አስቀድሞ መዘጋጀት ደስታ ያስገኛል
1 በመስክ አገልግሎት መካፈላችን ከፍተኛ ደስታ ያስገኝልናል። (መዝ. 89:15, 16) እርግጥ ይህን ደስታ ሙሉ በሙሉ ለማጣጣም የሚያስችለው ቁልፍ ዝግጅት ነው። ይበልጥ በተዘጋጀን መጠን የበለጠ ማከናወን እንችላለን የበለጠ ካከናወን ደግሞ ደስታችን የዚያኑ ያህል ይጨምራል።
2 ያሉትን መሣሪያዎች ተጠቀሙባቸው፦ ዝግጅታችሁን በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የወጡትን ክፍሎች በማንበብና በመመርመር ጀምሩ። አብዛኛውን ጊዜ የመንግሥቱን መልእክት ቀላልና ውጤታማ በሆነ መንገድ እንድታቀርቡ ለመርዳት ተብለው የተዘጋጁ በሚገባ የታሰበባቸው አቀራረቦችን ይዞ ይወጣል። ብዙ ጊዜ የሚያጋጥሙ የተቃውሞ ሐሳቦችን እንዴት ማለፍ እንደምትችሉ የሚጠቁሙ ምሳሌዎችን ታገኛላችሁ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የማስጀመር ግብ በመያዝ እንዴት ውጤታማ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ እንደሚቻል የሚያሳዩ ቀጥተኛ ሐሳቦች ይቀርባሉ። እነዚህን ሐሳቦች ለመጠቀም እንደሚመቻችሁ ልትለውጧቸው ትችላላችሁ። ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ መግቢያዎችን እንዲሁም ውይይት ለማስቆም ለሚሰነዘሩ ሐሳቦች የምንሰጠውን መልስ የያዘው ማመራመር መጽሐፍ አለላችሁ። ይህም የሚያጋጥሟችሁን ብዙዎቹን ሁኔታዎች ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንድትወጡ ይረዳችኋል።
3 የምታበረክቱትን ጽሑፍ ተመልከቱና ለምታነጋግሩት ሰው የምታሳዩት አንድ ወይም ሁለት ፍላጎት የሚቀሰቅሱ ነጥቦች ምረጡ። የሰማችሁት ወይም ያነበባችሁት አንድ ስሜት ቀስቃሽ ዜና ውይይት ለመጀመር ያስችላችሁ ይሆናል። ሊያጋጥሟችሁ የሚችሉትን የተለመዱ የተቃውሞ ሐሳቦች ከግምት ውስጥ በማስገባት እንዴት ምላሽ መስጠት እንደምትችሉ ጥቂት አስቡበት። ከዚያም ጥቂት ደቂቃ ወስዳችሁ በሩን ካንኳኳችሁ በኋላ ምን እንደምትሉ ተለማመዱ።
4 በሁሉም የአገልግሎት ስብሰባዎች ላይ ተገኙ፦ በአገልግሎት ስብሰባ ወቅት በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የወጡት አቀራረቦች ውይይት ሲደረግባቸውና በሠርቶ ማሳያ ሲቀርቡ በጥሞና ተከታተሉ። በአቀራረቤ ውስጥ ልጨምረው እችላለሁ ብላችሁ የምታስቡትን ነጥብ ልብ በሉ። በአገልግሎት ካጋጠሟችሁ የተለመዱ ሁኔታዎች መካከል አንዳንዶቹን በማስታወስ እንዴት የበለጠ ውጤታማ በሆነ መንገድ መመሥከር እንደምትችሉ አስቡ። ከስብሰባ በፊትም ሆነ በኋላ ስለ እነዚህ ነገሮች ከሌሎች አስፋፊዎች ጋር ተነጋገሩ።
5 ‘ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጃችሁ’ ከሆናችሁ ሌሎች የሕይወትን መንገድ እንዲከተሉ በመርዳት ከፍተኛ ደስታና ስኬት በማግኘት እንደምትባረኩ እርግጠኛ መሆን ትችላላችሁ።—2 ጢሞ. 2:21