የጥያቄ ሣጥን
መጽሐፍ ቅዱስ ጋብቻ “በጌታ መሆን አለበት” በማለት የሚሰጠውን ምክር በግለሰብም ሆነ በጉባኤ ደረጃ እንዴት ልንመለከተው ይገባል?
1 ሐዋርያው ጳውሎስ ባሏ የሞተባትን አንዲት ሴት በተመለከተ “የፈለገችውን ሰው ለማግባት ነጻነት አላት፤ ሰውየው ግን በጌታ መሆን አለበት” የሚል ምክር ሰጥቶ ነበር። (1 ቆሮ. 7:39) ይህ አባባል አንድ ሰው የሰጠው የግል አስተያየት አይደለም። ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት የጻፈው እንደመሆኑ መጠን የዚህ ጥበብ ያዘለና ፍቅራዊ ምክር ምንጭ አምላክ ነው። ስለዚህ ክርስቲያኖች ጉዳዩን በቁም ነገር ሊያዩት የሚገባ እንጂ ቸል የሚሉት ወይም አቅልለው የሚመለከቱት አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሰፍሮ የምናገኘው ታሪካዊ ዘገባ ይህን ጉዳይ በሚገባ ያሳያል።
2 አብርሃም ለልጁ ለይስሐቅ ሚስት የመረጠው በዙሪያቸው ካሉት የሐሰት ሃይማኖት ተከታዮች ከሆኑት ከከነዓናውያን ሴቶች አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ምንም ያህል አድካሚ ቢሆንም ከእርሱ በጣም ርቀው ከሚገኙትና እውነተኛውን አምላክ ከሚያመልኩት ዘመዶቹ ለልጁ ሚስት ለማግኘት ጥሯል። በተመሳሳይም ይስሐቅ ያዕቆብን “ምንም ቢሆን ከነዓናዊት ሴት አታግባ” በማለት ነግሮታል። (ዘፍ. 28:1፤ 24:1-67) አብርሃምም ሆነ ይስሐቅ ጋብቻ እንዲሁ ስለተፋቀሩ ብቻ የሚደረግ ጥምረት እንዳልሆነ ተረድተዋል። አማኝ ካልሆነ ሰው ጋር በትዳር መቆራኘት ከባድ ችግር ከማስከተሉም በተጨማሪ ግለሰቡን ከንጹሕ አምልኮ ሊያርቀው ስለሚችል ለይሖዋ የማደርን ጉዳይም ይመለከታል።
3 ይሁን እንጂ ይሖዋን ከማያመልኩ ሰዎች ጋር ጋብቻ ያልመሠረቱት ሁሉም ዕብራውያን አይደሉም። ለምሳሌ ያህል፣ ይሁዳ ለተወሰነ ጊዜ ከቤተሰቦቹ ተለይቶ በኖረበት ወቅት ሳይሆን አይቀርም ከነዓናዊት ሴት አገባ። በመጨረሻስ ውጤቱ ምን ሆነ? ይሁዳ የመሠረተው አቻ ያልሆነ ጋብቻ ሦስት ወንዶች ልጆች ቢያስገኝለትም ይሖዋ በክፋታቸው ምክንያት ሁለቱን ልጆች ቀሥፏቸዋል።—ዘፍ. 38:1-10
4 አምላክ እስራኤላውያንን ለመምራት ሕግ በሰጠበት ወቅት እርሱን ከማያመልኩ ሰዎች ጋር በጋብቻ እንዳይተሳሰሩ አስጠንቅቋቸው ነበር። (ዘዳ. 7:2-4) ይህ መመሪያ ጥበብ ያዘለ ለመሆኑ ሰሎሞን ከደረሰበት ኪሳራ ማረጋገጥ ይቻላል። እጅግ ላቅ ያለ ጥበብ ስለነበረው ይሖዋን የማያመልኩ ሴቶች ማግባቱ የሚያስከትልበትን ማንኛውንም ዓይነት ችግር ወይም ፈተና መቋቋም እንደሚችል ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ አምላክ የሰጠውን ምክር ወደ ጎን ገሸሽ ማድረጉ ሐዘን አስከትሎበታል።—1 ነገ. 11:1-6
5 በመጨረሻም፣ አምላክ የጌታ አገልጋይ ያልሆነን ሰው አታግቡ የሚለውን ምክር በግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በድጋሚ አስጽፏል። በመንፈስ አነሳሽነት የተሰጠው ምክር ‘ወደፊት እህት ወይም ወንድም ሊሆኑ ይችላሉ በሚል ተስፋ ጨዋ እና የተከበረ ሰው ካገኛችሁ ከዚህ ሰው ጋር ተጠናንታችሁ መጋባት ትችላላችሁ’ አይልም። ይልቁንም የአምላክ ቃል “ከማያምኑ ሰዎች ጋር አግባብ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ” በማለት በግልጽ ይናገራል። (2 ቆሮ. 6:14) ያልተጠመቀን ሰው ማግባት ይህን ጠንካራ ምክር እንደ መናቅ ይቆጠራል።
6 በጥቅሉ ሲታይ የይሖዋ ምሥክሮች ይህ ምክር ጥበብ የተንጸባረቀበት እንደሆነና አክብደው ሊያዩት እንደሚገባ ስለሚያምኑ አንድ ሰው ከዚህ መመሪያ ውጭ እንዲሄድ አንዳች ነገር ማድረግ አይፈልጉም። ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት እህት ወይም አንድ ወንድም መንፈሳዊ አቋማቸው በመዳከሙ ምክንያት የይሖዋ ምሥክር ካልሆነ ሰው ጋር መጠናናት ወይም ተቀጣጥረው መጨዋወት ቢጀምሩ ሌሎች የጉባኤው አባላት አማኝ ካልሆነው ወገን ጋር ቅርርብ በመፍጠር ለግንኙነቱ ድጋፍ መስጠት አይፈልጉም። መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያን ያልሆነ ሰው መልካም ባልንጀራ ሊሆን እንደማይችል የሚናገረውን ሐሳብ ይቀበላሉ። (1 ቆሮ. 15:33) ይሁን እንጂ ለወንድማቸው ወይም ለእህታቸው ፍቅር ማሳየታቸውን መቀጠል ይኖርባቸዋል። የተሳሳተ እርምጃ በመውሰድ ላይ ያለው ይህ ክርስቲያን ሰሎሞን የተጓዘበትን አሣዛኝ ጎዳና እንዳይከተል በዘዴ የሚያበረታታ ምክር ሊለግሱት ይችላሉ።—ከ2 ተሰሎንቄ 3:14, 15 ጋር አወዳድር።
7 ይሁንና አንድ የይሖዋ ምሥክር አምላክ የሰጠውን ምክር ንቆ የተጠመቀ ክርስቲያን ካልሆነ ሰው ጋር ለመጋባት ቢወስንስ? አንድ ዓይነት ለየት ያለ ምክንያት ከሌለ በስተቀር በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞች እንዲህ ያለውን ተገቢ ያልሆነ የጋብቻ ጥምረት በመደገፍ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ለመገኘት አይፈልጉም። በተጨማሪም የመንግሥት አዳራሹን ለሠርጉ ሥርዓት እንዲጠቀሙበት አይፈቀድም። በአዳራሹ መጠቀም የሚፈቀደው “በጌታ” ለሚጋቡ ሁለት የተጠመቁ ክርስቲያኖች ነው። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከጉባኤው ጋር ተባብረው ዘወትር አምላክን ለሚያገለግሉና ከጥቂት ጊዜ በኋላ ለሚጠመቁ ሁለት ሰዎች ሊፈቀድላቸው ይችላል። የጉባኤ ሽማግሌዎች ‘አግባብ ባልሆነ መንገድ ለመጠመድ’ ለወሰነ አንድ ክርስቲያን የመንግሥት አዳራሹን ለጋብቻ ሥነ ሥርዓት እንዲጠቀምበት ባለመፍቀድ አምላክ “በጌታ” ብቻ ስለማግባት የሰጠው ምክር ከባድ መሆኑ እንዲስተዋል ሊያደርጉ ይችላሉ።