በበረከት መዝራት በረከት ያስገኛል
1 በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት ድንቅ ተስፋዎች ፍጻሜአቸውን የሚያገኙበትን ጊዜ ሁላችንም በጉጉት እንጠባበቃለን። በአሁኑ ጊዜም እንኳ ቢሆን ይሖዋ ደስታችንን እጥፍ ድርብ የሚያደርግልንን የተትረፈረፈ በረከት እያፈሰሰልን ነው። ሆኖም በግለሰብ ደረጃ የምናገኘው በረከት በምናደርገው ጥረት ላይ በእጅጉ የተመካ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለጸው “በበረከትም የሚዘራ በበረከት ደግሞ ያጭዳል።” (2 ቆሮ. 9:6) ይህ መሠረታዊ ሥርዓት የሚሠራባቸውን ሁለት አቅጣጫዎች ተመልከት።
2 የስብከቱ ሥራ፦ ምሥራቹን ለሰዎች ለማብሰር አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረጋችን ብዙ በረከት ያስገኝልናል። (ምሳሌ 3:27, 28) ብዙዎች በረዳት ወይም በዘወትር አቅኚነት መካፈልን ጨምሮ በአገልግሎቱ የሚያደርጉትን ተሳትፎ ከፍ በማድረግ በበረከት እየዘሩ መሆናቸው የሚያስመሰግን ነው። ሁላችንም ፍላጎት ያሳዩትን ሰዎች ሁሉ በትጋት ተመልሰን በማነጋገርና መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑ በመጋበዝ በበረከት መዝራት እንችላለን። (ሮሜ 12:11) በእነዚህ መስኮች የምናደርገው ጥረት የሚያበረታቱ ተሞክሮዎች ከማስገኘቱም በላይ በአገልግሎታችን ተጨማሪ ደስታ ያመጣልናል።
3 የአምላክን መንግሥት መደገፍ፦ ጳውሎስ ‘በበረከት ስለመዝራት’ የተናገረው ቁሳዊ ልግስና ከማድረግ ጋር አያይዞ ነው። (2 ቆሮ. 9:6, 7, 11, 13) ዛሬ የአምላክን መንግሥት በጉልበታችንም ሆነ በንብረታችን በመደገፍ ረገድ ልናከናውነው የምንችለው ብዙ ነገር አለ። በመንግሥት አዳራሽ ግንባታው ሥራ እገዛ ልናደርግ እንችላለን። እንዲሁም እነዚህን የእውነተኛ አምልኮ ቦታዎች በማጽዳቱና በማደሱ ሥራ በፈቃደኝነት የበኩላችንን ልናደርግ እንችላለን። ከዚህም በተጨማሪ የጉባኤያችንን ወጪዎች ለመሸፈንም ሆነ ዓለም አቀፉን የስብከትና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ ለመደገፍ የገንዘብ መዋጮ ማድረግ እንችላለን። ሁላችንም የበኩላችንን ካደረግን ይሖዋ እንድንሠራው የሰጠንን ሥራ አብዝቶ እየባረከው እንዳለ በመመልከት እጅግ እንደሰታለን!—ሚል. 3:10፤ ሉቃስ 6:38
4 የአምላክ ቃል ‘መልካምን እንድናደርግ፣ በበጎም ሥራ ባለጠጎች እንድንሆን፣ ለመርዳትና ለማካፈልም የተዘጋጀን እንድንሆን’ ይመክረናል። ይህን ምክር ሰምተን ተግባራዊ ካደረግን አሁን የተትረፈረፈ በረከት እናገኛለን። ከዚህም በላይ ‘እውነተኛውን ሕይወት ለመያዝ፣ ለሚመጣው ዘመን ለራሳችን መልካም መሠረት የሚሆንልን መዝገብ እንሰበስባለን።’—1 ጢሞ. 6:18, 19