በመንፈሳዊ ጠንካራ የሆነ ቤተሰብ መገንባት—እንዴት?
1 ክርስቲያን ቤተሰቦች ‘ለገዛ ቤተ ሰዎቻቸው ለአምላክ የማደርን ባሕርይ በማሳየታቸው’ ይመሰገናሉ። (1 ጢሞ. 5:4 NW ) ይሁን እንጂ እምነታችንን ሊያዳክሙ የሚችሉ ብዙ መጥፎ ተጽእኖዎች በዙሪያችን ስላሉ ቤተሰቦች በመንፈሳዊ ጠንካሮች ሆነው እንዲቀጥሉ ጠንክረው መሥራታቸው የግድ አስፈላጊ ነው። ይህን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
2 የራስነትን ሥልጣን እንደ ክርስቶስ ተጠቀሙበት:- የቤተሰብ ራሶች ቤተሰባቸውን በማጠናከር በኩል የተጣለባቸውን ኃላፊነት በሚወጡበት ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስን መምሰል ይኖርባቸዋል። ኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት በመሞት ለእኛ ያለውን ፍቅር ከማሳየቱም በላይ ጉባኤውን አዘውትሮ “ይመግበዋል ይከባከበውማል።” (ኤፌ. 5:25-29) አፍቃሪ ወላጆች የቤተሰባቸውን የዕለት ተዕለት መንፈሳዊ ፍላጎት በማሟላት ጥልቅ አሳቢነት የተንጸባረቀበትን ይህንን ምሳሌ ይከተላሉ። ይህም በየሳምንቱ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማካሄድን፣ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ጥልቀት ያለው መንፈሳዊ ውይይት ማድረግንና ችግሮች እንደተነሱ ወዲያውኑ መፍትሔ መፈለግን ያጠቃልላል።—ዘዳ. 6:6, 7
3 በመስክ አገልግሎት፦ ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ ለሌሎች መመስከር የአምልኳቸው ዓቢይ ክፍል መሆኑን ሁሉም የቤተሰቡ አባላት መገንዘብ ይኖርባቸዋል። (ኢሳ. 43:10-12) እናንተ ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ታማኝ የይሖዋ ምሥክሮች እንዲሆኑ ከፈለጋችሁ ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ልባቸውን ለአገልግሎቱ ማዘጋጀት አለባችሁ። በአገልግሎቱ የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ማሳየት እንዲሁም በየሳምንቱ በስብከቱ ሥራ መካፈል አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ አወያዩአቸው። (ማቴ. 22:37-39) ከዚያም አዘውትረው ከእናንተ ጋር በመስክ አገልግሎት እንዲካፈሉ ዝግጅቶች አድርጉ።
4 በሳምንቱ የቤተሰብ ጥናት ወቅት ውጤታማ የሆነ መግቢያ ለመዘጋጀትና ለመለማመድ የሚያስችል ጊዜ በመመደብ ለስብከቱ ሥራ አድናቆት እንዲያድርባቸው አድርጉ። ልጆቻችሁን በግለሰብ ደረጃ ለአገልግሎቱ በማሰልጠን እንደ ዕድሜያቸውና እንደ ችሎታቸው መጠን እድገት እንዲያደርጉ እርዷቸው። አብራችሁ በአገልግሎት ካሳለፋችሁ በኋላ እነሱ በግላቸው የይሖዋን ጥሩነት እንዴት እንደተመለከቱ ተወያዩ። እምነት የሚያጠነክሩ ተሞክሮዎች ንገሯቸው። ቤተሰቦች ‘ጌታ ቸር መሆኑን በቀመሱ’ መጠን ወደ ይሖዋ ይበልጥ ይቀርባሉ፤ ይህም “ክፋትን ሁሉ” ለመቋቋም የሚያስችል ተጨማሪ ጥንካሬ ይሰጣቸዋል።—1 ጴጥ. 2:1-3
5 በስብሰባዎች ላይ፦ በተለይ ከቤተሰቡ አባላት አንዱ ድካም በሚሰማው፣ ተስፋ በሚቆርጥበት ወይም ከአቅሙ በላይ የሆነ ችግር በሚያጋጥመው ወቅት የቤተሰቡ አባላት በሙሉ በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት እርስ በእርስ መበረታታታቸው ምንኛ መልካም ይሆናል! አንዲት ወጣት እህት እንዲህ ብላለች:- “አባቴ ከሥራ ወደ ቤት ሲመለስ በጣም ይደክመዋል። ሆኖም በዚያ ምሽት በሚደረገው ስብሰባ ላይ ትምህርት የሚሰጥበትን አንድ ጥሩ ነጥብ አንስቼ ሳካፍለው ወደ ስብሰባው ለመሄድ ይበረታታል። እኔ ሲደክመኝ ደግሞ እሱ ያበረታታኛል።”—ዕብ. 10:24, 25
6 አንድ ላይ ሆናችሁ ሥሩ፦ ቤተሰቦች የቤት ውስጥ ሥራዎችን እና ሌሎች ተግባራትን ተጋግዘው በማከናወን አንድ ላይ ሆነው መሥራት ይኖርባቸዋል። በሚገባ ታስቦበት በተመረጠ መዝናኛ ለመካፈልም ጊዜ መመደብ ይገባቸዋል። ሽርሽር መሄድ፣ በእግር መጓዝ፣ የተለያዩ ጨዋታዎችን መጫወት እንዲሁም ዘመዶችንና ወዳጆችን መጠየቅ አስደሳች ከመሆናቸውም በላይ ጥሩ ትዝታዎች ጥለው ያልፋሉ።—መክ. 3:4
7 ጠንካራ ክርስቲያን ቤተሰቦች በመንፈሳዊነታቸው ላይ በየዕለቱ የሚሰነዘሩ ፈተናዎችን ይቋቋማሉ። ወደ ይሖዋ ይበልጥ በመቅረብ እሱ የሚሰጠውን ኃይል ያገኛሉ።—ኤፌ. 6:10