ቲኦክራሲያዊ ዜናዎች
◼ የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ በዎልኪል የሚካሄደው ትልቅ የማተሚያ ሕንጻ ግንባታ ተጠናቅቆ ሥራ መጀመሩን ሪፖርት አድርጓል። እያንዳንዳቸው በሰዓት 90,000 መጽሔቶችን ማተም የሚችሉ ሁለት አዳዲስ የማተሚያ ማሽኖችና 120 ጠንካራ ሽፋን ያላቸውን መጻሕፍት በአንድ ደቂቃ መጠረዝ የሚችሉ መሣሪያዎችም በአዲሱ ሕንጻ ውስጥ ተተክለዋል። የሕትመት ሥራው ወደ ዎልኪል በመዛወሩ በብሩክሊን፣ 360 ፉርማን ጎዳና የሚገኘው ሕንጻ ተሽጧል። በአሁኑ ወቅት ወንድሞች በ360 ፉርማን ጎዳና በሚገኘው ሕንጻ ውስጥ የነበሩትን የተለያዩ ዲፓርትመንቶች በ117 አዳምስ ጎዳና ላይ ወደሚገኘው ሕንጻ ለማዛወር እንዲቻል ከፍተኛ የእድሳት ሥራ እያከናወኑ ነው።
የሕትመት ሥራው ወደ ዎልኪል በመዛወሩ ምክንያት ወደ 300 የሚጠጉ ወንድሞችና እህቶች ከብሩክሊን ወደ ዎልኪል ተዛውረዋል። በተጨማሪም በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ የኮምፒውተር ፕሮግራሞችንና ከዚያ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ይሠሩ የነበሩ 100 የሚያህሉ ፈቃደኛ ሠራተኞችም ከዎልኪል ወደ ብሩክሊን የተዛወሩ ሲሆን ከዚህ በኋላ ኢንፎርሜሽን ሲስተምስ የተባለው ዲፓርትመንት አብዛኛውን ሥራውን የሚያከናውነው በብሩክሊን ይሆናል።