የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • km 3/03 ገጽ 6
  • ከአስተዳደር አካል የተላከ ደብዳቤ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከአስተዳደር አካል የተላከ ደብዳቤ
  • የመንግሥት አገልግሎታችን—2003
የመንግሥት አገልግሎታችን—2003
km 3/03 ገጽ 6

ከአስተዳደር አካል የተላከ ደብዳቤ

የተወደዳችሁ ወንድሞችና እህቶች:-

ይህን ደብዳቤ ስንጽፍላችሁ ከፍተኛ ደስታ ይሰማናል! ለምታሳዩት ፍቅርና የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ልናመሰግናችሁ እንወዳለን። ባለፈው የአገልግሎት ዓመት ብዙ ሥራ መከናወኑን ከ2003 የዓመት መጽሐፍ መመልከት ትችላላችሁ። በዚያ ዓመትም በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ አማካኝነት ሰዎች ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ በማበረታታት ከአንድ ቢልዮን ሰዓት በላይ አሳልፈናል። በሰማይ ከሚኖረው ከታላቁ አምላካችንና አባታችን ጋር አብሮ መሥራት ከፍተኛ ክብር አይደለምን?​—⁠1 ቆ⁠ሮ. 3:​9

ከፊታችን የሚጠብቀንን ሥራ ስናስብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን የአምላክ አገልጋዮች ያሳዩትን ቅንዓትና እምነት መኮረጃችሁን እንደምትቀጥሉ እርግጠኞች ነን። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጳውሎስ የመንግሥቱን ጉዳዮች በማስፋፋት ረገድ በተቻለው መጠን ውጤታማ የመሆን ጉጉት ነበረው። በቆሮንቶስ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች የላከውን የመጀመሪያ ደብዳቤ የጻፈው በኤፌሶን በቆየበት የመጨረሻ ዓመት እንደነበር ከሁኔታዎቹ መረዳት ይቻላል። ቀጥሎ ለማከናወን ስላቀደው ነገር ሲጽፍ “በኤፌሶን . . . እስከ በዓለ ኀምሳ ድረስ እሰነብታለሁ። ሥራ የሞላበት ትልቅ በር ተከፍቶልኛልና ተቃዋሚዎችም ብዙ ናቸው” ብሏል።​—⁠1 ቆሮ. 16:8, 9

ጳውሎስ ወደ መቄዶንያና ወደ ቆሮንቶስ የመጓዝ ዕቅድ ነበረው። ይሁን እንጂ ለተወሰነ ጊዜ እዚያው ኤፌሶን በመቆየት ጠቃሚ ሥራ ማከናወን የሚያስችለው አጋጣሚ እንደተከፈተለት አስተዋለ። ጳውሎስ ሁኔታዎችን እንዳመጣጣቸው የማስተናገድ ልማድ ነበረው። በመሆኑም በኤፌሶን የመንግሥቱን ጉዳዮች ለማስፋፋት የሚያስችለው ጥሩ አጋጣሚ መፈጠሩን ሲመለከት ፕሮግራሙን ከዚህ አኳያ አስተካክሏል። ጳውሎስ ሥራ የሞላበት ትልቅ በር ስለተከፈተለት በአጋጣሚው ለመጠቀም ልባዊ ፍላጎት ነበረው።

በተከፈተለት በር መግባቱ ምሥራቹን በመስበክም ሆነ በኤፌሶን የሚገኘውን ጉባኤ በማጠናከር ረገድ ብዙ መሥራት ይጠይቅበታል ማለት ነው። ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ ለኤፌሶን ጉባኤ ሽማግሌዎች እንዲህ ብሏቸዋል:- “ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ንስሐንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ለአይሁድና ለግሪክ ሰዎች እየመሰከርሁ በጉባኤም በየቤታችሁም አወራሁላችሁና አስተማርኋችሁ እንጂ፣ ከሚጠቅማችሁ ነገር አንዳች ስንኳ አላስቀረሁባችሁም።”​—⁠ሥራ 20:20, 21

በተመሳሳይም አብዛኞቻችሁ በተከፈተላችሁ የአገልግሎት አጋጣሚ በሚገባ ተጠቅማችኋል። ባለፈው የአገልግሎት ዓመት ውስጥ በአንድ ዓይነት የአቅኚነት አገልግሎት ለመካፈል ሲሉ በአማካይ 798, 938 የሚሆኑ አስፋፊዎች ሁኔታቸውን አመቻችተዋል። አንዳንዶቻችሁ በሚስዮናዊነት ለማገልገል ከምትኖሩበት አገር ርቃችሁ ሄዳችኋል። በተመደባችሁበት ቦታም ምሥራቹን በቅንዓት በመስበክና ጉባኤዎችን በማጠናከር ላይ ትገኛላችሁ። ሌሎቻችሁ በአካባቢያችሁ የሚኖሩ የውጭ አገር ዜጎችን መርዳት እንድትችሉ ሌላ ቋንቋ ተምራችኋል። ሌሎች ደግሞ ገለልተኛ በሆኑ ክልሎችና የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉባቸው ቦታዎች ለማገልገል ሁኔታዎቻቸውን አስተካክለዋል። አንዳንዶች በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታቸው ወይም ውጤታማ ምሥክርነት መስጠት በሚቻልባቸው በስልክ እንደ መመስከር ባሉ ሌሎች ዘርፎች ሥራ የሞላበት ትልቅ በር እንደተከፈተላቸው ተገንዝበዋል። በየትኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ የአምላክ ሕዝቦች በማንኛውም ቦታ ለሚገኙ ሰዎች የእውነትን እውቀት ለማካፈል የሚያስችሏቸውን አጋጣሚዎች በንቃት እንደሚከታተሉ ከዓለም ዙሪያ የተገኙ ተሞክሮዎች ያሳያሉ።

ይሖዋ የምታደርጉትን ጥረት እንደሚመለከትና እንደሚደሰትበት ፈጽሞ አትጠራጠሩ። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ “ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለም” ይላል። (ዕብ. 6:10) ንጹሑን አምልኮ ለማስፋፋት የሚያስችሏችሁን አጋጣሚዎች በንቃት መከታተላችሁን ቀጥሉ። አንዳንዶቻችሁ በአገልግሎት የምታደርጉትን ተሳትፎ ለማሳደግ ትችሉ ይሆናል። ሁላችንም በአገልግሎታችን ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን ጥረት ማድረግ እንችላለን።

የስብከት ተልዕኳችንን ስንፈጽም ተቃውሞ ማጋጠሙ አይቀርም። ጳውሎስ ሥራ የሞላበት ትልቅ በር እንደተከፈተለት ከተናገረ በኋላ “ተቃዋሚዎችም ብዙ ናቸው” በማለት እንደጻፈ አስታውስ። ጳውሎስ ተቃውሞ ያጋጠመው ከአይሁዳውያንም ሆነ ከአሕዛብ ወገን ሲሆን አንዳንዶቹ በግልጽ ሲያሳድዱት ሌሎቹ ደግሞ በተንኮል አሲረውበት ነበር።​—⁠ሥራ 19:​24-28፤ 20:​18, 19

በዛሬው ጊዜ እኛም ተመሳሳይ ሁኔታ ያጋጥመናል። የዚህ ክፉ ሥርዓት ጥፋት እየተቃረበ ሲመጣ ተቃውሞው እያየለ እንደሚሄድ እንጠብቃለን። ሰይጣን “በታላቅ ቁጣ” የተሞላ ከመሆኑም በላይ ቁጣው ያነጣጠረው አምላክን በሚያገለግሉ ሰዎች ላይ ነው። (ራእይ 12:​12) ሰይጣን “የዚህ ዓለም ገዥ” መሆኑን ፈጽሞ አትዘንጉ። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ ብሏቸዋል:- “ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል።”​—⁠ዮሐ. 14:30፤ 15:19

ማንም ሰው በአምላክ ላይ ያለንን እምነት እንዲያዳክምብን ወይም የስብከት እንቅስቃሴያችንን እንዲያቀዘቅዝብን ላለመፍቀድ ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል። ተቃዋሚዎች ጥቃት መሰንዘራቸውንና በእኛ ላይ ማሴራቸውን እንደሚቀጥሉ እንገነዘባለን። ይሁንና ኢየሱስ ሰይጣንንና ግብረ አበሮቹን ይሖዋ በቀጠረው ጊዜ እንደሚያጠፋቸው ትምክህት በማሳደር የመንግሥቱን ምሥራች በጽናት መስበካችንን እንቀጥላለን። ተቃዋሚዎች የሐዋርያው ጳውሎስን የስብከት እንቅስቃሴ ለማስቆም ያደረጉት ሙከራ እንዳልተሳካላቸው ሁሉ ዛሬም የይሖዋ አገልጋዮች የሚያከናውኑትን ሥራ ማስቆም አይችሉም። የሰይጣን ቁጣና የዓለም ጥላቻ ቢኖርም የይሖዋ መንፈስ በሕዝቦቹ መካከል በኃይል እየሠራ ነው። የምሥራቹ ሰባኪዎች ቁጥር አዲስ ጭማሪ በማሳየት 6, 304, 645 መድረሱን ማወቁ እጅግ ያስደስታል!

የይሖዋን መንግሥት ጉዳዮች ለማስፋፋት የሚያስችሏችሁን አጋጣሚዎች በሚገባ መጠቀማችሁን እንድትቀጥሉ በጸሎታችን እናስባችኋለን። “እጅ ለእጅ” ተያይዘን ልዑሉን አምላክ ይሖዋን ስናገለግል በግለሰብ ደረጃ ለእያንዳንዳችሁ እንደምናስብላችሁ እርግጠኛ ሁኑ።​—⁠ሶፎ. 3:​9

ወንድሞቻችሁ፣

የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ