ወላጆች—ለልጆቻችሁ ጥሩ ምሳሌ ሁኑ
1 የአምላክ ቃል ‘የጻድቅ አባት [እንዲሁም እናት] እጅግ ደስ ይላቸዋል’ ሲል ይናገራል። (ምሳሌ 23:24, 25) ለልጆቻቸው ጥሩ ምሳሌ ለሆኑ ወላጆች ይህ ምንኛ በረከት ነው! አንድ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነ ወንድም ወላጆቹን በተመለከተ እንዲህ ብሏል:- “መላ ሕይወታቸው በእውነት ላይ ያተኮረ ነበር፤ እኔም መላ ሕይወቴ በእውነት ላይ እንዲያተኩር ፈለግሁ።” ልጆች ከወላጆቻቸው ምን ማየት አለባቸው?
2 ጥሩ ምግባርና ጥልቅ አክብሮት፦ በልጆቻቸው ውስጥ ጥሩ ምግባር መቅረጽ የወላጆች ኃላፊነት ነው። ጥሩ ምግባር እንዲያው በቃል በሚሰጥ መመሪያ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሲያደርጉት በማየትና በመቅሰም የሚማሩት ነገር ነው። ታዲያ የምታሳዩት ምን ዓይነት ምግባር ነው? ልጆቻችሁ “ይቅርታ”፣ “እባክህ” እና “አመሰግናለሁ” ስትሉ ሰምተዋችሁ ያውቃሉ? ቤተሰባችሁ ውስጥ አንዳችሁ ለአንዳችሁ ጥልቅ አክብሮት አላችሁ? ሌሎች ሲናገሩ በጥሞና ታዳምጣላችሁ? ልጆቻችሁ ሲያነጋግሯችሁ ታዳምጧቸዋላችሁ? ይህ ጥሩ ምግባር በመንግሥት አዳራሽም ሆነ ቤት ውስጥ ብቻችሁን ስትሆኑ ይንጸባረቃልን?
3 ጠንካራ መንፈሳዊነትና ቅንዓት የተሞላበት አገልግሎት፦ ከ50 ዓመት በላይ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያሳለፈ አንድ ወንድም እንዲህ ሲል ያስታውሳል:- “እናቴና አባቴ ለስብሰባዎች በነበራቸው አድናቆትና ለአገልግሎት በነበራቸው ቅንዓት ረገድ ግሩም ምሳሌዎች ነበሩ።” የቤተሰባችሁን መንፈሳዊነት የመጠበቁ ጉዳይ እንደሚያሳስባችሁ ለልጆቻችሁ በተግባር የምታሳዩት እንዴት ነው? የዕለት ጥቅሱን አብራችሁ ታደርጋላችሁ? ቋሚ የቤተሰብ ጥናት አላችሁ? ልጆቻችሁ መጽሐፍ ቅዱስንና የማኅበሩን ጽሑፎች ስታነቡ ያዩዋችኋል? ቤተሰቡን ወክላችሁ ስትጸልዩ የሚሰሙት ነገር ምንድን ነው? ስለ እውነትና ስለ ጉባኤያችሁ አዎንታዊ ነገሮችን በመወያየት ከልጆቻችሁ ጋር የሚያንጽ መንፈሳዊ ጭውውት ታደርጋላችሁ? በቤተሰብ መልክ በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘትና በመስክ አገልግሎት ለመካፈል ትጓጓላችሁ?
4 ወላጆች ለልጆቻችሁ ምን ምሳሌ እየተዋችሁ እንዳላችሁ አስቡ። ጥሩ ምሳሌ ተዉላቸው፤ በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ እንደ ውድ ሃብት ይመለከቱታል። አሁን በ70ዎቹ ዕድሜ የምትገኝ የአንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሚስት እንዲህ ብላለች:- “አፍቃሪ የሆኑት ክርስቲያን ወላጆቼ የተዉልኝ ጥሩ ምሳሌ አሁንም እየጠቀመኝ ነው። እንዲሁም በሚመጡት ጊዜያት ሁሉ በዚህ ቅርስ በአግባቡ በመጠቀም ላወረሱኝ ነገር ያለኝን ሙሉ አድናቆት ለማረጋገጥ ከልብ እጸልያለሁ።”