ውብ የሆነውን የይሖዋ ስም ከፍ አድርጋችሁ ተመልከቱ
1 ሰይጣን የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ኃጢአት እንዲሠሩ ባደረገበት ወቅት የአምላክን ስም ያጎደፈ ሲሆን ይሖዋ አዳምን እንደዋሸው አድርጎ ተናግሯል። (ዘፍ. 3:1-5) መለኮታዊው ስም አምላክ ቃሉን ለመፈጸም ካለው ችሎታ ጋር የተያያዘ በመሆኑ የሰይጣን አባባል የለየለት ስም ማጥፋት ነበር። ይሖዋ መለኮታዊ ዓላማውን ደረጃ በደረጃ በመፈጸም ስሙ ከተከመረበት ነቀፋ እንዲነጻና ውብ እንዲሆን አድርጓል።—ኢሳ. 63:12-14
2 ይሖዋ ‘በስሙ የጠራን’ እኛን ነው። (ሥራ 15:14, 16, 17) ይህ ደግሞ ስለ ስሙ መቀደስ የሚሰማንን ስሜት ለመግለጽ የሚያስችል አጋጣሚ ይሰጠናል። የይሖዋ ስም ጥሩነት፣ ደግነት፣ ፍቅር፣ ምሕረትና ጽድቅ ያለበትን ነገር ሁሉ የሚወክል በመሆኑ በእርግጥም ውብ ነው። ክብራማ የሆነው የአምላክ ስም ያለው ግርማ በአድናቆት እንድንሞላ ያደርገናል። (መዝ. 8:1፤ 99:3፤ 148:13) ምን ለማድረግ መነሳሳት ይኖርብናል?
3 የአምላክን ስም ቀድሱ፦ የአምላክ ስም ምን ጊዜም ቅዱስ ነው። ይሁን እንጂ በንጹሕ አኗኗራችንና በመንግሥቱ የስብከት ሥራችን ለአምላክ ስም የላቀ ግምት እንዳለን ልናሳይ እንችላለን። እኛም “እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ስሙንም ጥሩ፤ በአሕዛብ መካከል ሥራውን አስታውቁ ስሙ ከፍ ያለ እንደሆነ ተናገሩ” እንበል። (ኢሳ. 12:4) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
4 የይሖዋን ስምና ስሙ የሚወክላቸውን ነገሮች ለማስታወቅ ያገኘነውን አጋጣሚ ሁሉ መጠቀም እንችላለን። መደበኛም ይሁን መደበኛ ባልሆነ መንገድ፣ ከቤት ወደ ቤትም ይሁን ከሱቅ ወደ ሱቅ፣ በመንገድ ላይም ሆነ በሌሎች ጊዜያት የምናከናውነው የስብከት ሥራ ይሖዋን ያስከብረዋል። ለማዳመጥ ፈቃደኛ የሆኑ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ስናገኝ ተመልሰን ሄደን ስለ ይሖዋ የበለጠ ልናስተምራቸው እንችል ዘንድ ቁርጥ ያለ ቀጠሮ መያዝ ይገባናል። ይህ ደግሞ የያዝናቸውን ቀጠሮዎች ማክበርና የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር በምናደርገው ጥረት መጽናት አለብን ማለት ነው። በየዓመቱ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የይሖዋን ውብ ስም ማወቅ፣ ማክበርና መቀደስ መቻላቸው የሚያስደስት ነው።
5 የአምላክን ስም በመቀደሱ ሥራ የምናከናውነው የሙሉ ልብ ተሳትፎ ሰይጣን በኤደን ገነት ያስነሳውን አከራካሪ ጉዳይ በሚመለከት በየትኛው ወገን እንደቆምን በግልጽ ያሳያል። ይህ ልንሠራው ከምንችለው ሥራ ሁሉ የላቀና ክብራማ ነው። ውብ የሆነውን የይሖዋ ስም ከፍ አድርገን የምንመለከት እንዲሁም ስሙን በቅንዓት የምናወድስ እንሁን!—1 ዜና 29:13