ለይሖዋ ምርጣችንን መስጠት
1 ይሖዋ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ሕግ ለእርሱ በመሥዋዕትነት የሚቀርብ እንስሳ ‘እንከን የሌለበት’ እንዲሆን ይደነግግ ነበር። ጉድለት ያለበት እንስሳ ተቀባይነት አልነበረውም። (ዘሌ. 22:18-20፤ ሚል. 1:6-9) በተጨማሪም መሥዋዕት ሲቀርብ ለይሖዋ የሚሰጠው ስቡ ማለትም ምርጥ የሆነው ክፍል ነበር። (ዘሌ. 3:14-16) ይሖዋ የእስራኤል አባትና ጌታ እንደመሆኑ መጠን ምርጥ የሆነው ሊሰጠው ይገባ ነበር።
2 እንደ ጥንቱ ሁሉ ዛሬም አምላክ ለምናቀርብለት መሥዋዕት ጥራት ትኩረት ይሰጣል። አገልግሎታችን ለይሖዋ ተገቢ አክብሮት እንዳለን የሚያሳይ መሆን አለበት። እርግጥ ነው፣ ሁኔታችን ከሰው ወደ ሰው ይለያያል። ቢሆንም ለይሖዋ የምንሰጠው ምርጣችንን እንደሆነና እንዳልሆነ ራሳችንን መመርመራችን ተገቢ ነው።—ኤፌ. 5:10
3 በሙሉ ልብ የሚቀርብ አገልግሎት፦ አገልግሎታችን ይሖዋን የሚያስከብርና የአድማጮቻችንን ልብ የሚነካ እንዲሆን በዘልማድ የሚደረግ መሆን የለበትም። ስለ ይሖዋና ስለ ታላላቅ ዓላማዎቹ የምንናገረው መልእክት በአድናቆት ከተሞላ ልብ የመነጨ መሆን ይኖርበታል። (መዝ. 145:7) ይህ ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብና የግል ጥናት ፕሮግራማችንን በቋሚነት የመጠበቅን አስፈላጊነት ያጎላል።—ምሳሌ 15:28
4 ለይሖዋ ምርጣችንን መስጠት እርሱ ለሰዎች ያለውን ፍቅር መኮረጅንም ይጨምራል። (ኤፌ. 5:1, 2) ለሰዎች ያለን ፍቅር ሕይወት አድን የሆነውን የእውነት መልእክት በተቻለን መጠን ለብዙ ሰዎች ለማዳረስ ጥረት እንድናደርግ ያነሳሳናል። (ማር. 6:34) እንዲሁም ለምናነጋግራቸው ሰዎች ልባዊ አሳቢነት እንድናሳይ ይገፋፋናል። ከመጀመሪያው ውይይታችን በኋላ ስለ እነርሱ እንድናስብና ብዙም ሳንቆይ ተመልሰን እንድንሄድ ያደርገናል። በመንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ አቅማችን በፈቀደው መጠን እንድንረዳቸው ይገፋፋናል።—ሥራ 20:24፤ 26:28, 29
5 ‘የምስጋና መሥዋዕት’፦ ለይሖዋ ምርጣችንን የምንሰጥበት ሌላው መንገድ አገልግሎታችንን በትጋት በማከናወን ነው። አስቀድመን በሚገባ ከተዘጋጀንና ሙሉ ትኩረታችንን በአገልግሎታችን ላይ ካደረግን ጊዜያችንን ውጤታማ በሆነ መንገድ ልንጠቀምበት እንችላለን። (1 ጢሞ. 4:10) ጥሩ ዝግጅት መልእክታችንን ግልጽና አሳማኝ በሆነ መንገድ ለማቅረብ ስለሚያስችለን የምናነጋግራቸው ሰዎች ለመልእክታችን ጥሩ ምላሽ እንዲሰጡ ሊያደርጋቸው ይችላል። (ምሳሌ 16:21) ለሌሎች ምሥራቹን የምንናገረው ከልብ በመነጨ መንፈስ ከሆነ በእርግጥም ‘የምስጋና መሥዋዕት’ ሊባልልን ይችላል።—ዕብ. 13:15