ከይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል የተላከ ደብዳቤ
በመጪው አዲስ ሥርዓት ደፍ ላይ የምንገኝ እንደመሆኑ መጠን ይሖዋን መጠበቃችን አጣዳፊ ጉዳይ ነው። (ሶፎ. 3:8) ነቢዩ ዳንኤል “ምሥጢር የሚገልጥ አምላክ . . . አለ፣ እርሱም በኋለኛው ዘመን የሚሆነውን . . . አስታው[ቋል]” በማለት ተናግሮ ነበር። (ዳን. 2:28 የ1954 ትርጉም) አስቀድሞ በትንቢት በተነገረው በዚህ ጊዜ ማብቂያ ላይ መኖርና ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ የሚገልጣቸውን ምስጢሮች መረዳት መቻል እንዴት ያለ ልዩ መብት ነው!
ይሖዋ በዚህ አስቸጋሪ ‘የመጨረሻ ዘመን፣’ የእርሱ አምላኪ የሆነ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ከዓለም ዙሪያ የመሰብሰብ ዓላማ እንዳለው ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ በኩል ደረጃ በደረጃ ገልጧል። (ማቴ. 24:45 የ1954 ትርጉም፤ ራእይ 7:9፤ 2 ጢሞ. 3:1) ኢሳይያስ 2:2, 3 ይህ ዓለም አቀፋዊ ሥራ የሚከናወነው “በዘመኑ ፍጻሜ” እንደሆነ ይናገራል። ዓመጽና አለመረጋጋት በነገሰበት በዚህ ዓለም ውስጥ ይህ የመሰብሰብ ሥራ በየዓመቱ መከናወኑን ቀጥሏል።
ኢየሱስ “ንቁ . . . ተዘጋጅታችሁ ኑሩ” በማለት የሰጠውን መመሪያ መታዘዝ አስፈላጊ መሆኑ ባለፈው ዓመት ይበልጥ ጎላ ተደርጎ ተገልጾልን ነበር። (ማቴ. 24:42, 44) በእውነትም “የዘመኑን ምልክት” ለሚያስተውሉትና በዚያም መሠረት እርምጃ ለሚወስዱት ክርስቲያኖች በዓለም ላይ የሚፈጸሙት ነገሮች ትልቅ ትርጉም አላቸው። (ማቴ. 16:1-3) ይሖዋ ሥራውን እንዲያከናውኑ ያደራጃቸውን ሕዝቦቹን ምንም ዓይነት ተቃውሞ ቢያጋጥማቸውም ከእነርሱ ጋር በመሆን ቃሉን ይጠብቃል።
አንዳንዶች ስለ አምላክ መንግሥት እንዳይሰበክ እንቅፋት ለመፍጠር ወይም ሥራውን ለማስቆም የቱንም ያህል ጥረት ቢያደርጉም ወንድሞቻችን እውነትን መናገራቸውንና አንድ ላይ መሰብሰባቸውን አላቋረጡም። (ሥራ 5:19, 20፤ ዕብ. 10:24, 25) በሰኔ ወር 2004፣ በሞስኮ የሚገኝ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ እንዲታገድና በዚያ ከተማ ያለው ሕጋዊ ድርጅታቸውም እንዲዘጋ የበታች ፍርድ ቤቱ ያሳለፈውን ውሳኔ አጽድቋል። ሆኖም ወንድሞች በዚህ አልተበገሩም፤ አምላክ ምን እንደሚጠብቅባቸው ስለሚያውቁ ከሰው ይልቅ እርሱን ይታዘዛሉ። (ሥራ 5:29) ይሖዋ አገልጋዮቹ አስቸጋሪ ሕግ ነክ ጉዳዮች ቢያጋጥሟቸውም እንደሚመራቸው እርግጠኞች ነን።
በጆርጂያ ሪፑብሊክ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ወንድሞች ንብረታቸውን አጥተዋል፣ በሕዝባዊ ዓመጽ ሳቢያ ብዙ ተሠቃይተዋል እንዲሁም ጽሑፎቻቸው ተቃጥለውባቸዋል። ሆኖም በእነርሱ ላይ የተደገነ ማንኛውም መሣሪያ ከሽፏል። (ኢሳ. 54:17) በ2004 የአገልግሎት ዓመት በጆርጂያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች እንደገና ሕጋዊ እውቅና አግኝተዋል። ያለ ምንም ችግር የአውራጃ ስብሰባዎች ማድረግ ከመቻሉም በላይ ጽሑፎች ወደ አገሪቱ በነጻ እየገቡ ነው። በአስፋፊዎች ቁጥርና በመታሰቢያው በዓል ላይ በተገኙ ሰዎች ረገድ አዲስ ጭማሪ ተገኝቷል።
በሩዋንዳ፣ በቱርክሜኒስታን፣ በአርሜንያ፣ በኤርትራ እንዲሁም በኮሪያ ሪፑብሊክ በእምነታቸው ምክንያት በእስር ላይ የሚገኙ ወንድሞች አሉ። እነዚህ ወንድሞች በደል ቢፈጸምባቸውም መከራ እየደረሰባቸው ያለው ለምን እንደሆነ የሚገልጸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ስለሚያውቁ ጽኑ አቋማቸውን ጠብቀው ይሖዋ ነጻ እስኪያወጣቸው ለመታገሥ ችለዋል።—1 ጴጥ. 1:6፤ 2 ጴጥ. 2:9
ባለፈው ዓመት ስለተፈጸሙ ጎላ ያሉ ክንውኖች ስታነቡ እንዲሁም የ2004ን ዓለም አቀፍ ሪፖርት ስትመለከቱ በይሖዋ በጎነት መደሰታችሁ አይቀርም። (መዝ. 31:19፤ 65:11) ይህ የዓመት መጽሐፍ አምላክን በሚያስደስተው ጎዳና መመላለሳችሁን እንድትቀጥሉ እንደሚያበረታታችሁ ተስፋ እናደርጋለን።—1 ተሰ. 4:1
ሁሉም ዓይነት ሰዎች እውነትን እንዲሰሙ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋችንን አላቆምንም። ለአብነት ያህል፣ መስማት ወይም ማየት የተሳናቸውን በመንፈሳዊ ለመርዳት ቪዲዮዎች፣ ዲቪዲዎችና ሌሎች ነገሮች በምልክት ቋንቋ እንዲሁም የተለያዩ ጽሑፎች በብሬይል ተዘጋጅተዋል። በርካታ የአምላክ መንግሥት አስፋፊዎች በጉባኤያቸው ክልል ውስጥ የሚኖሩ የውጭ አገር ሰዎች የሚናገሯቸውን ቋንቋዎች ተምረዋል።
ከዚህም በላይ በቀላሉ ሊደረስባቸው በማይችሉ ክልሎች ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ገለልተኛ ቡድኖች ተቋቁመዋል። በአንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ሥር ከ7,000 የሚበልጡ አስፋፊዎችን ያቀፉ ከ300 በላይ ገለልተኛ ቡድኖች ይገኛሉ። ይህ አዳዲስ ጉባኤዎችን የማቋቋም ሰፊ አጋጣሚ እንዳለ የሚጠቁም ነው! ከዚህም በላይ በዘንድሮው የአገልግሎት ዓመት በመታሰቢያው በዓል ላይ ከተገኙት 16,760,607 ተሰብሳቢዎች መካከል ከ10 ሚሊዮን የሚበልጡት የይሖዋ ምሥክሮች አይደሉም። ይህም ቢሆን ለመሰብሰብ የደረሰ መከር እንዳለ የሚጠቁም ነው።
ይሖዋ ለሰጠን የተትረፈረፈ በረከትና በየዕለቱ ለሚያደርግልን ፍቅራዊ እንክብካቤ እናመሰግነዋለን። (ምሳሌ 10:22፤ ሚል. 3:10፤ 1 ጴጥ. 5:7) በዚህ “በኋላኛው ዘመን” በአንድነት ወደፊት ስንጓዝ መታመኛችንና መመኪያችን ይሖዋ ነው። ምንም ዓይነት ችግር ቢያጋጥመን “ረዳቴ . . . ይሖዋ ነው” የሚለውን የ2005 የዓመት ጥቅስ እናስታውስ። (መዝ. 121:2 NW) እንደምንወዳችሁና ስለ እናንተ እንደምንጸልይ ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን።
ወንድሞቻችሁ፣
የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል