የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • km 2/04 ገጽ 6
  • ከአስተዳደር አካል የተላከ ደብዳቤ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከአስተዳደር አካል የተላከ ደብዳቤ
  • የመንግሥት አገልግሎታችን—2004
የመንግሥት አገልግሎታችን—2004
km 2/04 ገጽ 6

ከአስተዳደር አካል የተላከ ደብዳቤ

የተወደዳችሁ ወንድሞችና እህቶች:-

“ከእግዚአብሔር ከአባታችን፣ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።” (1 ቆ⁠ሮ. 1:3) እስትንፋስ ያለው ሁሉ ለይሖዋ ክብር የሚሰጥበትን ጊዜ ለማየት እጅግ እንናፍቃለን! (መዝ. 150:6) ያንን ታላቅ ቀን በምንጠባበቅበት ጊዜ የአምላክን መንግሥት ወንጌል መስበካችንንና ደቀ መዛሙርት ማድረጋችንን እንቀጥላለን።

በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ በምድር ላይ እያከናወናቸው ካሉት ሥራዎች መካከል ዋነኛው ወንጌሉን መስበክ ነው። (ማር. 13:10) ይሖዋ ይህን ሥራ በትኩረት እንደሚከታተል በሚገባ ስለምናውቅና እያንዳንዱ ሰው ከቤዛው ዝግጅት የመጠቀም አጋጣሚ እንዳለው ስለምንገነዘብ ሥራውን መወጣት እንድንችል በጸሎት እንጠይቀዋለን። (ራእይ 14:6, 7, 14, 15) ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥሙን የታወቀ ነው፤ ሆኖም አገልግሎታችንን ለመፈጸም የሚያስችለንን ‘ከላይ የተሰጠንን ኀይል በመልበሳችን’ ምንኛ አመስጋኞች ነን!​—⁠ሉቃስ 24:49

ያለፈውን የአገልግሎት ዓመት መለስ ብለን ማየታችንና ይሖዋ በታማኝ አገልጋዮቹ አማካኝነት ባከናወነው ሥራ ላይ ማሰላሰላችን የሚያስደስት ነው። የአምላክ ሕዝቦች ከመንፈስ ቅዱስ ባገኙት ኃይል በዓለም ዙሪያ የሚደርስባቸውን ጥላቻ ተቋቁመው የክርስቶስ ዓይነት ፍቅር አሳይተዋል። እንዲህ ያለው ፍቅር ባደረግናቸው የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ታይቷል። ከሰኔ እስከ ታኅሣሥ 2003 ባሉት ወራት ከአንድ መቶ ከሚበልጡ አገሮች የተውጣጡ ልዑካን በስድስት አሕጉራት በተካሄዱ 32 ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ላይ ተገኝተዋል። ሚስዮናውያን፣ ዓለም አቀፍ ፈቃደኛ ሠራተኞችና ከአገራቸው ውጭ የሚያገለግሉ ቤቴላውያን በአውራጃና በብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ላይ ቃለ ምልልስ ተደርጎላቸዋል።

በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ “መልካሚቱን ምድር ተመልከቱ” እና ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ የተባሉትን አዳዲስ ጽሑፎች አግኝተናል። ከዚህ በተጨማሪ በ2004 የአገልግሎት ዓመት ማብቂያ ላይ የአቅኚዎች አገልግሎት ትምህርት ቤት መማሪያ መጽሐፍ ተሻሽሎ እንደሚወጣ ማስታወቂያ ተነግሮ ነበር። ለረጅም ጊዜ በአቅኚነት ሲያገለግሉ የቆዩ በትምህርት ቤቱ የተካፈሉ ወንድሞችና እህቶች ከአዳዲስ አቅኚዎች ጋር ደረጃ በደረጃ በኮርሱ እንዲሳተፉ ይደረጋል።

በአምላክ እርዳታና በሰዎች ልግስና፣ በተለይ የኢኮኖሚ አቅማቸው ውስን በሆነ አገሮች ውስጥ በርካታ የመንግሥት አዳራሾችን መገንባት ተችሏል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የመንፈሳዊ ምግብ ፍላጎት እያደገ በመምጣቱ በበርካታ አገሮች ውስጥ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን የማስፋፋት ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል። በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለው ብሮሹር በአሁኑ ጊዜ በ299 ቋንቋዎች የሚገኝ ሲሆን እስከ አሁን ድረስ 139 ሚሊዮን ቅጂዎች ታትመዋል። ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለው መጽሐፍ በ161 ቋንቋዎች ከ93 ሚሊዮን በሚበልጡ ቅጂዎች፣ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለው ብሮሹር ደግሞ በ267 ቋንቋዎች ከ200 ሚሊዮን በሚበልጡ ቅጂዎች ታትመዋል።

ባለፈው የአገልግሎት ዓመት 258,845 ወንድሞችና እህቶች ሕይወታቸውን ወስነው በመጠመቃቸው በጣም ተደስተናል! የአምላክ መንግሥት ደጋፊዎች መሆናችሁ በአንድ በኩል የሰይጣን ጥቃት ዒላማ ቢያደርጋችሁም በሌላ በኩል ደግሞ በፊታችሁ ያለውን የሕይወት ሩጫ ስትሮጡ የይሖዋን በረከትና መንፈሳዊ ጥበቃ አስገኝቶላችኋል። (ዕብ. 12:1, 2፤ ራእይ 12:17) አዎን፣ “የሚጠብቅህም አይተኛም” የሚል ዋስትና ተሰጥቶናል።​—⁠መዝ. 121:3

“ንቁ . . . ተዘጋጅታችሁ ኑሩ” የሚለው የ2004 የዓመት ጥቅስ ወቅታዊ ነው። (ማቴ. 24:42, 44 የ1954 ትርጉም ) ክርስቲያኖች መጥፊያው በተቃረበው በዚህ ሥርዓት ውስጥ መጻተኞች መሆናቸውን የአምላክ ቃል ይገልጻል። (1 ጴ⁠ጥ. 2:11፤ 4:7) በመሆኑም ሕይወታችንን ቀላል ማድረግና ልባችንን በሚገባ መመርመር እንድንችል ለመንፈሳዊ ነገሮች ትኩረት መስጠት ይገባናል። “ታላቁ ዘንዶ” በእርሱ ሥርዓት ውስጥ እንድንዘፈቅ በማድረግ ሊውጠን ይፈልጋል።​—⁠ራእይ 12:9

ነቅተን መኖር እንድንችል መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበባችን የግድ አስፈላጊ ነው። እንዲህ ማድረጋችን ውሳኔያችንን በተመለከተ ቃላችን ‘“አዎ” ቢሆን አዎ’ እንዲሆንና ‘በመጀመሪያ የነበረንን እምነት እስከ መጨረሻው አጽንተን እንድንይዝ’ ሊረዳን ይችላል። (ያዕ. 5:12፤ ዕብ. 3:14) በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችን የምንኖርበት ዓለም ከማይለወጠው የአምላክ የሥነ ምግባር መሥፈርት ምን ያህል እንደራቀ እንድናስታውስ ይረዳናል። (ሚል. 3:6፤ 2 ጢ⁠ሞ. 3:1, 13) የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት “በሰዎች ጥበብ የተፈጠረውን ተረት” እንድንርቅና ለይሖዋ ታማኝ እንድንሆን ይረዳናል።​—⁠2 ጴ⁠ጥ. 1:16፤ 3:11

ወላጆች፣ ልጆቻችሁን በይሖዋ ምክርና ተግሣጽ ስታሳድጓቸው መንፈሳዊ ግቦች እንዲያወጡና ‘ነቅተው እንዲኖሩ’ አስፈላጊውን እርዳታ እየሰጣችኋቸው ነው? (ኤፌ. 6:4) በምድር ላይ ከኖሩት ሁሉ ጥበበኛ የሆነው ኢየሱስ የወደፊት ሕይወቱን በተመለከተ የነበረው ዓይነት አመለካከት እንዲያዳብሩ እያሠለጠናችኋቸው ነው? ኢየሱስ አቻ የማይገኝለት አናጢ፣ የፈጠራ ሰው ወይም ሐኪም ሊወጣው ይችል ነበር፤ እርሱ ግን የሕይወቱ ዋነኛ ግብ ያደረገው የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ነበር። እርሱ የተወው ምሳሌ ልጆቻችሁ በሕይወታቸው ውስጥ የመንግሥቱን ፍላጎቶች እንዲያስቀድሙ ለመርዳት እንዲያነሳሳችሁ እንመኛለን።

የታማኙን ባሪያ ክፍል የምንወክለው የአስተዳደር አካል አባላት ‘የመንግሥቱን ወንጌል በዓለም ሁሉ እንድንሰብክ’ የተሰጠንን ኃላፊነት መወጣት እንድንችል “እጅግ ብዙ ሰዎች” ላደረጉልን ድጋፍ በጣም አመስጋኞች ነን። (ራእይ 7:9 የ1954 ትርጉም፤ ማቴ. 24:14, 45) እናንት የተወደዳችሁ ወንድሞችና እህቶች፣ ይሖዋ “ሥራችሁን እንዲሁም በፊትም ሆነ አሁን ቅዱሳንን በመርዳት ስለ ስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር” እንደማይረሳ ዋስትና ሰጥቷችኋል። (ዕብ. 6:10) በ2004 የዓመት መጽሐፍ ላይ የሚገኙትን አስደናቂ ተሞክሮዎች ስታነቡና በጋራ ያደረጋችሁት ጥረት ያስገኘውን ውጤት ስትመለከቱ በዓለም አቀፉ የምሥክርነት ሥራ ጠቃሚ አስተዋጽኦ እንዳበረከታችሁ ሊሰማችሁ ይገባል።

‘ወደፊት የምትቀበሉትን ብድራት ከሩቅ መመልከታችሁን’ በመቀጠል የወደፊቱን ጊዜ በድፍረት እንድትጋፈጡ እንመኛለን። ሰዎችም ሆኑ አጋንንት ይህን ብድራት እንዳያሳጧችሁ ተጠንቀቁ። (ዕብ. 11:26፤ ቆላ. 2:18) አዎን፣ ይሖዋ የሚወዱትን ሁሉ ወደ ሕይወት ሙላት እንዲደርሱ እንደሚረዳ እርግጠኞች በመሆን በእርሱ ታመኑ።​—⁠ዮሐ. 6:48-54

ለይሖዋ ክብር ከእናንተ ጋር አብረን መሥራታችን እንደሚያስደስተን ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን።

ወንድሞቻችሁ፣

የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ