜም ምስጋናህን ይናገራል።” (መዝ. 35:28) መዝሙራዊው ለይሖዋ ጥልቅ አድናቆት ስለነበረው ስለ አምላክ መናገርንና ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ እርሱን ማወደስን እንደ ውድ መብት ቆጥሮታል። መዝሙራዊው ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ስለነበረው የሚደሰትባቸው ብዙ መልካም ነገሮች ነበሩ። (መዝ. 35:9) የእርሱን ጥሩ ምሳሌ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?
2 በቤታችሁ ውስጥ ስለ ይሖዋ ተናገሩ፦ በቤተሰብ ክልል ውስጥ የየዕለቱ ዋና የመነጋገሪያ ርዕስ ይሖዋ መሆን ይኖርበታል። ለይሖዋ ጠንካራ ፍቅር ያላቸው ወላጆች በማንኛውም እንቅስቃሴያቸው ስለ እርሱ ሳይናገሩ አያልፉም። (ዘዳ. 6:5-7) እንደዚህ በሚያደርጉበት ጊዜ ልጆቹ፣ አባታቸውና እናታቸው ከሚያምኑት ነገር ጋር ተስማምተው እንደሚኖሩና የአምላክን ሕግ ከፍ አድርገው እንደሚይዙ ይመለከታሉ። ከዚህም የተነሳ ልጆች የቤተሰቡን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወላጆች በእርግጥ ለአምላክ ያደሩ መሆናቸውን የሚያሳይ ነገር አድርገው ይመለከቱታል።—2 ጴጥ. 3:11
3 ከወንድሞቻችሁ ጋር ስለ ይሖዋ ተነጋገሩ፦ በየሳምንቱ በምናደርገው ቲኦክራሲያዊ ፕሮግራም አማካኝነት ልባችንንና አእምሮአችንን መንፈሳዊ ምግብ ለመመገብ ብዙ አጋጣሚዎች እናገኛለን። በመሆኑም ለሌሎች የምናወራው የሚያንጽ ነገር በጭራሽ አናጣም። (ሉቃስ 6:45) ከግል ጥናትህ ያገኘኸው ወይም ከሳምንታዊው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህ ውስጥ ይበልጥ የነካህ ነጥብ አለን? ይህን ነጥብ ለወንድሞችህ ማካፈልህ ለይሖዋ ያላቸው ፍቅር እንዲያድግ አስተዋጽኦ ያደርጋል።—መዝ. 35:18፤ ዕብ. 10:24
4 ለሌሎች ሰዎች ስለ ይሖዋ ተናገሩ፦ በየቀኑ ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ማለትም በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤትና ከማያምኑ የቤተሰብ አባሎቻችን ጋር ስንሆን በሕይወታችን ውስጥ ትኩረት የምንሰጠው ነገር ለይሖዋ ስለ መመስከር መሆኑ በግልጽ መታየት አለበት። ንግግራችን በዓለም ዘንድ በሚዘወተሩ የብልግናና ሻካራ ቃላት እንዲበከል ከመፍቀድ ይልቅ አምላክን የሚያወድስ መሆን ይኖርበታል። ይሖዋ እንድንሰብክ ያዘዘንን ምሥራች በየዕለቱ ባገኛችሁት አጋጣሚ ሁሉ ለሰዎች ተናገሩ።—ሥራ 5:42፤ ቆላ. 4:6
5 እውነተኛ የይሖዋ አምላኪዎች እንደመሆናችን መጠን ተወዳዳሪ ስለሌለው አምላካችን ስለ ይሖዋ ለመናገር አጋጣሚዎችን ሁሉ ለመጠቀም ንቁ እንሁን።—መዝ. 106:47