የሐምሌ የአገልግሎት ስብሰባዎች
ሰኔ 29 የሚጀምር ሳምንት
መዝሙር 49 (114)
10 ደቂቃ፦ የጉባኤ ማስታወቂያዎች። ሁሉም የሰኔ ወር ሪፖርት እንዲመልሱ አሳስብ።
20 ደቂቃ፦ “ጎረቤቶቻችን ምሥራቹን መስማት ያስፈልጋቸዋል።” ሁለት ወይም ሦስት ጥሩ ችሎታ ያላቸው አስፋፊዎች በጉባኤው ካሉ ብሮሹሮች ጥቂቶቹን በመጠቀም የቀረቡትን ሐሳቦች እንዲከልሱ ዝግጅት አድርግ። አቀራረቦቹ በጉባኤው ክልል ውስጥ ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉበትን ምክንያት አብራራ። አምላክ ከእኛ የሚፈልገው በተባለው ብሮሹር ወይም እውቀት በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች የማስጀመርን ግብ አጉላ። መጀመሪያ ሲገናኙ ከዚያም ተመላልሶ መጠየቅ ሲደረግና ጥናት እንዲጀመር ሐሳብ ሲያቀርብ የሚያሳይ ሠርቶ ማሳያ አቅርብ። እባክህ፣ በመንግሥት አገልግሎታችን የመጨረሻ ገጽ ላይ ያሉት አቀራረቦች መስክ አገልግሎት ላይ ሰዎችን ስናነጋግር መጀመሪያ ላይ መጥቀስ ያለብንን ሐሳቦች እንዳልያዙ ግለጽ። መጀመሪያ ላይ ወዳጃዊ ሰላምታ መቅደም እንዳለበት የታወቀ ነው። በብዙዎቹ አጋጣሚዎች ስማችንንና የምንኖርበትን አካባቢ መናገሩ ተገቢ ሆኖ እናገኘው ይሆናል። አንዳንድ ሰዎችን ስናነጋግር መልእክቱን ከመናገራችን በፊት ስለ አየሩ ሁኔታ፣ በአካባቢው ስለተከሰተ ጉዳይ ወይም ስለ ቀኑ ውሎ አንዳንድ ጠቅለል ያሉ አስተያየቶችን መሰንዘር እንችላለን። በአካባቢው የተለመደውን ሰላምታ ጥቀስና ተስማሚ የሆነ መግቢያ ተናገር።
15 ደቂቃ፦ “ፍቅር ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ ነው።” በታኅሣሥ 15, 1994 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 13 እና 14 አንቀጽ 1-7 ላይ ተመስርቶ በሽማግሌ የሚቀርብ ንግግር። ዓለም የሚያመጣቸው ማዘናጊያዎችና የሚያሳድራቸው ተጽዕኖዎች በበዙበት በዚህ ወቅት በተለያዩ አጋጣሚዎች ከወንድሞቻችን ጋር ጊዜ ማሳለፍንና አንዳችን ለሌላው ትኩረት የመስጠትን አስፈላጊነት ይገልጻል።
መዝሙር 28 (58) እና የመደምደሚያ ጸሎት።
ሐምሌ 6 የሚጀምር ሳምንት
መዝሙር 88 (200)
10 ደቂቃ፦ የጉባኤ ማስታወቂያዎች። ከመንግሥት አገልግሎታችን የተመረጡ ማስታወቂያዎች። በአገሪቱና በጉባኤው የሚያዝያ ወር የመስክ አገልግሎት ሪፖርት ላይ ሐሳብ ስጥ። ብሮሹሮች ማበርከትን በተመለከተ አንድ ገንቢ ተሞክሮ ተናገር። ገጽ 12 ላይ ካሉት ብሮሹር ለማበርከት ከሚያስችሉ አቀራረቦች አንዱን ተናገር። ቲኦክራሲያዊ ዜናዎች።
20 ደቂቃ፦ ለጉባኤው እንደሚያስፈልግ ተጠቀሙበት።
15 ደቂቃ፦ “ዘወትር በስብሰባዎች መገኘት ምንኛ መልካም ነው!” ጥያቄና መልስ። ወጣቶች ዘወትር በስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ ለማበረታታት ከሰኔ 8, 1988 ንቁ! (የእንግሊዝኛ) ገጽ 19-21 ላይ ተጨማሪ ሐሳቦች አቅርብ።
መዝሙር 29 (62) እና የመደምደሚያ ጸሎት።
ሐምሌ 13 የሚጀምር ሳምንት
መዝሙር 95 (213)
10 ደቂቃ፦ የጉባኤ ማስታወቂያዎች። የሒሳብ ሪፖርት። አምስት ቅዳሜና እሁዶች ባሉት የነሐሴ ወር ሁሉም በረዳት አቅኚነት ማገልገልን ትኩረት ሰጥተው እንዲያስቡበት አበረታታቸው።
12 ደቂቃ፦ “የሚያስፈልገው አንድ ነገር ብቻ ነው።” ከአድማጮች ጋር የሚደረግ ውይይት።
23 ደቂቃ፦ “ከቤት ወደ ቤት የሚደረገውን አገልግሎት ችላ ማለት የሌለብን ለምንድን ነው?” የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ በጥያቄና መልስ ያቀርበዋል። እባክህ፣ ከጉባኤያችሁ ክልል ውስጥ ምን ያህሉ እንደተሸፈነ ከገለጽክ በኋላ በሕዝቅኤል 3:18, 19 እና በ1 ቆሮ. 9:16, 17 መሠረት ያለብንን ኃላፊነት ጎላ አድርገህ ግለጽ። በአገልግሎት መጽናታችን ተቃውሞዎችን እንዴት ሊቀንስ እንደሚችል ግለጽ። ከዚያም አንድ ጥሩ አንባቢ የሆነ ወንድም ከ7/94 የመንግሥት አገልግሎታችን ገጽ 1 ላይ አንቀጽ 2-5ን እና ከጥር 15, 1991 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 11 አንቀጽ 3ና 6ን፣ ከገጽ 12 አንቀጽ 7ና 8ን እንዲሁም ከገጽ 13 አንቀጽ 11ና 12ን እንዲያነብ አድርግና ነጥቦቹን አብራራ። ከዚያም አደገኛ በሆኑ ክልሎች ውስጥ ስናገለግል ልንወስዳቸው ስለሚገቡ ጥንቃቄዎች አንዳንድ ነጥቦች አክል። ለምሳሌ ያህል አራት ሆነው በቡድን መልክ (ምናልባትም ሁለት ወንድሞችና ሁለት እህቶች) ቅርብ ለቅርብ ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ።
መዝሙር 43 (98) እና የመደምደሚያ ጸሎት።
ሐምሌ 20 የሚጀምር ሳምንት
መዝሙር 8 (21)
8 ደቂቃ፦ የጉባኤ ማስታወቂያዎች። “ወደ 6,000 ምን ያህል እንጠጋ ይሆን?” በሚል ርዕስ የቀረበውን ሣጥን ከልስ።
12 ደቂቃ፦ “በረከት ሊያስገኝ የሚችል ጉብኝት።” በሁለት ሽማግሌዎች መካከል የሚደረግ ውይይት። በመስከረም 15, 1993 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 20-3 ላይ ባለው መሠረት የእረኝነት ሥራ ዓላማዎችን ግለጹ። ጉባኤው ሽማግሌዎች የሚያደርጉትን ጉብኝት በጉጉት እንዲጠባበቅ ሞቅ ባለ መንፈስ አበረታቱ።
25 ደቂቃ፦ “አቅኚ መሆን ትችላለህን?” (አንቀጽ 1-14) የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ ሁሉም የዘወትር አቅኚነትን በቁም ነገር እንዲያስቡበት የሚያበረታታ አጠር ያለ የመክፈቻ ንግግር ያቀርባል። ከዚያም በ1998 የዓመት መጽሐፍ ገጽ 104-5 ላይ ከሚገኘው “ግለት የተሞላበት የአቅኚነት መንፈስ” ከሚለው ርዕስ አንዳንድ ሐሳቦች በመጨመር የመጀመሪያውን ጥያቄ ያብራራል። የአቅኚነት ተሞክሮ ያላቸው ሁለት ወይም ሦስት የጉባኤው አባላት ሁለተኛውን ጥያቄ አብረውት ለመወያየት ወደ መድረኩ ይወጣሉ። አንድ ሰው አስፈላጊ የሆኑ ቁሳዊ ነገሮች ሳይጓደሉበት እንዴት አቅኚ ሆኖ ማገልገል እንደሚችል ተግባራዊና ትክክለኛ አስተያየት ይሰጣሉ። ከዚህ በመቀጠል ሦስተኛውን ጥያቄ ለመወያየት ሁለት ወላጆች ከእነሱ ጋር ይቀላቀላሉ። ወጣቶች የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ሙያ አድርጎ መያዝን በተመለከተ በቁም ነገር ሊያስቡ የሚገባው ለምን እንደሆነ የሚጠቁሙ ገንቢ ምክንያቶች ይጠቅሳሉ። የቀሩት ጥያቄዎች የሚሸፈኑት በሚቀጥለው ሳምንት ስለሆነ ሁሉም በሚቀጥለው ሳምንት በሚደረገው የአገልግሎት ስብሰባ ላይ እንዲገኙ አበረታታ።
መዝሙር 31 (67) እና የመደምደሚያ ጸሎት።
ሐምሌ 27 የሚጀምር ሳምንት
መዝሙር 66 (155)
5 ደቂቃ፦ የጉባኤ ማስታወቂያዎች። ሁሉም የሐምሌ ወር ሪፖርት እንዲመልሱ አሳስብ። በነሐሴ ወር በመጀመሪያዎቹ ቅዳሜና እሁድ አገልግሎትን በተመለከተ የተደረጉትን ዝግጅቶች አስታውቅና ሁሉም እንዲሳተፉ አበረታታ። እባክህ፣ “ታምሜ ጠይቃችሁኛልና” በሚለው የማቴዎስ 25:36 ጥቅስ ላይ ሐሳብ ስጥ። ጊዜያችን የተጣበበ ቢሆንም የታመሙ ወንድሞቻችንን ለመርዳት፣ ለመጠየቅና ለማበረታታት ጊዜ የመመደብን አስፈላጊነት ግለጽ። ከኅዳር 1, 1994 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 20-1 አንቀጽ 16-17 እና ከነሐሴ 1, 1994 ገጽ 29-30 እንዲሁም ከሰኔ 22, 1995 ንቁ! (የእንግሊዝኛ) ገጽ 16 አንቀጽ 3 ላይ አንዳንድ ሐሳቦች ጨምረህ አቅርብ።
30 ደቂቃ፦ “አቅኚ መሆን ትችላለህን?” (አንቀጽ 15-25) አንድ ሽማግሌ በንግግርና በውይይት ያቀርበዋል። በአራተኛውና በአምስተኛው ጥያቄ ላይ ልባዊ ስሜታቸውን በመግለጽ መልስ እንዲሰጡ አቅኚዎችንና ከዚህ ቀደም በአቅኚነት የተካፈሉትን አስቀድመህ አዘጋጅ። ሊሠሩ የሚችሉ ውጤታማ ሳምንታዊ የአገልግሎት ፕሮግራም ምሳሌዎችን በመጥቀስ ጥሩ ፕሮግራም የማውጣትንና በጥብቅ የመከተልን አስፈላጊነት ጎላ አድርገው ይገልጻሉ። ሽማግሌው ቀስቃሽ በሆነ መንገድ የስድስተኛውን ጥያቄ መልስ በንግግር በማቅረብ ይደመድማል። መስከረም 1 ላይ የሚጀምረው የአገልግሎት ዓመት አዳዲስ አቅኚዎች የሙሉ ጊዜ አገልግሎታቸውን ለመጀመር ጥሩ አጋጣሚ ይሆንላቸዋል። የማመልከቻ ቅጹን ከጉባኤው የአገልግሎት ኮሚቴ አባላት ማግኘት ይቻላል።
መዝሙር 69 (160) እና የመደምደሚያ ጸሎት።