ስለ ይሖዋ ድንቅ ሥራዎች መናገራችሁን ቀጥሉ
1. አንተ በተለይ የምታደንቃቸው አንዳንድ የይሖዋ ድንቅ ሥራዎች የትኞቹ ናቸው?
1 ታላቁ አምላካችን ይሖዋ አቻ የለውም! ዳዊት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ! ብዙ አስደናቂ ነገሮችን አድርገህልናል፤ ከአንተ ጋር ሊወዳደር የሚችል ማንም የለም።” (መዝ. 40:5 የ1980 ትርጉም ) ይሖዋ ካከናወናቸው ድንቅ ሥራዎች መካከል አጽናፈ ዓለሙን መፍጠሩ፣ መሲሐዊውን መንግሥት ማቋቋሙ፣ ለሕዝቦቹ ያሳየው ፍቅራዊ ደግነትና ዓለም አቀፉ የስብከት ዘመቻ ይገኙበታል። (መዝ. 17:7, 8፤ 139:14፤ ዳን. 2:44፤ ማቴ. 24:14) ለይሖዋ ያለን ፍቅርና ላደረገልን ነገሮች በሙሉ ያለን አድናቆት ለሌሎች ስለ እርሱ እንድንናገር ይገፋፋናል። (መዝ. 145:5-7) የአገልግሎት ክልሎቻችንን ለመሸፈን ልዩ ዘመቻ የምናደርግባቸው የመጋቢት፣ የሚያዝያና የግንቦት ወራት በዚህ ሥራ የበለጠ ተሳትፎ ለማድረግ የሚያስችል አጋጣሚ ይከፍቱልናል።
2. ረዳት አቅኚ በመሆን ምን ጥቅሞች እናገኛለን?
2 ረዳት አቅኚ በመሆን:- ልዩ እንቅስቃሴ በምናደርግባቸው በእነዚህ ወራት በአንዱ ወይም በሁለቱ በአገልግሎት ላይ 50 ሰዓት ለማሳለፍ ፕሮግራምህን ማስተካከል ትችላለህ? ማንኛውንም ዓይነት ማስተካከያ ብታደርግ በውጤቱ እንደምትደሰት አያጠራጥርም። (ኤፌ. 5:16) ብዙ አስፋፊዎች ረዳት አቅኚ መሆናቸው የአገልግሎታቸውን ጥራት እንዲያሻሽሉ እንደረዳቸው ተገንዝበዋል። ከቤት ወደ ቤት በማገልገል ረገድ ይበልጥ ድፍረት ያገኙ ከመሆኑም በላይ መጽሐፍ ቅዱስን በተሻለ መንገድ የመጠቀም ችሎታቸውን አዳብረዋል። በአገልግሎት ላይ ሰፊ ጊዜ ማሳለፋቸው ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ተከታትሎ ለመርዳት ያስቻላቸው ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ኖሯቸው የማያውቁ አስፋፊዎች እንኳን ረዳት አቅኚ ሲሆኑ ጥናት ማግኘት ችለዋል። ረዳት አቅኚነት ሌሎችን ለመርዳት ከፍተኛ ጥረት ማድረግን ስለሚጨምር ደስታ ያስገኛል።—ሥራ 20:35
3. አንዳንድ አስፋፊዎች በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥር እያሉም እንኳን ረዳት አቅኚ መሆን የቻሉት እንዴት ነው?
3 ረዳት አቅኚ ለመሆን ሁኔታዬ አይፈቅድልኝም የሚል መደምደሚያ ላይ ለመድረስ አትቸኩል። ሁለት ልጆችና የሙሉ ቀን ሥራ ያለው አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ባለፈው ዓመት ረዳት አቅኚ ሆኖ ነበር። እንዴት ሊሳካለት ቻለ? ከሰኞ እስከ አርብ ሥራ ላይ ስለሚውል ቅዳሜና እሁድ ረጅም ሰዓት ለማገልገል እቅድ ያወጣ ሲሆን በተለይ ቅዳሜ ከጠዋቱ 1:00 ጀምሮ በመንገድ ላይ ምሥክርነት በመስጠቱ ሥራ ይካፈል ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች በርካታ አስፋፊዎችም በረዳት አቅኚነት ያገለገሉ ሲሆን እርስ በርስ ይረዳዱና ይበረታቱ ነበር። በአንድ ሌላ ጉባኤ ደግሞ አንዲት የ99 ዓመት እህት ረዳት አቅኚ የሆነች ልጃቸው ካበረታታቻቸው በኋላ በግንቦት ረዳት አቅኚ ለመሆን ወሰኑ። እኚህ አረጋዊት እህት ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግሉና መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት ሲሄዱ ሌሎች የጉባኤው አባላት ተሽከርካሪ ወንበራቸውን እየገፉ ረድተዋቸዋል። እህት ስልክ በመደወል፣ በመንገድ ላይ በማገልገልና ደብዳቤ በመጻፍ በምሥክርነቱ ሥራ ተካፍለዋል። ይህን ሁሉ ማድረግ የቻሉት በራሳቸው ብርታት ሳይሆን በይሖዋ እርዳታ እንደሆነ ተገንዝበዋል።—ኢሳ. 40:29-31
4. ረዳት አቅኚ ለመሆን ፕሮግራም ስናወጣ ምን ነገሮችን ግምት ውስጥ ልናስገባ እንችላለን?
4 ከሁኔታህ ጋር የሚስማማ ፕሮግራም አውጣ። በዚህ ርዕስ ሥር ለናሙናነት የቀረቡት ፕሮግራሞች ይረዱህ ይሆናል። ሠራተኛ ነህ ወይስ ተማሪ? በዋነኝነት ቅዳሜንና እሁድን የምታገለግልበት ፕሮግራም ብታወጣ ጥሩ ይሆናል። የጤና ችግር ካለብህና ረጅም ሰዓት ለማገልገል አቅምህ የማይፈቅድልህ ከሆነ በየዕለቱ አጠር አጠር ያለ ሰዓት ለማገልገል የሚያስችልህን ፕሮግራም ብታወጣ የተሻለ ነው። ረዳት አቅኚ የመሆን ፍላጎት እንዳለህ ለሌሎች ንገራቸው። እነርሱም ተመሳሳይ ግብ ያወጡ ይሆናል።
5. ልጆች ልዩ እንቅስቃሴ ለሚደረግባቸው ከመጋቢት እስከ ግንቦት ላሉት ወራት ምን ግብ ማውጣት ይችላሉ?
5 ልጆች ተሳትፎ ማድረግ የሚችሉባቸው መንገዶች:- ልጆች ስለ እርሱ ድንቅ ሥራዎች መናገራቸው ይሖዋን ያስደስተዋል። (መዝ. 71:17፤ ማቴ. 21:16) የተጠመቅህ ልጅ ከሆንክ ትምህርት ቤት ለእረፍት በሚዘጋባቸው ወራት ረዳት አቅኚ መሆን ትችላለህ። ረዳት አቅኚ መሆን የማትችል ከሆነ በእነዚህ ወራት በአገልግሎት ላይ የምታደርገውን ተሳትፎ ለመጨመርና ጥራቱን ለማሻሻል ግብ ማውጣት ትችላለህ? አስፋፊ ባትሆንም ከወላጆችህ ጋር አገልግሎት መውጣት ጀምረህ ከሆነ ያልተጠመቀ አስፋፊ ለመሆን የሚያስፈልገውን ብቃት ለማሟላት ጥረት አድርግ። ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥያቄዎች መልስ በመስጠት ረገድ የተዋጣልኝ መሆን ወይም እንደ ጎለመሱ አስፋፊዎች ጥልቅ እውቀት ሊኖረኝ ይገባል የሚል አመለካከት መያዝ አይኖርብህም። መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ገብተውሃል? አኗኗርህ ከመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር የአቋም ደረጃዎች ጋር ይስማማል? የይሖዋ ምሥክር መሆን ትፈልጋለህ? ከሆነ ወላጆችህን አማክራቸው። ብቃቶቹን የምታሟላ መሆኑን ለማየት እነርሱ በተገኙበት ሽማግሌዎች እንዲያነጋግሩህ ዝግጅት ሊያደርጉልህ ይችላሉ።—አገልግሎታችን የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 98-9 ተመልከት።
6. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የምሥራቹ አስፋፊዎች እንዲሆኑ ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው?
6 ሌሎች በስብከቱ ሥራ እንዲካፈሉ መርዳት:- እድገት በማድረግ ላይ የሚገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ልዩ የአገልግሎት እንቅስቃሴ በምናደርግባቸው በመጪዎቹ ወራት አስፋፊ ለመሆን ብቃቱን ያሟሉ ይሆናል። ጥሩ እድገት በማድረግ ላይ ያለ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ካለህ ለመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቹ ወይም ለአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ ልትነግረው ትችላለህ። ከእነርሱ መካከል አንዱ በጥናቱ ላይ ተገኝቶ በእርግጥ እድገት አድርጎ እንደሆነ ሊያይልህ ይችላል። ተማሪው ብቁ ከሆነና አስፋፊ ለመሆን ፍላጎት ካለው ሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹ አንተ በተገኘህበት ሁለት ሽማግሌዎች እንዲያነጋግሩት ዝግጅት ሊያደርግ ይችላል። (የኅዳር 15, 1988 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 17 ተመልከት።) በአገልግሎት እንዲካፈል ከተፈቀደለት ጊዜ ሳታጠፋ አሠልጥነው።
7. የማያዘወትሩ አስፋፊዎችንና አገልግሎት ያቆሙትን እንዴት መርዳት ይቻላል?
7 የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቾች በየቡድኖቻቸው ውስጥ ላሉ አገልግሎት ያቆሙ ወይም የማያዘወትሩ አስፋፊዎች ልዩ ትኩረት መስጠት ይገባቸዋል። አብረውህ እንዲያገለግሉ ጋብዛቸው። አገልግሎት ካቆሙ ረጅም ጊዜ ከሆናቸው ብቃቱን ያሟሉ እንደሆነ ለማየት በመጀመሪያ ሁለት ሽማግሌዎች ቢያነጋግሯቸው ይመረጣል። (በኅዳር 2000 የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የሚገኘውን የጥያቄ ሣጥን ተመልከት።) ልዩ እንቅስቃሴ በሚደረግባቸው በእነዚህ ወራት ጉባኤው የሚያሳየው ቅንዓት አገልግሎትን ዳግመኛ የሕይወታቸው ዋነኛ ክፍል እንዲያደርጉ ሊያበረታታቸው ይችላል።
8, 9. ሽማግሌዎች ልዩ የአገልግሎት እንቅስቃሴ ለሚደረግባቸው ወራት የአስፋፊዎችን ስሜት ለመቀስቀስ ምን ማድረግ ይችላሉ?
8 የአገልግሎት እንቅስቃሴያችሁን ከፍ ለማድረግ ከወዲሁ ተዘጋጁ:- ሽማግሌዎች በርካታ አስፋፊዎች ረዳት አቅኚ ሆነው እንዲያገለግሉ ከወዲሁ ማበረታቻ መስጠት መጀመር ይኖርባቸዋል። አበረታች ሐሳቦችን በማካፈልና ጥሩ ምሳሌ በመሆን ይህን ማድረግ ትችላላችሁ። (1 ጴጥ. 5:3) የጉባኤው ከፍተኛ የረዳት አቅኚዎች ቁጥር ስንት ነበር? በዚህ ዓመት ከዚያ የበለጡ አስፋፊዎች ረዳት አቅኚ መሆን ይችላሉ? የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቾችና ረዳቶቻቸው በየቡድኖቻቸው የሚገኙት አስፋፊዎች በሙሉ የአገልግሎት እንቅስቃሴያቸውን ከፍ እንዲያደርጉ ለማበረታታት ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። የአገልግሎት የበላይ ተመልካቾች ተጨማሪ የመስክ ስምሪት ስብሰባዎች እንዲደረጉ ፕሮግራም ማውጣት ይችላሉ። የወጣውን ፕሮግራም አስቀድማችሁ ለጉባኤው አስታውቁ። የስምሪት ስብሰባውን የሚመሩ ጥሩ ችሎታ ያላቸው አስፋፊዎች እንዲመደቡና ስብሰባዎቹ በሰዓቱ ተጀምረው በሰዓቱ እንዲያልቁ ማድረግ ይኖርባችኋል። (በመስከረም 2001 የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የወጣውን የጥያቄ ሣጥን ተመልከት።) የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ የስምሪት ስብሰባ በሚደረግባቸው ቦታዎች ላይ በቂ የአገልግሎት ክልል፣ መጽሔቶችና ሌሎች ጽሑፎች እንዲኖሩ ዝግጅት ማድረግ ይገባዋል።
9 ባለፈው ዓመት የአንድ ጉባኤ ሽማግሌዎች ከወራት በፊት አስፋፊዎች ረዳት አቅኚ እንዲሆኑ በግለት ማበረታታት የጀመሩ ሲሆን ከመካከላቸውም ብዙዎቹ ረዳት አቅኚ ለመሆን አመለከቱ። በተጨማሪም በመንገድ ላይ ምሥክርነት ለመስጠት ማለዳ በ11:30፣ ከትምህርት ቤት ለሚወጡ ተማሪዎች ከሰዓት በኋላ በ9:00 ከሥራ ለሚወጡ ሠራተኞች ደግሞ አመሻሹ ላይ በ12:00 ተጨማሪ የመስክ ስምሪት ስብሰባዎችን አዘጋጁ። ለቅዳሜም እንዲሁ ሦስት የመስክ ስምሪት ስብሰባዎች ተዘጋጁ። በዚህም የተነሳ ጉባኤው በሚያዝያ ወር 66 ረዳት አቅኚዎች ነበሩት!
10. እያንዳንዱ ቤተሰብ የአገልግሎት እንቅስቃሴውን ከፍ ለማድረግ ምን ዝግጅት ማድረግ ይችላል?
10 በሚቀጥለው ሳምንት የቤተሰብ ጥናት በምታደርጉበት ጊዜ ለመጪዎቹ ወራት ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ግብ ለምን አታወጡም? የቤተሰብ አባላት በሚገባ ከተባበሩና ጥሩ እቅድ ካወጡ ሁሉም ወይም አንዳንዶቹ ረዳት አቅኚ መሆን ይችሉ ይሆናል። ያም የማይቻል ከሆነ ለወትሮው በአገልግሎት ላይ ከምታሳልፈው የበለጠ ረዘም ያለ ሰዓት ለማገልገል ወይም በሳምንቱ ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜ አገልግሎት ለመውጣት ግብ ማውጣት ትችላለህ። በጉዳዩ ላይ በቤተሰብ ሆናችሁ ጸልዩበት። ይሖዋ የምታደርጉትን ጥረት እንደሚባርክ እርግጠኞች መሆን ትችላላችሁ።—1 ዮሐ. 3:22
11. (ሀ) የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ምን አስደናቂ ነገሮችን አከናውኗል? (ለ) ጉባኤው የመታሰቢያውን በዓል የሚያከብርበትን ጊዜና ቦታ ተናገር።
11 ከሁሉ የላቀው የአምላክ ድንቅ ሥራ:- ይሖዋ ፍቅሩን ለሰው ልጆች ከገለጠባቸው መንገዶች ሁሉ የሚበልጠው ልጁን ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ መስጠቱ ነው። (1 ዮሐ. 4:9, 10) ቤዛው የሰውን ልጆች ከኃጢአትና ከሞት ለመቤዠት የሚያስችል ሕጋዊ መሠረት ጥሏል። (ሮሜ 3:23, 24) የፈሰሰው የኢየሱስ ደም አዲሱን ቃል ኪዳን ያጸናው ሲሆን ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች የአምላክ ልጆች ሆነው እርሱ ባቋቋመው መንግሥት ገዥዎች የመሆን ተስፋ እንዲኖራቸው የሚያስችል መንገድ ከፍቷል። (ኤር. 31:31-34፤ ማር. 14:24) ከዚህም በላይ ኢየሱስ የተከተለው የታዛዥነት ጎዳና የይሖዋን ስም አስቀድሷል። (ዘዳ. 32:4፤ ምሳሌ 27:11) የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል እሁድ ሚያዝያ 4 (በኢትዮጵያ አቆጣጠር ደግሞ መጋቢት 26, 1996) ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ በዓለም ዙሪያ ይከበራል።
12. ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በጌታ እራት ላይ በመገኘታቸው የሚጠቀሙት እንዴት ነው?
12 የጌታ እራት መከበር የይሖዋ ድንቅ ሥራዎች ጎልተው እንዲታዩ ያደርጋል። በዕለቱ የሚቀርበው ንግግር ይሖዋ ላደረገልን የቤዛ ዝግጅት ያለን አድናቆት እንዲጨምር ይረዳናል። በበዓሉ ላይ የሚገኙ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ሌሎች የአምላክ ድንቅ ሥራዎችንም ይመለከታሉ። ይሖዋ ሕዝቦቹ እንዲያሳዩ ያስተማራቸውን አንድነትና የጠበቀ ፍቅር የማየት አጋጣሚ ያገኛሉ። (ኤፌ. 4:16, 22-24፤ ያዕ. 3:17, 18) አንድ ሰው በዚህ ልዩ በዓል ላይ መገኘቱ በአስተሳሰቡ ላይ የጎላ ተጽዕኖ ስለሚኖረው በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች እንዲገኙ እንፈልጋለን።—2 ቆሮ. 5:14, 15
13, 14. ለመታሰቢያው በዓል እነማንን መጋበዝ እንችላለን? እንዴትስ?
13 ሌሎች በበዓሉ ላይ እንዲገኙ መጋበዝ:- ልትጋብዛቸው ያሰብካቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር በመያዝ ከአሁኑ ዝግጅት ማድረግ ትችላለህ። የማያምኑ ዘመዶችህን፣ ጎረቤቶችህን፣ በሥራ ቦታም ይሁን በትምህርት ቤት የምታውቃቸውን፣ ከዚህ በፊት ታስጠናቸው የነበሩትንና አሁን በማጥናት ላይ ያሉትን እንዲሁም ተመላልሶ መጠየቅ የምታደርግላቸውን ሁሉ ጨምረህ መዝግብ። የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቾች አገልግሎት ያቆሙ አስፋፊዎችን መጋበዝ እንዳለባቸው ማስታወስ ይኖርባቸዋል።
14 የመታሰቢያውን በዓል የመጋበዣ ወረቀት መጠቀም የምትችል ሲሆን በዓሉ የሚከበርበትን ሰዓትና ቦታ በታይፕ ወይም በግልጽ በሚነበብ ጽሑፍ አስፍር። አሊያም በመጋቢት 15, 2004 መጠበቂያ ግንብ ወይም በመጋቢት 22, 2004 ንቁ! (እንግሊዝኛ) መጽሔቶች የመጨረሻ ገጽ ላይ የሚገኘውን መጋበዣ መጠቀም ትፈልግ ይሆናል። በዓሉ የሚከበርበት ሚያዝያ 4 ሲቃረብ የጋበዝካቸውን ሰዎች በግንባር አግኝተህ ወይም ስልክ ደውለህ አስታውሳቸው።
15. የመታሰቢያው በዓል በሚከበርበት ምሽት የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?
15 በመታሰቢያው በዓል ላይ:- የመታሰቢያው በዓል በሚከበርበት ምሽት ቀደም ብለህ ድረስ። አዳዲሶችን በደንብ ሰላም በማለት የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አሳይ። (ሮሜ 12:13) ለጋበዝካቸው እንግዶች ልዩ ኃላፊነት እንዳለብህ አትዘንጋ። ባይተዋርነት እንዳይሰማቸው አድርግ፤ እንዲሁም ከሌሎች የጉባኤው አባላት ጋር አስተዋውቃቸው። አጠገብህ እንዲቀመጡ ልታደርግ ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስ ወይም የመዝሙር መጽሐፍ ከሌላቸው ከአንተ ወይም ከሌሎች ጋር እንዲከታተሉ አድርግ። ከበዓሉ በኋላ ጥያቄ ቢኖራቸው ለመመለስ ዝግጁ ሁን። አንዳንዶች በመታሰቢያው በዓል ላይ ሲገኙ የመጀመሪያቸው ከሆነ ስለ መጽሐፍ ቅዱስና ስለ አምላክ ዓላማ ይበልጥ ማወቅ ይፈልጉ እንደሆነ ጠይቃቸው። እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምሩ ጋብዛቸው።
16. በበዓሉ ላይ የተገኙ ሰዎች መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ለመርዳት ምን ማድረግ ይቻላል?
16 በበዓሉ ላይ የተገኙትን መርዳታችሁን ቀጥሉ:- በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙት ሰዎች ከበዓሉ በኋላ ባሉት ሳምንታት ተጨማሪ እርዳታ ማግኘት ያስፈልጋቸው ይሆናል። ይህ ደግሞ በአንድ ወቅት ጉባኤ አዘውትረው ይገኙ የነበሩትን አሁን ግን አልፎ አልፎ ብቻ ብቅ የሚሉትንም ይጨምራል። ሽማግሌዎች እንደነዚህ ያሉ ሰዎች እንዳልተዘነጉ ነቅተው ይከታተላሉ። እድገት እንዳያደርጉ እንቅፋት የሆነባቸው ምን እንደሆነ ለማወቅና የጊዜውን አጣዳፊነት እንዲገነዘቡ ለመርዳት ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። (1 ጴጥ. 4:7) ከአምላክ ሕዝቦች ጋር አዘውትረን እንድንሰበሰብ ቅዱሳን ጽሑፎች የሚሰጡንን ማሳሰቢያ መታዘዛችን የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች እንዲገነዘቡ እርዷቸው።—ዕብ. 10:24, 25
17. ስለ ይሖዋ ድንቅ ሥራዎች መናገራችንን መቀጠል የሚኖርብን ለምንድን ነው?
17 የይሖዋ ሥራዎች በጣም ድንቅ ከመሆናቸው የተነሳ ለዘላለም ብንኖር እንኳን ሙሉ በሙሉ ልንረዳቸው አንችልም። (ኢዮብ 42:2, 3፤ መክ. 3:11) ስለሆነም እርሱን እንድናወድሰው የሚያደርጉን ምክንያቶች አናጣም። በዚህ የመታሰቢያ በዓል ሰሞን አገልግሎታችንን ከፍ በማድረግ ለይሖዋ ድንቅ ሥራዎች ያለንን አድናቆት ማሳየት እንችላለን።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]
ከእነዚህ ፕሮግራሞች አንዱን በመጠቀም ረዳት አቅኚ መሆን ትችላለህ?
መጋቢት እ ሰ* ማ* ረ* ሐ ዓ ቅ ወር ድምር
ሳምንቱን በሙሉ 2 1 1 1 1 1 5 51
ሁለት ቀን 0 5 0 5 0 0 0 50
ቅዳሜና እሁድ ብቻ 5 0 0 0 0 0 8 52
ቅዳሜና እሁድ እና
ሁለት የሥራ ቀኖች 2 0 0 2 0 2 6 50
ሚያዝያ እ ሰ ማ ረ ሐ* ዓ* ቅ Month Total
ሳምንቱን በሙሉ 2 1 1 1 1 1 5 50
ሁለት ቀን 0 0 0 0 5 5 0 50
ቅዳሜና እሁድ ብቻ 5 0 0 0 0 0 8 52
ቅዳሜና እሁድ እና
ሁለት የሥራ ቀኖች 2 0 0 2 0 2 6 50
ግንቦት እ* ሰ* ማ ረ ሐ ዓ ቅ* Month Total
ሳምንቱን በሙሉ 2 1 1 1 1 1 4 51
ሁለት ቀን 0 5 0 0 0 0 5 50
ቅዳሜና እሁድ ብቻ 3 0 0 0 0 0 7 50
ቅዳሜና እሁድ እና
ሁለት የሥራ ቀኖች 2 0 0 2 0 2 5 51
* በወር አምስት