ሌሎችን የመርዳት ልባዊ ፍላጎት አለህን?
1 ኢየሱስ ለሰዎች ከልብ ያስብ ነበር። አንድ ለምጻም እንዲረዳው በተማጸነው ጊዜ ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ሰውየውን ዳሰሰውና “እወድዳለሁ ንጻ” አለው። (ማር. 1:40-42) ሌሎችን በመርዳት ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መኮረጅ የምንችለው በምን መንገዶች ነው?
2 ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች፦ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች የይሖዋ አምላኪዎች እንዲሆኑ በመርዳት በኩል እያንዳንዱ የጉባኤው አባል የሚያበረክተው ድርሻ አለ። አዲሶች በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ሲገኙ ሰላም በሏቸው እንዲሁም ቀረብ ብላችሁ ተዋወቋቸው። እነሱን ለማበረታታትም ጥረት አድርጉ። ለሚሰጡት ሐሳብ አመስግኗቸው። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ለማዋል የሚያደርጉትን ጥረት እንደምታደንቁም ንገሯቸው። በጉባኤ ውስጥ እውነተኛ ጓደኞች የማግኘት አጋጣሚ እንዳላቸው እንዲያውቁ አድርጉ።
3 ለእምነት ባልደረቦቻችን፦ በተለይ ‘የሃይማኖት ቤተሰዎቻችንን’ በብዙ መንገዶች ልንረዳቸው ይገባል። (ገላ. 6:10) ብዙዎች ከጤና እክል ጋር ይታገላሉ። ቤታቸው ሄዳችሁ በመጠየቅ ልታጽናኗቸውና ልታበረታቷቸው አልፎ ተርፎም በአንዳንድ ነገር ልትረዷቸው ትችላላችሁ። አንዳንዶች ደግሞ በሕይወታቸው ውስጥ ሌሎች ችግሮች ሊኖሩባቸው ይችላሉ። ቀረብ ብላችሁ በማጫወትና የሚናገሩትን በጥሞና በማዳመጥ እንዲሁም በማበረታታት እንደምታስቡላቸው ማሳየት ትችላላችሁ። (1 ተሰ. 5:14) ያለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት እየጣሩ ያሉ ሽማግሌዎችም የእኛን ትብብር ይሻሉ። (ዕብ. 13:17) የፈቃደኝነትና የትብብር መንፈስ በማሳየት ለእምነት ባልደረቦቻችን ‘የብርታትና የመጽናናት ምንጭ ልንሆን’ እንችላለን።—ቆላ. 4:10, 11
4 ለቤተሰብ አባሎች፦ ለቤተሰባችን አባሎችም አሳቢነት በማሳየት የኢየሱስን አርዓያ ለመኮረጅ መጣር አለብን። ወላጆች ለልጆቻቸው ያላቸው ጥልቅ አሳቢነት ‘ልጆቻቸውን በጌታ ምክርና ተግሣጽ እንዲያሳድጓቸው’ ይገፋፋቸዋል። (ኤፌ. 6:4) ልጆችም የቤተሰብ ጥናት፣ የጉባኤ ስብሰባዎች ወይም የመስክ አገልግሎት ሰዓት ሲደርስ በፍጥነት በመዘጋጀት የበኩላቸውን ሊያደርጉ ይችላሉ። ራሳቸውን የቻሉ ልጆችም በእርጅና ዕድሜ የሚገኙ ወላጆቻቸውን በመጦር ኢየሱስ ያሳየው ዓይነት ርኅራኄ ሊያሳዩ ይችላሉ። ሁላችንም ለቤተሰባችን እንዲህ የመሰሉ ነገሮች በማድረግ ‘ለአምላክ ያደርን መሆናችንን’ ማሳየት እንችላለን።—1 ጢሞ. 5:4 NW
5 የኢየሱስን አርዓያ መከተላችን ሌሎችን ለመርዳት እንድንነሳሳ እንዲሁም ከቤተሰባችንና ከጉባኤያችን ጋር ይበልጥ እንድንቀራረብ ያስችለናል። ከሁሉ በላይ ደግሞ “የርኅራኄ አባት” የሆነውን ይሖዋን እናስከብራለን።—2 ቆሮ. 1:3