አሁንስ አቅኚ መሆን ትችሉ ይሆን?
1 የ1999 የዓመት ጥቅሳችን በይሖዋ “የመዳን ቀን” ውስጥ እንደምንገኝ ያስታውሰናል። (2 ቆሮ. 6:2) ይሁን እንጂ በቅርቡ ይህ የይሖዋ የመዳን ቀን ያበቃና ‘የፍርድ ቀኑ’ ይጀምራል። (2 ጴጥ. 2:9) ይሖዋ የመዳንን አጋጣሚ ለሰው ዘር እንደዘረጋ ባለበት በአሁኑ ወቅት በየጊዜው ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ብዙ ሰዎች ምላሽ ሲሰጡ መመልከት እንዴት ያስደስታል!
2 የይሖዋ አገልጋዮች ጊዜው ከማለቁ በፊት ምላሽ የሚሰጡ ሰዎችን መፈለግ የሚጠይቀውን ተፈታታኝ ሁኔታ ለመጋፈጥ ቆርጠው ተነሥተዋል። ከዚህ የተነሣ ብዙ የመንግሥቱ አስፋፊዎች የአቅኚነት አገልግሎት ጀምረዋል። እናንተስ አሁን አቅኚ መሆን ትችሉ ይሆን? እንደዚህ ብለን የምንጠይቀው ለምንድን ነው?
3 የምስጋና መግለጫዎች፦ በጥር 1999 የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ እንደተገለጸው የዘወትርና ረዳት አቅኚዎች እንዲያሟሉ የሚጠበቅባቸው ሰዓት ተቀንሷል። የዘወትር አቅኚዎች አዲሱ የሰዓት ግባቸው ላይ ለመድረስ በየወሩ 70 ሰዓት በአገልግሎት በማሳለፍ በአንድ የአገልግሎት ዓመት 840 ሰዓት ማምጣት ይኖርባቸዋል። ረዳት አቅኚዎች ደግሞ በየወሩ በአገልግሎቱ 50 ሰዓት ያሳልፋሉ። እነዚህ ማሻሻያዎች በመደረጋቸው ምክንያት ከደረሱን ብዙ የምስጋና መግለጫዎች መካከል ጥቂቶቹ ከዚህ በታች ቀርበዋል:-
“ከሰማያዊው አባታችን የተገኘ ታላቅ ስጦታ ነው!”
“ይህ ዝግጅት በመደረጉ የተሰማኝን የደስታ፣ የፍቅርና የአመስጋኝነት ስሜት ለመግለጽ ቃል ያጥረኛል!”
“ይህ በቀላሉ ግባችን ላይ ለመድረስ ያስችለናል!”
“ብዙዎች የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን እንዲጀምሩና ይሖዋን በሰፊው ከማገልገል የሚገኘው በረከት ተካፋይ እንዲሆኑ ጸሎታችን ነው።”
4 የአምላክ የመዳን ቀን ወደሚያበቃበት ጊዜ እየተቃረብን ስንመጣ ይሖዋ ሕዝቦቹ ለመጨረሻ ጊዜ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ውዳሴውን እንዲያሰሙ እንደሚፈልግ ግልጽ ነው። የዚህ መልእክት ሥርጭት ስፋትና ጥራቱ የሚጨምረው:- (1) የማያቋርጥ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች እድገት በመኖሩና (2) እያንዳንዱ ሰው በመንግሥቱ ስብከት የተሻለ ነገር ለማድረግ ስለሚጥር ነው። ‘የሚያሳድገው’ ይሖዋ፣ መዳንን የተቀበሉ ሰዎች የሚያሳዩትን የፈቃደኝነት መንፈስ በመባረኩ በሁለቱም መስክ ቢሆን መልካም ውጤት ተገኝቷል።—1 ቆሮ. 3:6, 7፤ መዝ. 110:3 NW
5 ዓላማውን አትሳቱ፦ ጳውሎስ መሰል ክርስቲያኖችን “አብረንም እየሠራን የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ እንዳትቀበሉ [“ዓላማውን እንዳትስቱ፣” NW] ደግሞ እንለምናለን” በማለት አጥብቆ የመከራቸው ከይሖዋ የመዳን ቀን ጋር በተያያዘ ነበር። ይህ ጊዜ ማንኛውንም አጋጣሚ በመጠቀም ለሌሎች መዳን የምንሠራበት ‘የተወደደ ሰዓት’ መሆኑን ካስተዋልን “ዓላማውን አንስትም።” (2 ቆሮ. 6:1, 2) ጳውሎስ የተናገረው ነገር ዛሬ ይበልጥ አንገብጋቢ ሆኗል። ለይሖዋ ልባዊ ፍቅር ያላቸው ክርስቲያኖች እርሱ እንዲሠሩት ባዘዛቸው አገልግሎት የተቻላቸውን ያህል ሙሉ ተሳትፎ ማድረጉን እንደ ልዩ መብት ይቆጥሩታል። እናንተስ አሁን የዘወትር አቅኚ በመሆን በአገልግሎቱ የበለጠ መካፈል ትችሉ ይሆን?
6 ምክንያታዊ ግብ ነው፦ በእኛ የአገልግሎት መስክ ያሉትን የዘወትር አቅኚዎች ቁጥር እስከ መስከረም 1 ድረስ 600 ለማድረስ ግብ አውጥተናል። ይህ ምክንያታዊና ሊደረስበት የሚችል ግብ ነው ብለን እናምናለን። ይህን ያህል እርግጠኞች የሆንነው ለምንድን ነው? በመጋቢት 1997 እና በሚያዝያ 1998 ከ1,000 በላይ የሚሆኑ ወንድሞችና እህቶች በረዳት አቅኚነት አገልግለዋል። አብዛኞቹ 60 ሰዓት ሪፖርት አድርገዋል። ይህም አሁን የዘወትር አቅኚዎች እንዲያሟሉት ከሚጠበቅባቸው ሰዓት የሚያንሰው በ10 ብቻ ነው! በረዳት አቅኚነት ካገለገሉት ከእነዚህ አስፋፊዎች ውስጥ 160ዎቹ ብቻ እንኳን ይህ የአገልግሎት ዓመት ከማለቁ በፊት የዘወትር አቅኚ ለመሆን ቢመዘገቡ በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ 600 ወይም ከዚያ የሚበልጡ የሙሉ ጊዜ አቅኚዎች ሊኖሩን ይችላሉ!
7 ፕሮግራም ማውጣት ያስፈልጋል፦ በወር ውስጥ 70 ሰዓት በመስክ አገልግሎት ማሳለፍ አሁንም ልትደርሱበት እንደማትችሉ ሆኖ ይታያችኋል? ምናልባት በሳምንት ማገልገል ያለባችሁ 17 ሰዓት ብቻ እንደሆነ ማሰቡ ይረዳችሁ ይሆናል። በሚቀጥለው ገጽ ላይ ለናሙና የቀረቡትን ፕሮግራሞች በመጠቀም ከራሳችሁ የግል ሁኔታ ጋር የሚስማማ የዘወትር አቅኚነት ፕሮግራም ለማውጣት ሞክሩ። ይህን በምታደርጉበት ወቅት አቅኚነትን እንዴት ከግልና ከቤተሰብ ኃላፊነቶች ጋር ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማከናወን እንደቻሉ ምክር እንዲሰጧችሁ ተሞክሮ ካላቸው አቅኚዎች ጋር ተወያዩ። በወረዳው ውስጥ ያሉ አቅኚዎች በየሳምንቱ ለሚያከናውኑት የአገልግሎት እንቅስቃሴ እንዴት ፕሮግራም እንደሚያወጡ የወረዳችሁን የበላይ ተመልካች ጠይቁት። ከዚያ በተረፈ በአቅኚነት ለማገልገል ያወጣችሁትን እቅድ ይሖዋ እንደሚባርክላችሁ እምነት ይኑራችሁ።—ምሳሌ 16:3
8 የቤተሰባችሁ ፕሮጄክት አድርጉት፦ አቅኚነት የቤተሰባችሁ ፕሮጄክት እንዲሆን ስለማድረግ አስባችሁ ታውቃላችሁ? መላው ቤተሰብ በጥንቃቄ እቅድ ቢያወጣና ጥሩ የመተባበር መንፈስ ቢያሳይ አንድ ወይም ሁለት የቤተሰቡ አባላት እንዴት አቅኚ መሆን እንደሚችሉ በቤተሰብ አንድ ላይ ተቀምጣችሁ መወያየት ትችሉ ይሆናል። አንዳንዶች ሁኔታቸውን በሐቀኝነት በመመርመር አሁን የዘወትር አቅኚ መሆን እንደማይችሉ ይገነዘቡ ይሆናል። እንዲህ ከሆነ አቅኚነትን የወደፊት ግባችሁ አድርጉት። ይሁን እንጂ አቅኚነት የምትጀምሩበትን ጊዜ ወስኑና እዚያ ግብ ላይ ለመድረስ የሚያስችላችሁን እቅድ አውጡ። ምናልባትም የዘወትር አቅኚነት ግብ ላይ እንድትደርሱ በዓመቱ ውስጥ የተወሰነ ጊዜ ረዳት አቅኚ ሆናችሁ ማገልገል ትችላላችሁ።
9 አሁን በመስካችን ያሉት ከ443 የሚበልጡ የዘወትር አቅኚዎች ያላቸው ሁኔታ የተለያየ ነው። ጥሩ ጤንነት ያላቸው ሁሉም አይደሉም እንዲሁም አብዛኞቹ የቤተሰብ ኃላፊነትና ገንዘብ ነክ ግዴታ አለባቸው። እድሜያቸው ከ50 በላይ የሆኑ ከ54 የሚበልጡ አቅኚዎች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ 30 የሚሆኑት ከ65 ዓመት በላይ ሆኗቸዋል። ሦስት መቶ አሥራ ስምንት የሚያህሉት ነጠላ ሲሆኑ አሥሩ ብቻ እድሜያቸው 20 ወይም ከዚያ ያነሰ ነው። ብዙዎቹ አቅኚዎች ወንድሞች ሲሆኑ የቤተሰብና የጉባኤ ኃላፊነቶች አሉባቸው። እነዚህ ሁሉ አቅኚ ለመሆን ሲሉ ‘ዘመኑን ዋጅተዋል።’ ይህ ደግሞ ብዙውን ጊዜ ቀለል ያለ ነገር ግን የበለጠ እርካታ ያለው ሕይወት መኖር ማለት ነው።—ቆላ. 4:5
10 ኑሯችሁን ቀላል ማድረግ ያስፈልጋችሁ ይሆን? አቅኚ ሆናችሁ እንድታገለግሉ የሚያስችላችሁ ቁልፍ ኑሯችሁን ቀላል ማድረግ ሊሆን ይችላል። ኑሯችሁ ለመንከባከብ ብዙ ገንዘብ፣ ጊዜና ሥራ የሚጠይቁ አላስፈላጊ ክፍሎችና የቤት ውስጥ ዕቃዎች እንዳሉት ትልቅ ቤት ነውን? ከሆነ ሁኔታችሁን የበለጠ ልከኛ ማድረግ አቅኚ ለመሆን ያስችላችሁ ይሆናል። በሰብዓዊ ሥራ የምታሳልፉትን ጊዜ መቀነስ ትችሉ ይሆን? አላስፈላጊ ከሆኑ እንቅስቃሴዎች ላይ ጊዜ መዋጀት ወይም ለመዝናኛ በምታሳልፉት ጊዜ ረገድ ይበልጥ ሚዛናዊ መሆን ትችሉ ይሆን?
11 መጽሐፍ ቅዱስ በ1 ጢሞቴዎስ 6:8 ላይ “ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፣ እርሱ ይበቃናል” በማለት ይመክረናል። በአነስተኛ ነገር ረክቶ መኖር በይሖዋ አገልግሎት የምንችለውን ያህል ለመሥራት የሚያስችለን አስፈላጊ ነገር ሲሆን ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ መስጠቱንም ቀላል ያደርግልናል። (ማቴ. 6:22, 23) በ1998 የዓመት መጽሐፍ ገጽ 104 ላይ በጃፓን አገር ዛሬ ያለውን ዓይነት ጥሩ የአቅኚነት መንፈስ ሊኖር የቻለው ለምን እንደሆነ የሚጠቁሙ አንዳንድ ሐሳቦች ቀርበዋል። አንዱን ተመልከቱ:- “የጃፓናውያን ቤቶች በአብዛኛው አነስ ያሉ ስለሆኑ ለመንከባከብ የሚጠይቁት ጊዜ ትንሽ ነው። አኗኗራቸውም በጥቅሉ ሲታይ ቀለል ያለ ነው።” የ1 ጢሞቴዎስ 6:8 ፍሬ ነገርስ ይኸው አይደለምን?
12 የአምላክ አገልጋዮች የይሖዋ የመዳን ቀን ወደ ፍጻሜው ከመምጣቱ በፊት በዓለም ዙሪያ ምሥራቹን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መጠን እየሰበኩ ነው። ባለፈው ዓመት በአማካይ 700,000 የሚሆኑ አስፋፊዎች በየወሩ በአንድ ዓይነት የአቅኚነት አገልግሎት ዘርፍ መሳተፋቸው የሚያስመሰግን ነው። እናንተስ በአቅኚነት ለማገልገል አኗኗራችሁን ማስተካከል ትችሉ ይሆን? “አሁንስ አቅኚ መሆን ትችሉ ይሆን?” ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ሁኔታችሁን በጥንቃቄና በጸሎት እንድትመረምሩ እናበረታታችኋለን።
[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ ሥዕል1]
(ወደ ገጽ 7 ዞሯል)
[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ ሥዕል7]
አቅኚ . . . (ከገጽ 1 የዞረ)
[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ ሥዕል7]
ግብ፦ 600
የዘወትር አቅኚዎች!
[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ ሥዕል7]
(ወደ ገጽ 8 ዞሯል)
[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ ሥዕል8]
አቅኚ . . . (ከገጽ 7 የዞረ)