መልካም ለማድረግ የምትቀኑ ሁኑ!
1 በዚህ ዓመት በሚከበረው የመታሰቢያ በዓል ሰሞን ‘መልካም ለማድረግ እንድንቀና’ የሚያነሳሱ በርካታ ምክንያቶች አሉን። (1 ጴጥ. 3:13) ዋነኛው ምክንያት የኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ነው። (ማቴ. 20:28፤ ዮሐ. 3:16) ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህን አስመልክቶ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፣ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ።” (1 ጴጥ. 1:18, 19) ለዚህ ወደር የማይገኝለት የፍቅር መግለጫ ያለን አድናቆት ኢየሱስ “ከዓመፅ ሁሉ እንዲቤዠን፣ መልካሙንም ለማድረግ የሚቀናውን ገንዘቡም የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ፣ ስለ እኛ ነፍሱን” እንደሰጠ በመገንዘብ መልካም ለማድረግ እንድንተጋ ይገፋፋናል።—ቲቶ 2:14፤ 2 ቆሮ. 5:14, 15
2 አምላክን ደስ የሚያሰኘውን ስናደርግ ከእርሱ ጋር ጥሩ ወዳጅነት የምንመሠርት ከመሆኑም በላይ ፍቅራዊ ጥበቃውን እናገኛለን። ጴጥሮስ አክሎ እንዲህ ብሏል:- “ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው፣ . . . ከክፉ ፈቀቅ ይበል፣ መልካምንም ያድርግ፣ ሰላምን ይሻ ይከተለውም፤ የጌታ ዓይኖች ወደ ጻድቃን ናቸውና፣ ጆሮዎቹም ለጸሎታቸው ተከፍተዋል።” (1 ጴጥ. 3:10-12) በዚህ ክፉ ዘመን ይሖዋ እንደሚንከባከበንና እኛን ‘እንደ ዓይኑ ብሌን’ ለመጠበቅ እርምጃ እንደሚወስድ ማወቃችን ምንኛ የሚያስደስት ነው።—ዘዳ. 32:10፤ 2 ዜና 16:9
3 ጴጥሮስ የጻፈላቸው የጥንት ክርስቲያኖች የተለያዩ ፈተናዎች ቢያጋጥሟቸውም ምሥራቹን በከፍተኛ ቅንዓት አውጀዋል። (1 ጴጥ. 1:6፤ 4:12) ዛሬ ያሉ የአምላክ ሕዝቦች ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። የምንኖረው ‘በሚያስጨንቅ ዘመን’ ውስጥ ቢሆንም ይሖዋ ላሳየን ጥሩነት ያለን አድናቆት የአምላክን ፈቃድ በቅንዓት እንድናከናውን ያነሳሳናል። (2 ጢሞ. 3:1፤ መዝ. 145:7) በዚህ የመታሰቢያ በዓል ሰሞን በትጋት ልንካፈልባቸው የሚገቡ አንዳንድ መልካም ሥራዎችን እንመልከት።
4 ሌሎች በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ ጋብዟቸው:- ወደር ለማይገኝለት የቤዛው ዝግጅት ያለንን አድናቆት መግለጽ የምንችልበት አንደኛው መንገድ በዚህ ዓመት ረቡዕ፣ ሚያዝያ 16 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ በሚከበረው የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ መገኘት ነው። (ሉቃስ 22:19, 20) ባለፈው ዓመት በዓለም ዙሪያ በሚገኙ 94, 600 ጉባኤዎች ውስጥ በጠቅላላው 15, 597, 746 ሰዎች በዚህ በዓል ላይ እንደተገኙ ሪፖርት ተደርጓል! ይህም ከዚያ በፊት በነበረው ዓመት በበዓሉ ላይ ከተገኙት ሰዎች በ220, 000 ይበልጣል።
5 በዚህ ዓመት በበዓሉ ላይ ምን ያህል ሰዎች ይገኙ ይሆን? ይህ በአብዛኛው ሌሎች በበዓሉ ላይ እንዲገኙ ለማበረታታት በምናደርገው ትጋት የተሞላበት ጥረት ላይ የተመካ ይሆናል። ልትጋብዟቸው ያሰባችኋቸውን ሰዎች በሙሉ በዝርዝር ጻፏቸው። ቅድሚያ መስጠት የሚኖርባችሁ ለቤተሰቦቻችሁ አባላት መሆን አለበት። የትዳር ጓደኞቻችሁ የይሖዋ ምሥክር ካልሆኑ በበዓሉ ላይ ቢገኙ ምን ያህል እንደምትደሰቱ ንገሯቸው። ባለፈው ዓመት፣ አንድ ሰው በበዓሉ ላይ የተገኘው ሚስቱ ምን ያህል እንደምትደሰት ስለተገነዘበ እንደሆነ ተናግሯል። ቀጥሎ ደግሞ ዘመዶቻችሁን፣ ጎረቤቶቻችሁን፣ የሥራ ባልደረቦቻችሁን ወይም አብረዋችሁ የሚማሩትን ልጆች ስም ልትጽፉ ትችላላችሁ። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችሁንም መጋበዝ እንደሚኖርባችሁ አትርሱ።
6 በዚህ መንገድ ማስታወሻ ከያዛችሁ በኋላ እያንዳንዳቸውን በግንባር አግኝታችሁ ለመጋበዝ ጊዜ መድቡ። የመታሰቢያውን በዓል የመጋበዣ ወረቀት መጠቀም ትችላላችሁ። የጋበዛችኋቸው ሰዎች በዓሉ የሚከበረው መቼና የት እንደሆነ እንዲያስታውሱ ለመርዳት በመጋበዣው ወረቀት ላይ በዓሉ የሚጀመርበትን ሰዓትና ቦታውን እንዲነበብ አድርጋችሁ ጻፉላቸው። ቀኑ ሲቃረብ የጋበዛችኋቸውን ሰዎች በግንባር አግኝታችሁ ወይም ስልክ ደውላችሁ አስታውሷቸው። በዚህ ቅዱስ በዓል ላይ ብዙ ሰዎች እንዲገኙ የሚቻለንን ጥረት እናድርግ።
7 በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙትን ሰዎች እርዷቸው:- የመታሰቢያው በዓል የሚከበርበት ምሽት አስደሳች ጊዜ ነው። ለወትሮው ወደ ስብሰባዎቻችን የማይመጡ ሰዎች በዚህ በዓል ላይ ይገኛሉ። ሁኔታችሁ በሚፈቅድላችሁ መጠን ቀደም ብላችሁ ለመገኘትና ከበዓሉም በኋላ እዚያው ለመቆየት ጥረት አድርጉ። በበዓሉ ላይ የተገኙ አዳዲስ ሰዎችን ቀርባችሁ ተዋወቋቸው። ሞቅ ያለ ስሜትና የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ይኑራችሁ።—ሮሜ 12:13
8 በመታሰቢያው በዓል ላይ ከተገኙት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ለመርዳት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር ይቻል ይሆን? ተመላልሶ መጠየቅ የማይደረግላቸውን አዳዲስ ሰዎች ተከታትሎ ለመርዳት ስማቸውንና አድራሻቸውን ለማግኘት ሞክሩ። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ፍቅራዊ እርዳታ ከተደረገላቸው በሚቀጥለው ዓመት ከሚከበረው የመታሰቢያ በዓል በፊት ያልተጠመቁ አስፋፊዎች ሊሆኑ ይችላሉ። በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙትን ሰዎች ተመልሳችሁ ስታነጋግሯቸው ሚያዝያ 27 በሚቀርበው ልዩ የሕዝብ ንግግር ላይ እንዲገኙ ጋብዟቸው።
9 ረዳት አቅኚ መሆን ትችሉ ይሆን? ለይሖዋ ያለን ቅንዓት በዓመቱ ውስጥ ልዩ ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴ በሚደረግባቸው ወራት በአገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ እንድናደርግ ይገፋፋናል። ጉባኤው በሙሉ በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ምሥራቹን በቅንዓት ለመስበክ የተቀናጀ ጥረት ማድረጉ ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል።
10 ባለፈው ዓመት፣ 126 አስፋፊዎች የነበሩት አንድ ጉባኤ በመጋቢት ወር ሁሉንም ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ጨምሮ 89 አስፋፊዎች በዘወትር ወይም በረዳት አቅኚነት በመካፈላቸው “ልዩ ወር” እንዳሳለፉ ሪፖርት አድርጓል። የጉባኤው ሽማግሌዎች አስፋፊዎቹ በዚያ ወር ረዳት አቅኚ የመሆን ፍላጎት እንዲያድርባቸው ለማነሳሳት ምን አድርገው ነበር? በተቻለ መጠን በርካታ አስፋፊዎች ረዳት አቅኚ ሆነው እንዲያገለግሉ ማበረታታት የጀመሩት ቀደም ብለው ነበር። ሁሉም የጉባኤው አባላት በአገልግሎት እንዲካፈሉ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ሲባል በቀኑ ውስጥ በዛ ያሉ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎች ተዘጋጅተው ነበር። እናንተም ጥሩ እቅድ በማውጣት በጉባኤያችሁ ተመሳሳይ በረከት ማግኘት ትችላላችሁ።
11 ሁሉም አስፋፊዎች በአገልግሎት እንዲካፈሉ ጥረት አድርጉ:- ለአምላክና ለሰዎች ያለን ፍቅር በየወሩ ምሥራቹን ለሌሎች ለማካፈል የሚያስችል ጊዜ እንድንዋጅ ይገፋፋናል። (ማቴ. 22:37-39) የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቾችና ረዳቶቻቸው በቡድናቸው ውስጥ ያሉት አስፋፊዎች በሙሉ በየወሩ በአገልግሎት እንዲካፈሉ ሊረዷቸው ይገባል። ይህን ማድረግ የሚቻልበት አንዱ ግሩም መንገድ በቡድኑ ውስጥ ከሚገኝ ከእያንዳንዱ አስፋፊ ጋር ለማገልገል አስቀድሞ ዝግጅት ማድረግ ነው። በወሩ መገባደጃ ላይ ይህን ለማድረግ ከመሯሯጥ ይልቅ ቀደም ብሎ መጀመሩ የተሻለ ይሆናል። ይህም ፍቅራዊ እርዳታ ለመስጠት የሚያስችል ተጨማሪ አጋጣሚ ይከፍትላችኋል።
12 በመጽሐፍ ጥናት ቡድናችሁ ውስጥ በጤና እክል ወይም አቅመ ደካማ በመሆናቸው ምክንያት በአገልግሎት ለመካፈል የሚቸገሩ አስፋፊዎች አሉ? አንዳንዶች ከቤት መውጣት የማይችሉ ከሆነ ለመመሥከር ያላቸው አጋጣሚ ውስን እንደሚሆን የታወቀ ነው። ሆኖም ብርሃናቸውን ለማብራት ያላቸውን አጋጣሚ በሚገባ ከተጠቀሙበት ሌሎች መልካም ሥራቸውን በመመልከት ለእውነት ፍላጎት ሊያድርባቸው ይችላል። (ማቴ. 5:16) የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቾች እንደነዚህ ያሉት አስፋፊዎች በመስክ አገልግሎት ያሳለፉትን ጊዜ ከ15 ደቂቃ ጀምሮ የ15 ደቂቃ ድምሮችን መመለስ እንደሚችሉ ማስታወስ ይኖርባቸዋል። እነዚህ ታማኝ አስፋፊዎች በአገልግሎት ያሳለፉትን ያህል ሪፖርት ማድረግ መቻላቸው የሚያበረታታቸው ከመሆኑም በላይ ደስታና እርካታ ያስገኝላቸዋል። ከዚህም በላይ የአምላክ ሕዝቦች በዓለም ዙሪያ ስላደረጉት የአገልግሎት እንቅስቃሴ ትክክለኛ መረጃ ለማጠናቀር ያስችላል።
13 መልካም የሆነውን ለማድረግ የሚተጉ ወጣቶች! ክርስቲያን ወጣቶች የልጅነት ጉልበታቸውን ይሖዋን ለማገልገል ሲጠቀሙበት ማየት እንዴት የሚያስደስት ነው! (ምሳሌ 20:29) ወጣት ከሆንህ ልዩ የአገልግሎት እንቅስቃሴ በሚደረግባቸው በእነዚህ ወራት ለይሖዋ ያለህን ቅንዓት በተግባር ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?
14 እስከ አሁን ድረስ አስፋፊ ካልሆንህ እዚህ መብት ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረግ ትችላለህ። ራስህን እንዲህ እያልህ ጠይቅ:- ‘መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት አለኝ? ስለ አምላክ መንግሥት የመስበክ ፍላጎት አለኝ? አኗኗሬ ምሳሌ የሚሆን ነው? ምሥራቹን ለሌሎች በመስበክ ስለማምንበት ነገር ማስረዳት እችላለሁ? ይህን የማድረግ ልባዊ ፍላጎት አለኝን?’ ለእነዚህ ጥያቄዎች አዎንታዊ መልስ መስጠት ከቻልክ አስፋፊ መሆን እንደምትፈልግ ለወላጆችህ ንገራቸው። ወላጆችህ የአገልግሎት ኮሚቴ አባላት ከሆኑት ሽማግሌዎች መካከል ለአንዱ ሊነግሩልህ ይችላሉ።
15 አስፋፊ ከሆንህ ደግሞ ትምህርት በማይኖርባቸው ቀናት አገልግሎትህን ማስፋት ትችል ይሆን? ብዙ የተጠመቁ አስፋፊዎች ጥሩ ፕሮግራም ስላወጡ እንዲሁም ወላጆቻቸውና ሌሎች እገዛ ስላደረጉላቸው ረዳት አቅኚ ሆነው ማገልገል ችለዋል። ረዳት አቅኚ መሆን የማትችል ከሆነ በመስክ አገልግሎት የምታደርገውን ተሳትፎ ለማሳደግ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ለራስህ ግብ አውጣ። ግብህ በአገልግሎት የምታሳልፈውን ሰዓት ከፍ ከማድረግም በተጨማሪ የአገልግሎትህን ጥራት ማሻሻልንም የሚጨምር ይሁን። ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል ለምታነጋግረው ለእያንዳንዱ ሰው አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ለማንበብ፣ ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርግ በደንብ ተዘጋጅተህ ለመሄድ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር፣ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው ምሥክርነት ወይም በሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች አዘውትረህ በመካፈል አገልግሎትህን ለማስፋት ግብ ማውጣት ትችላለህ። በዚህ ዓመት በሚከበረው የመታሰቢያ በዓል ላይ ጎረቤቶችህን፣ አብረውህ የሚማሩትን ልጆች ወይም ዘመዶችህን ለመጋበዝ ግብ ማውጣት ትችላለህ። በእነዚህ ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች የተሟላ ተሳትፎ ማድረጉ መልሶ የሚክስ ከመሆኑም በላይ በጉባኤው ውስጥ የሚገኙ ሌሎች አስፋፊዎችን እንደሚያበረታታ ምንም ጥርጥር የለውም።—1 ተሰ. 5:11
16 አዲሶች እድገት እንዲያደርጉ እርዷቸው:- ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በኢትዮጵያ በየወሩ 5, 000 የሚያህሉ ሰዎች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እንደሚያጠኑ ሪፖርቶች ያሳያሉ። ከእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መካከል አብዛኞቹ እድገት በማድረግ ራሳቸውን ወስነው ይጠመቃሉ። ይሁን እንጂ እዚህ ግብ ላይ ከመድረሳቸው በፊት የምሥራቹ አስፋፊዎች እንዲሆኑ ልንረዳቸው ይገባል። ይህ አዲሶች የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች እንዲሆኑ በማሠልጠን ረገድ ልንወስደው የሚገባ ወሳኝ እርምጃ ነው። (ማቴ. 9:9፤ ሉቃስ 6:40) አስፋፊ ለመሆን የሚያስፈልገውን ብቃት የሚያሟላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አለህ?
17 ጥናትህ አስፋፊ ለመሆን የሚያስፈልገውን ብቃት ያሟላ እንደሆነና እንዳልሆነ እርግጠኛ መሆን ካልቻልክ የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቹን ወይም የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹን ልታማክር ትችላለህ። ተማሪህን በምታስጠናበት ጊዜ አብረውህ እንዲገኙ ጋብዛቸው። እነዚህ ወንድሞች የተማሪውን መንፈሳዊ እድገት ለመገምገም የሚያስችል ጥሩ ተሞክሮ ስላላቸው ተማሪው ተጨማሪ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ የሚረዱ ሐሳቦች ሊያካፍሉት ይችላሉ።
18 ጥናትህ ያልተጠመቀ አስፋፊ ለመሆን እንደሚፈልግ ከነገረህና አንተም ብቃቱን እንደሚያሟላ ከተሰማህ ለሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹ ንገረው። እርሱም ጥናትህ ብቃቱን ያሟላ እንደሆነ ለማረጋገጥ ሁለት ሽማግሌዎች አንተ በተገኘህበት አገልግሎታችን በተባለው መጽሐፍ ከገጽ 98-9 ባለው ሐሳብ ላይ እንዲያወያዩት ዝግጅት ያደርጋል። (የኅዳር 15, 1988 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ገጽ 17 ተመልከት።) ጥናትህ አስፋፊ እንዲሆን ከተፈቀደለት ሥልጠናውን መጀመር የሚኖርብህ ወዲያውኑ ነው። የመስክ አገልግሎት ሪፖርቱን ለመጀመሪያ ጊዜ ከመለሰ በኋላ ያልተጠመቀ አስፋፊ መሆኑን የሚገልጽ ማስታወቂያ ለጉባኤው ይነገራል። ልዩ የአገልግሎት እንቅስቃሴ በሚደረግባቸው በእነዚህ ወራት በሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣትና በዕድሜ የገፉ አዳዲስ አስፋፊዎች መንፈሳዊ እድገት በማድረግ ይህን አስፈላጊ እርምጃ እንደሚወስዱ ተስፋ እናደርጋለን።
19 እቅድ ማውጣት የተሻለ ሥራ ለማከናወን ያስችላል:- በዚህ ዓመት በሚከበረው የመታሰቢያ በዓል ሰሞን የምናከናውናቸው ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ስኬታማነት የተመካው አስቀድመን እቅድ በማውጣታችን ላይ ነው። (ምሳሌ 21:5) ሽማግሌዎች ትኩረት ሊሰጧቸው የሚገቡ በርካታ ጉዳዮች አሉ።
20 ጉባኤው በመስክ አገልግሎት ጥሩ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ሽማግሌዎች ሳምንቱን ሙሉ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ እንዲኖር ዝግጅት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ይህንን ማደራጀት የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ ኃላፊነት ነው። ጠዋት በማለዳ፣ ከሰዓት በኋላ ወይም አመሻሹ ላይ ተጨማሪ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ማድረግ ይቻል ይሆን? ጉባኤው ስለተደረገው ዝግጅት በማስታወቂያ ሊነገረው ይገባል። ፕሮግራሙን በማስታወቂያ ሰሌዳው ላይ መለጠፍ ጠቃሚ ነው።
21 ሽማግሌዎች ለመታሰቢያው በዓል የሚደረጉ ዝግጅቶችን ከሚያዝያ 16 ቀደም ብለው ሊያጠናቅቁ ይገባል። ይህ ሲባል በመንግሥት አዳራሹ ከሚጠቀሙ ሌሎች ጉባኤዎች ጋር ፕሮግራማቸውን ማስተካከል፣ አዳራሹ የሚጸዳበትን መንገድ ማመቻቸት፣ አስተናጋጆች እንዲሁም ቂጣውንና የወይን ጠጁን የሚያዞሩ ወንድሞች መምረጥ ከዚህም በላይ ቂጣውንና የወይን ጠጁን የሚያዘጋጅ ሰው መመደብ ማለት ነው። የመታሰቢያው በዓል የሚከበርበትን ሰዓትና ቦታ እንዲሁም በሳምንቱ ውስጥ በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ የሚደረግ ለውጥ ካለ ለጉባኤው መነገር ይኖርበታል። እነዚህን ነገሮች ትኩረት ሰጥታችሁ ማከናወናችሁ በዓሉን “በአገባብና በሥርዓት” ለማክበር ያስችላችኋል።—1 ቆሮ. 14:40
22 የቤተሰብ ራሶች በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ቤተሰባቸው የአገልግሎት እንቅስቃሴውን ከፍ ማድረግ ስለሚችልበት መንገድ በቤተሰብ ጥናታቸው ወቅት ሊወያዩ ይችላሉ። መላው ቤተሰባችሁ ረዳት አቅኚ ሆኖ ማገልገል ይችላል? ወይም ደግሞ አንድ ወይም ከዚያ በላይ የቤተሰባችሁ አባላት ረዳት አቅኚ ሆነው እንዲያገለግሉ ልትደግፏቸው ትችላላችሁ? ይህ ካልሆነ ደግሞ በቤተሰብ ሆናችሁ በአገልግሎቱ ተጨማሪ ሰዓት ለማሳለፍ ግብ አውጡ። በቤተሰባችሁ ውስጥ ትንሽ ማበረታቻና ድጋፍ ቢያገኝ ያልተጠመቀ አስፋፊ ሊሆን የሚችል ልጅ አለ? ቤተሰባችሁ በዚህ ዓመት ለሚከበረው የመታሰቢያ በዓል ምን ያህል ሰዎች መጋበዝ ይችላል? ጥሩ እቅድ ማውጣት በረከትና ደስታ ያስገኝላችኋል።
23 የቀረውን ጊዜ በሚገባ ተጠቀሙበት:- ሐዋርያው ጴጥሮስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የአይሁድ ሥርዓት መጨረሻ በመቃረቡ የጥድፊያ ስሜት ሊኖራቸው እንደሚገባ አሳስቧቸው ነበር። (1 ጴጥ. 4:7) ዛሬም ማስረጃዎቹ እንደሚያሳዩት የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ተቃርቧል። መጨረሻው መቅረቡን እንደምናምን በዕለት ተዕለት አኗኗራችን ማሳየት እንችላለን። ቀናተኛ የይሖዋ አገልጋዮች በመሆን አጣዳፊ በሆነው ምሥራቹን የማወጅ ሥራ እንጠመድ።—ቲቶ 2:13, 14
24 በቅንዓት ማገልገል በሚገባን ጊዜ ውስጥ እንደምንኖር ልብ ማለት ይኖርብናል! ይሖዋ ለአንተ፣ ለቤተሰብህ እንዲሁም ለጉባኤው ባደረጋቸው ነገሮች ላይ አሰላስል። ይሖዋ ላደረገልን ነገሮች ልንከፍለው ባንችልም በፍጹም ልባችን ልናገለግለው እንችላለን። (መዝ. 116:12-14) ይሖዋ የምናደርገውን ትጋት የታከለበት ጥረት ይባርከዋል። (ምሳሌ 10:22) ሁላችንም ልዩ የአገልግሎት እንቅስቃሴ በሚደረግበት በዚህ ወቅት ‘መልካም ለማድረግ በመቅናት’ ‘በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እግዚአብሔር በነገር ሁሉ እንዲከበር’ ማድረግ እንችላለን።—1 ጴጥ. 3:13፤ 4:11
[ገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ለመታሰቢያው በዓል ማንን ለመጋበዝ አስበሃል?
□✔ ቤተሰቦችህንና ዘመዶችህን
□✔ ጎረቤቶችህንና የምታውቃቸውን ሰዎች
□✔ የሥራ ባልደረቦችህንና አብረውህ የሚማሩትን
□✔ ተመላልሶ መጠየቅ የምታደርግላቸውንና መጽሐፍ ቅዱስ የምታስጠናቸውን ሰዎች
[ገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙትን ሰዎች እርዷቸው
□✔ ሞቅ ባለ ስሜት ሰላም በሏቸው
□✔ ተከታትላችሁ እርዷቸው
□✔ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑ ጋብዟቸው
□✔ በልዩ የሕዝብ ንግግር ላይ እንዲገኙ ጋብዟቸው
[ገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ምን ለማድረግ ግብ አውጥተሃል?
□✔ የጋበዝከው ሰው በበዓሉ ላይ እንዲገኝ መርዳት
□✔ የምሥራቹ አስፋፊ ለመሆን ጥረት ማድረግ
□✔ በአገልግሎት የተወሰነ ሰዓት ማሳለፍ
□✔ በአንዳንድ የአገልግሎቱ ዘርፎች ማሻሻያ ማድረግ
□✔ ረዳት አቅኚ ሆኖ ማገልገል