የምትሠሩት በዓላማ ነውን?
1 ይሖዋ የዓላማ አምላክ ነው። (ኢሳ. 55:10, 11) እኛም እርሱን እንድንመስለው ተመክረናል። (ኤፌ. 5:1) ይህም አገልግሎታችንን በምናከናውንበት መንገድ ላይ መታየት እንዳለበት ጥርጥር የለውም። ስለዚህ “የምትሠሩት በዓላማ ነውን?” የሚለው ጥያቄ መነሳቱ ተገቢ ነው።
2 ከቤት ወደ ቤት መስበካችሁ፣ መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመሥከራችሁ እንዲሁም ጽሑፍ ማበርከታችሁ በዓላማ የሚከናወን አገልግሎት ክፍል ነው። ሆኖም ተልዕኳችን መስበክን ብቻ ሳይሆን ደቀ መዛሙርት ማድረግንም እንደሚያጠቃልል አስታውሱ። (ማቴ. 28:19, 20) የመንግሥቱን የእውነት ዘር ከዘራን በኋላ ይሖዋ ጭማሪውን እንዲያስገኝ እየተጠባበቅን ተመልሰን ውኃ ማጠጣትና የማያቋርጥ እንክብካቤ ማድረግ ይኖርብናል። (1 ቆሮ. 3:6) ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግንና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመርን በተመለከተ ትጉዎች መሆን አለብን።
3 አገልግሎታችሁን አስፉ፦ በአገልግሎት ያከናወናችሁትን ነገር መለስ ብላችሁ ስትመለከቱና “ላደርገው ያሰብኩትን ፈጽሜአለሁ” ብላችሁ ለራሳችሁ ስትናገሩ ምንጊዜም ጥሩ ስሜት ይኖራችኋል። በ2 ጢሞቴዎስ 4:5 [NW] ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ጳውሎስ “አገልግሎትህን ሙሉ በሙሉ ፈጽም” የሚል ምክር ሰጥቷል። ይህም ፍላጎት ያሳዩትን ሰዎች ሁሉ ተከታትሎ ለመርዳት የምታደርጉትን ጥረት ማሳደግን ያጠቃልላል። በሳምንታዊ የአገልግሎት ፕሮግራማችሁ ውስጥ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ የተወሰነ ጊዜ መድቡ። የጽድቅ ዝንባሌ ላላቸው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የማስጀመር ግብ ይኑራችሁ። በአገልግሎት በምትካፈልበት ጊዜ ይህ ግብህ ሊሆን ይገባል።
4 አስፋፊዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻቸው በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ሲጠመቁ በሚያዩበት ጊዜ ምን እንደተሰማቸው ጠይቋቸው። ከተጠመቁት ጥናቶቻቸው ባላነሰ ምናልባትም በበለጠ ሁኔታ ተደስተዋል። አንድ ታላቅ ዓላማ ከግብ አድርሰዋል! ደቀ መዝሙር በማድረጉ ሥራ የተሳተፈ አንድ ወንድም ጉዳዩን እንዲህ ሲል ገልጾታል:- “ደቀ መዝሙር ማድረግ ማለት ይሖዋን የሚያወድሱ ተጨማሪ ሰዎች ማፍራት ማለት ነው። እውነትን ለተቀበሉት ሰዎች ደግሞ ሕይወት ማለት ነው። ለሌሎች እውነትን ማስተማር በጣም ያስደስተኛል። ደቀ መዝሙር የማድረጉ ሥራ እጅግ አስደሳች ነው! . . . ይሖዋን ወደ ማፍቀር ደረጃ የደረሱት አብዛኞቹ ጥናቶቼ የቅርብ ወዳጆቼ ሆነዋል።”
5 አንድ ሰው ራሱን የወሰነ የይሖዋ አገልጋይ እንዲሆን መርዳት መቻል ምን ያህል አስደሳች እንደሆነ እስቲ አስቡት! እንዲህ ዓይነት ውጤት የሚገኘው አገልግሎቱን በዓላማ በማከናወን ነው።—ቆላ. 4:17