የአገልግሎት ስብሰባ ፕሮግራም
ማሳሰቢያ:- የመንግሥት አገልግሎታችን የአውራጃ ስብሰባ በምታደርጉበት ወር የሁሉንም ሳምንታት ፕሮግራም ይዞ ይወጣል። ጉባኤዎች “ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች” በተሰኘው የአውራጃ ስብሰባ ላይ በሚገኙበት ሳምንት የሚደረገው የአገልግሎት ስብሰባ ፕሮግራም እንዳያመልጣቸው እንደ አስፈላጊነቱ ማስተካከያ ማድረግ ይችላሉ። ከአውራጃ ስብሰባው በፊት ባለው ሳምንት በምታደርጉት የአገልግሎት ስብሰባ ላይ ጥቂት ደቂቃዎች ወስዳችሁ በቅርብ ወራት በወጡ የመንግሥት አገልግሎታችን እትሞች ላይ ከሰፈሩት ጠቃሚ ምክሮች ውስጥ ለጉባኤው ያስፈልጋሉ የምትሏቸውን ከልሱ። ሁሉም የአውራጃ ስብሰባዎች ሲጠናቀቁ የፕሮግራሙን ጎላ ያሉ ነጥቦች ለመከለስ አንድ ሙሉ የአገልግሎት ስብሰባ ፕሮግራም ይመደባል። በክለሳ ውይይቱ ላይ ጥሩ ተሳትፎ ለማድረግ ሁላችንም በስብሰባው ወቅት ጠቃሚ የሆኑ ነጥቦችን እንዲሁም በግል ሕይወታችንና በመስክ አገልግሎት ላይ ልንሠራባቸው የምንፈልጋቸውን ዝርዝር ሐሳቦች በማስታወሻ መያዝ እንችላለን። ከዚያም በውይይቱ ላይ እነዚህን ምክሮች ከአውራጃ ስብሰባው በኋላ እንዴት በሥራ ላይ ማዋል እንደቻልን መናገር እንችላለን። በስብሰባው ላይ ያገኙትን ጠቃሚ ትምህርቶች ሁሉም ሲናገሩ መስማት ሁላችንንም የሚያንጽ ይሆናል።
መስከረም 9 የሚጀምር ሳምንት
መዝሙር 92 (209)
13 ደቂቃ:- የጉባኤ ማስታወቂያዎች። ከመንግሥት አገልግሎታችን የተመረጡ ማስታወቂያዎች። ሁሉም በሚቀጥለው ሳምንት ለሚደረገው የአገልግሎት ስብሰባ ባለፈው የአገልግሎት ዓመት በተካሄደው የወረዳ ስብሰባ ላይ የወሰዱትን ማስታወሻ ከልሰው እንዲመጡ አሳስባቸው። በገጽ 8 ላይ ያሉትን ሐሳቦች በመጠቀም መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ሲበረከቱ የሚያሳዩ ሁለት ሠርቶ ማሳያዎች አቅርብ። ሁለቱም ሠርቶ ማሳያዎች ‘የይሖዋ ምሥክሮችን አልፈልግም’ ለሚል ሰው በተለያየ መንገድ መልስ ሲሰጥ የሚያሳዩ ይሁኑ።—ማመራመር መጽሐፍ ገጽ 17ና 18 ተመልከት።
17 ደቂቃ:- “ይሖዋን እንዲያከብሩት ሌሎችን መርዳት።” አንድ ደቂቃ በማይሞላ ጊዜ ውስጥ የመግቢያ ሐሳብ ከተናገርክ በኋላ በጥያቄና መልስ አቅርበው። ጊዜ በፈቀደልህ መጠን ማመራመር ከተባለው መጽሐፍ ከገጽ 197-199 ላይ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ አንድ ወይም ሁለት ነጥቦችን ጥቀስ።
15 ደቂቃ:- እምነት የሚጎድላቸው ለምንድን ነው? ከአድማጮች ጋር በውይይት የሚቀርብ። አብዛኛውን ጊዜ እምነት የሌላቸው ሰዎች ያጋጥሙናል። (2 ተሰ. 3:1, 2) ስለ ይሖዋ የሚናገረውን እውነት ለእነዚህ ሰዎች ለማካፈል እንድንችል በመጀመሪያ ስለ አምላክ የተለየ አመለካከት እንዲኖራቸው ያደረገው ምን እንደሆነ ማወቅ አለብን። በማመራመር መጽሐፍ ገጽ 131, 132 ላይ የሰፈሩትን ሰዎች እምነት እንዳይኖራቸው ሊያደርጉ የሚችሉ አራት ምክንያቶች ተመልከቱ። በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ እምነት የጎደላቸው ሰዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ ምን ዓይነት አቀራረብ መጠቀም እንደምንችል አድማጮች ሐሳብ እንዲሰጡ ጋብዝ። ውጤታማ የሆነ አቀራረብ የሚያሳይ አንድ ተሞክሮ ወይም በነሐሴ 22, 1993 ንቁ! (እንግሊዝኛ) መጽሔት ገጽ ከ14-15 ላይ ያለውን ተናገር።
መዝሙር 95 (213) እና የመደምደሚያ ጸሎት።
መስከረም 16 የሚጀምር ሳምንት
መዝሙር 71 (163)
5 ደቂቃ:- የጉባኤ ማስታወቂያዎች።
25 ደቂቃ:- “አምላክን ፍሩ ክብርንም ስጡት።” (ራእይ 14:7) ባለፈው የአገልግሎት ዓመት ያደረግነውን የወረዳ ስብሰባ ፕሮግራም በተመለከተ በንግግርና ከአድማጮች ጋር በውይይት የሚደረግ ክለሳ። አስፋፊዎች ስለተማሯቸው ዋና ዋና ነጥቦች ሐሳብ እንዲሰጡና ትምህርቱን በግል ወይም በቤተሰብ ተግባራዊ ማድረግ የቻሉት እንዴት እንደሆነ እንዲናገሩ ጋብዝ። (ሐሳብ የሚሰጥባቸውን ነጥቦች አስቀድሞ ማከፋፈል ይቻላል።) ከስብሰባው ፕሮግራም ውስጥ የሚከተሉትን ክፍሎች ሸፍን:- (1) “አዳዲሶች ፈሪሃ አምላክ እንዲያዳብሩ እርዷቸው።” በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች እድገት እንዲያደርጉና ቀናተኛ የይሖዋ አገልጋዮች እንዲሆኑ ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው? (2) “ይሖዋን መፍራት ክፋትን መጥላት ማለት ነው።” (የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ 87 4/15 16-18) ምሳሌ 6:16-19 እንደ ኩራት፣ መዋሸት፣ ቁሳዊ ሃብት ማሳደድ፣ ጤናማ ያልሆነ መዝናኛ፣ ተገቢ ያልሆነ የኢንተርኔት አጠቃቀም ከመሳሰሉ ይሖዋ ከሚጠላቸው ነገሮች ለመራቅ የሚረዳን እንዴት ነው? (3) “ወደምትወዷቸው ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ቅረቡ።” ይሖዋን፣ ኢየሱስን፣ የቤተሰባችንን አባላትና በጉባኤ ውስጥ ያሉትን ሌሎች ሰዎች እንወዳለን፤ ወደ እነርሱ ይበልጥ መቅረባችን ከዓለም ሊጠብቀን የሚችለው እንዴት ነው? (4) “ሰውን ሳይሆን፣ ይሖዋን ፍሩ።” ይሖዋን ላለማሳዘን ያለን ፍርሃት በአገልግሎት ላይ የሚሰማንን ፍርሃት እንድናሸንፍ፣ በሥራ ቦታም ሆነ በትምህርት ቤት አምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በጥብቅ እንድንከተል ወይም ከጉባኤ ስብሰባዎች፣ ከወረዳ ወይም ልዩ ስብሰባዎችና ከአውራጃ ስብሰባዎች እንድንቀር አሠሪያችን የሚያሳድርብንን ጫና እንድንቋቋም የረዳን እንዴት ነው? (5) “ሁሉን ለአምላክ ክብር አድርጉት።” (መዝ. 119:37፤ ዕብ. 4:13) አምላካዊ ፍርሃት ከልክ በላይ ከመጠጣት፣ ወሲባዊ ሥዕሎችን ከመመልከት ወይም ሌሎች ድብቅ ኃጢአቶችን ከመፈጸም የሚጠብቀን እንዴት ነው? (6) “ይሖዋን በመፍራት መመላለሳችሁን ቀጥሉ።” የይሖዋ መንፈስ በሕይወትህ ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንዲሠራ በማድረግህ የተባረክኸው እንዴት ነው?—መዝ. 31:19፤ 33:18፤ 34:9, 17፤ 145:19
15 ደቂቃ:- “መንፈሳዊ ፍላጎታችሁን አርኩ።” በንግግርና ከአድማጮች ጋር በሚደረግ ውይይት የሚቀርብ። በስብሰባው ላይ የሚሰጠውን ትምህርት በትኩረት መከታተልና የተማርነውን በሥራ ላይ ማዋል አስፈላጊ መሆኑን ጎላ አድርገህ ተናገር። ሁሉም በስብሰባው ወቅት ማስታወሻ እንዲይዙ አበረታታቸው። በዚህ የአገልግሎት ስብሰባ ፕሮግራም መግቢያ ላይ የአውራጃ ስብሰባውን ፕሮግራም ለመከለስ ስለተደረገው ዝግጅት የሚናገረውን ሐሳብ ተመልከት። እንዲሁም በምሳ የእረፍት ሰዓት ከሌሎች ጋር በመጨዋወት አስደሳች ጊዜ ማሳለፍ እንድንችል ውጪ ወጥተን ለመመገብ ከማሰብ ይልቅ ባለፉት ጊዜያት እንዳደረግነው ምግባችንን ከቤት ይዘን እንድንሄድ አሳስባቸው።
መዝሙር 36 (81) እና የመደምደሚያ ጸሎት።
መስከረም 23 የሚጀምር ሳምንት
መዝሙር 46 (107)
13 ደቂቃ:- የጉባኤ ማስታወቂያዎች። የሒሳብ ሪፖርት። በገጽ 8 ላይ ያሉትን አቀራረቦች በመጠቀም አንድ ሽማግሌ መጠበቂያ ግንብ ሲያበረክትና አንድ የጉባኤ አገልጋይ ንቁ! ሲያበረክት የሚያሳዩ ሠርቶ ማሳያዎች አቅርብ። ከእያንዳንዱ ሠርቶ ማሳያ በኋላ የሚያነጋግሩትን ግለሰብ ፍላጎት ለመቀስቀስ የተጠቀሙባቸውን አንድ ወይም ሁለት የመግቢያ ዓረፍተ ነገሮች በድጋሚ ተናገር።
15 ደቂቃ:- በትምህርት ቤት ለእውነት ጥብቅና መቆም። ሁሉም ልጆችና ትምህርት ቤት የሚሄዱ ተማሪዎች እንዲሁም ወላጆች ትምህርት ቤት የተባለውን ብሮሹር እንዲያነቡና እንዲጠቀሙበት አበረታታ። በስብሰባው ላይ የተገኙት ልጆች የዚህ ብሮሹር የራሳቸው ቅጂ ያላቸው መሆኑን እንዲያረጋግጡና ከሌላቸው በዚህ ሳምንት ከጽሑፍ አገልጋዩ አንድ ቅጂ እንዲወስዱ አሳስባቸው። ቅዱስ ጽሑፋዊ የሆነውን አቋማችን በሚመለከት ጥያቄ ላላቸው አስተማሪዎችም ይህን ብሮሹር መስጠት እንደሚቻል ጥቀስ። ወላጆች ተጨማሪ ቅጂዎችን እንዲወስዱ አበረታታቸው። አዲሱን የትምህርት ዘመን የጀመሩና ከማያምኑ የክፍል ጓደኞቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ ገደብ ማበጀት እንደሚያስፈልጋቸው ለተገነዘቡ ለአንድ ወይም ለሁለት ወጣት አስፋፊዎች ቃለ መጠይቅ አድርግላቸው። ብሔራዊ ስሜት በሚንጸባረቅባቸው ሥነ ሥርዓቶች፣ በትምህርት ቤት በሚዘጋጁ የዳንስና የፈንጠዝያ ዝግጅቶች፣ ከመደበኛ ትምህርት ውጪ በሚከናወኑ የስፖርት እንቅስቃሴዎችና ምግባረ ብልሹ በሆኑ ተግባራት እንዲሳተፉ የሚቀርቡላቸውን ፈተናዎችና ማባበያዎች ለመቋቋም ምን ዝግጅት አድርገዋል? በብሮሹሩ ውስጥ እነዚህ ነጥቦች የተብራሩበትን ገጾችና ንዑስ ርዕሶች ተናገር። ተማሪዎቹ በትምህርት ቤት በምን መንገድ ምሥክርነቱን መስጠት እንዳሰቡ እንዲናገሩ አድርግ።
17 ደቂቃ:- ነጠላ ወላጆች ያሉባቸው ፈተናዎች። አንድ ሽማግሌ ልጆቻቸውን በማሠልጠን፣ ተግሳጽ በመስጠትና በመንፈሳዊ በመምራት ረገድ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች የሚቋቋሙት እንዴት እንደሆነ እንዲናገሩ ለአንድ ወይም ለሁለት ነጠላ ወላጆች (ወይም የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ የትዳር ጓደኛ ላላቸው) ቃለ መጠይቅ ያደርጋል። የቤተሰብ ኃላፊነቶችን ለመወጣት እንዲሁም አዘውትሮ በስብሰባዎች ለመገኘትና በመስክ አገልግሎት ለመካፈል የቻሉት እንዴት ነው? የቤተሰብ ደስታ በተባለው መጽሐፍ ከገጽ 104-110 ላይ ከቀረቡት ሐሳቦች ውስጥ አንዳንዶቹን ጎላ አድርገህ ተናገር። ሌሎች እርዳታ ሊያበረክቱ የሚችሉባቸውን ጠቃሚ መንገዶች ከገጽ 113-115 ላይ ጥቀስ።
መዝሙር 75 (169) እና የመደምደሚያ ጸሎት።
መስከረም 30 የሚጀምር ሳምንት
መዝሙር 67 (156)
10 ደቂቃ:- የጉባኤ ማስታወቂያዎች። አስፋፊዎች የመስከረም ወር የመስክ አገልግሎት ሪፖርታቸውን እንዲመልሱ አስታውሳቸው። “የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ፕሮግራም ወደፊት በመግፋት ላይ ነው” የሚለውን ተወያዩበት።
15 ደቂቃ:- ያለፈው ዓመት የአገልግሎት እንቅስቃሴያችን ምን ይመስላል? በአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ የሚቀርብ ንግግር። የጉባኤውን የ2002 የአገልግሎት ዓመት ሪፖርት ጎላ ያሉ ገጽታዎች ተናገር። ላከናወኗቸው መልካም ነገሮች ሁሉንም አመስግን። ጉባኤው በስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ በመገኘት፣ ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግና መጽሐፍ ቅዱስ በማስጠናት እንዲሁም በረዳት አቅኚነት በመካፈል ረገድ ባደረጉት እንቅስቃሴ ላይ በማተኮር መሻሻል በሚያስፈልጋቸው ነገሮች ላይ ተግባራዊ ሐሳቦችን ስጥ። ለሚመጣው ዓመት ሊደረስባቸው የሚችሉ ግቦችን አውጡ።
20 ደቂቃ:- “ለጽሑፎቻችን አድናቆት ይኑራችሁ።” አንድ ደቂቃ በማይሞላ ጊዜ ውስጥ የመግቢያ ሐሳብ ከተናገርክ በኋላ በጥያቄና መልስ አቅርበው። በአንድ ሽማግሌ የሚቀርብ። ጉባኤው ለጽሑፎች ያለውን አድናቆት በተመለከተ የታዘብከውን ከተናገርክ በኋላ ወደፊት ጽሑፎቻችንን በጥንቃቄ በመጠቀም ረገድ አስፋፊዎች ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ሐሳብ ስጥ። ይሄን በሚመለከት በኅዳር 16, 2001 ለሁሉም ጉባኤዎችና ቡድኖች ከተላከው ደብዳቤ አንቀጽ 2ን መመልከት ትችላለህ። ሰዎች በተሳሳተ መንገድ ሊረዱት ስለሚችሉ ጽሑፎቻችንን ለሰዎች የምናበረክተው “በነጻ” እንደሆነ በሚያስመስል መንገድ መናገር እንደሌለብን እባክህ ግልጽ አድርገህ ተናገር። ከዚህ ይልቅ እንዲህ ለማለት እንችላለን:- “ፈቃደኛ ከሆንክና አቅሙ ካለህ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማር የሚካሄደውን ይህን ሥራ ለመደገፍ መጠነኛ መዋጮ ማድረግ ትችላለህ።” ወይም አንዳንድ አስፋፊዎች “የገቢ ምንጫቸው አነስተኛ የሆኑ ሰዎች ጭምር ይህን አስፈላጊ የሆነ ጽሑፍ ማግኘት እንዲችሉ ተብሎ ለጽሑፎቻችን የምናስከፍለው የተወሰነ የዋጋ መጠን የለም። እንደ አቅምህ መጠነኛ የሆነ መዋጮ ልታደርግ ትችላለህ።” ሁሉም ከሚያስፈልጋቸው በላይ ጽሑፍ እንዳያዝዙ አሳስባቸው። ዓለም አቀፉን ሥራ ለመደገፍ የገንዘብ አስተዋጽኦ የማድረግ መብታችንን አስታውሳቸው። ከላይ ከተጠቀሰው ደብዳቤ ላይ አንቀጽ 3ን ተመልከት።
መዝሙር 8 (21) እና የመደምደሚያ ጸሎት።
ጥቅምት 7 የሚጀምር ሳምንት
መዝሙር 52 (129)
10 ደቂቃ:- የጉባኤ ማስታወቂያዎች።
15 ደቂቃ:- መጽሔቶቻችንን ከሌሎች ልዩ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው? በንግግርና ከአድማጮች ጋር በውይይት የሚቀርብ። በጥቅምት ወር መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን እናበረክታለን። እነዚህን መጽሔቶች ከሌሎች ልዩ በሚያደርጓቸው ቀጥሎ በቀረቡት ነጥቦች ላይ ተወያዩ። (1) የይሖዋን ስም ያወድሳሉ። (2) በኢየሱስ ማመንን ያበረታታሉ። (3) የአምላክን መንግሥት ያውጃሉ። (4) መጽሐፍ ቅዱስን እንደመጨረሻው ባለ ሥልጣን አድርገው ይጠቅሳሉ። (5) የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ፍጻሜ ያብራራሉ። (6) በዓለማችን ላይ ከሚፈጸሙት ክስተቶች በስተጀርባ ያለውን እውነተኛ ትርጉም ያብራራሉ። (7) የጊዜያችንን ችግሮች መቋቋም የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ይናገራሉ። (8) ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ተስማሚ የሆኑ ትምህርቶችን ይዘዋል። (9) ከፖለቲካ ገለልተኛ ናቸው። ከእነዚህ ነጥቦች ውስጥ አንዱን በመጠቀም እንዴት ውይይት መክፈት እንደሚቻል የሚያሳዩ ሁለት አጫጭር ሠርቶ ማሳያዎችን አቅርብ።
20 ደቂቃ:- “‘ከንቱ’ ነገርን ከመከታተል ተቆጠቡ” አንድ ደቂቃ በማይሞላ ጊዜ ውስጥ የመግቢያ ሐሳብ ከተናገርክ በኋላ በጥያቄና መልስ አቅርበው። በአንቀጽ 3 ላይ ከተወያያችሁ በኋላ የኅዳር 1999 የመንግሥት አገልግሎታችን (እንግሊዝኛ) አባሪ ማግኘት የሚቻል ከሆነ ከአንቀጽ 30-32 ያለውን ሐሳብ ጨምረህ አቅርብ። (አንዳንድ ጉባኤዎች የዚህ አባሪ የእንግሊዝኛ ቅጂ በደብዳቤ ደርሷቸዋል።) አንቀጽ 4ን ስትወያዩ በጥቅምት 1, 1994 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 8 ላይ ካለው ሣጥን አንዳንድ ሐሳቦችን ተናገር። አንቀጽ 5 ላይ ስትደርሱ ከኅዳር 1999 የመንግሥት አገልግሎታችን አባሪ ላይ አንቀጽ 18ን አንብብ።
መዝሙር 44 (105) እና የመደምደሚያ ጸሎት።