ጡረታ መውጣት በአገልግሎት የበለጠ ተሳትፎ ለማድረግ በር ይከፍት ይሆን?
1 ብዙ ሰዎች በውጥረት ከተሞላውና አድካሚ ከሆነው ሰብዓዊ ሥራቸው ጡረታ ወጥተው የሚገላገሉበትን ጊዜ ይናፍቃሉ። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ጡረታ ከወጡ በኋላ ደስታቸው ይጠፋል፣ ስልቹዎች ይሆናሉ፤ እንዲሁም ቶሎ እርጅና ይጫጫናቸዋል። አንድ ሰው ትርጉም ባለው ሥራ ካልተጠመደ የተለያዩ ሐሳቦችን በማውጠንጠን ስለ ራሱ ከልክ በላይ ሊጨነቅ ይችላል። አንድ በብራዚል የሚታተም ጋዜጣ ጡረታ የወጡ የመንግሥት ሠራተኞች ‘እርካታ እንደሌላቸው፣ ብስጩ እንደሆኑ፣ ስጋት እንደሚሰማቸው፣ ሕይወት ትርጉም የለሽ እንደሚሆንባቸው፣ የመንፈስ ጭንቀት እንደሚያድርባቸውና ሕይወታቸው እንዳበቃለት ሆኖ እንደሚሰማቸው’ በምሬት ሲናገሩ እንደሚደመጡ ዘግቧል።
2 ከዚህ በተቃራኒ ግን በርካታ ክርስቲያኖች ይህንን አጋጣሚ በሕይወታቸው ውስጥ ተጨማሪ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ለማከናወን የሚያስችል አዲስ ምዕራፍ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። ስልሳ አምስት ዓመት ከሞላው ከሁለት ሳምንታት በኋላ አቅኚ የሆነ አንድ ወንድም “ባለፉት አሥር ዓመታት በአቅኚነት ስካፈል በሕይወቴ ሙሉ ያላገኘሁትን የተትረፈረፈ በረከት አግኝቻለሁ” በማለት ተናግሯል። አንድ ባልና ሚስት “በዕድሜያችን ውስጥ ወርቃማ የሆኑ ዓመታትን መቁጠር የጀመርነው አቅኚ ከሆንን በኋላ ነው” ብለዋል። በእርግጥም ጡረታ መውጣት ለብዙዎች አገልግሎታቸውን በማስፋት የይሖዋን የተትረፈረፉ በረከቶች ለማግኘት የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል።
3 ጠቃሚ ተግባር በማከናወን ራሳችሁን በሥራ ማስጠመድ:- በአሁኑ ወቅት ጡረታ የወጡ አብዛኞቹ ሰዎች ልጆች ሳሉ እንደዛሬው ሥራ የሚያቀሉ መሣሪያዎች ስላልነበሩ ገና ከልጅነታቸው ከባድ ሥራዎችን መስራት ተምረዋል። ምንም እንኳን ዛሬ ያ የወጣትነት ጉልበታቸው ባይኖርም አሁንም ቢሆን ብዙ ጠቃሚ ነገር ማከናወን ይችላሉ። በአንድ አገር ካሉት አቅኚዎች መካከል 22 በመቶ የሚሆኑት (ወደ 20, 000 ገደማ የሚሆኑ ወንድሞችና እህቶች) ዕድሜያቸው 60 ዓመት ወይም ከዚያ በላይ ነው። እነዚህ በዕድሜ የገፉ ወንድሞችና እህቶች ለስብከቱ ሥራ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። ተሞክሯቸውና አምላካዊ ባሕርያቸው ለየጉባኤዎቻቸው ትልቅ በረከት ነው።—ያዕ. 3:17, 18
4 በክርስቲያናዊው አገልግሎት መጠመድ ለጥሩ ጤንነትና ደስተኛ ሕይወት ለመምራትም አስተዋጽኦ ያደርጋል። ጡረታ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ አቅኚ ሆና ያገለገለች አንዲት የ84 ዓመት እህት እንዲህ ብላለች:- “ፍላጎት ያላቸውን በርካታ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናቴ አእምሮዬ ንቁ ሆኖ እንዲቀጥል አስችሎኛል። መኪና ስለሌለኝ በእግሬ ብዙ እጓዛለሁ። ይህም ለጤንነቴ አስተዋጽኦ አድርጓል።” አቅኚ የሆኑ አንድ አረጋውያን ባልና ሚስት እንዲህ ብለዋል:- “በአገልግሎት መካፈላችን በአእምሮም ሆነ በአካል ጤናሞች እንድንሆን ረድቶናል። ሁልጊዜ አብረን ነን። በጣም ደስተኞች ነን።”
5 ይበልጥ ሰባኪዎች በሚያስፈልጉበት መስክ ማገልገል:- የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ለመሄድ የሚያስችል የገንዘብ አቅም ያላቸው ጡረታ የወጡ አንዳንድ ክርስቲያኖች ወደ እነዚህ አካባቢዎች ሄደው ለማገልገል ፈቃደኞች ሆነዋል። ሌሎች ደግሞ የውጭ አገር ቋንቋ በሚነገርበት መስክ በመሥራት አገልግሎታቸውን አስፍተዋል። እነዚህ ቀናተኛ አስፋፊዎች እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ሁሉ “በወንጌልም ማኅበረተኛ እሆን ዘንድ ስለ ወንጌል ሁሉን አደርጋለሁ” ብለው መናገር ይችላሉ።—1 ቆሮ. 9:23
6 አንድ ባልና ሚስት ሁለት ወንዶች ልጆቻቸውን ካሳደጉ በኋላ አቅኚ ሆኑ። ለበርካታ ዓመታት በአቅኚነት ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ የቻይናን ቋንቋ መማር ጀመሩ። በአሁኑ ወቅት በ70ዎቹ ዕድሜ መገባደጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን ሲያገለግሉበት የነበረው የቻይና ቋንቋ ቡድን ጉባኤ ወደ መሆን ደረጃ ማደጉን በመመልከታቸው ተደስተዋል። እንደ እነዚህ ያሉ ባልና ሚስት በረከት ናቸው።
7 ጡረታ የማይወጣበት ሥራ:- ሰብዓዊ ሥራ የሚሠሩ አብዛኞቹ ሰዎች ከጊዜ በኋላ ጡረታ የሚወጡ ቢሆንም ክርስቲያኖች ከአምላክ አገልግሎት ጡረታ አይወጡም። ሁሉም ክርስቲያኖች ‘እስከ መጨረሻው’ በታማኝነት መጽናት አለባቸው። (ማቴ. 24:13, 14) እርግጥ ነው፣ አንዳንዶች ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ የቀድሞውን ያህል በይሖዋ አገልግሎት መካፈል አይችሉ ይሆናል። ያም ሆኖ አቅማቸው የፈቀደላቸውን ያህል በሙሉ ልብ ሲያገለግሉ ማየት እንዴት የሚያበረታታ ነው! ይሖዋ ድካማቸውንና ለስሙ ያሳዩትን ፍቅር እንደማይረሳ የአምላክ ቃል ማረጋገጫ ይሰጣል።—ሉቃስ 21:1-4፤ ዕብ. 6:10
8 ጡረታ ወደምትወጣበት ዕድሜ እየተቃረብክ ከሆነ በዚህ አጋጣሚ የተሻለ ነገር ለማከናወን ለምን በጸሎት አታስብበትም? ጡረታ መውጣትህ አገልግሎትህን በማስፋት ይሖዋን ማወደስና ብዙ በረከት ማግኘት የምትችልበት አጋጣሚ ይከፍትልህ ይሆናል።—መዝ. 148:12, 13