ነቅተህ ጠብቅ! የተባለውን ብሮሹር ለማጥናት የተደረገ ዝግጅት
በዓለም ዙሪያ ያሉ ጉባኤዎች ነቅተህ ጠብቅ! የተባለውን ብሮሹር በጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት ላይ እንዲያጠኑ ዝግጅት ተደርጓል። እባካችሁ ለመጽሐፍ ጥናት ስትዘጋጁም ሆነ ጥናቱን ስትመሩ በሚከተሉት ጥያቄዎች ተጠቀሙ። በጥናቱ ወቅት ብሮሹሩን እንዲሁም ጊዜ በፈቀደላችሁ መጠን ምዕራፍና ቁጥራቸው ብቻ የተጠቀሱ ጥቅሶችን እያወጣችሁ አንብቡ።
ጥቅምት 24 የሚጀምር ሳምንት
◼ ከገጽ 3-4:- እዚህ ላይ ከተጠቀሱት ክስተቶች ውስጥ በተለይ አንተን የነካህ የትኛው ነው? እነዚህ ክስተቶች አንተ በምትኖርበት አካባቢ ብቻ የተፈጸሙ ነገሮች እንዳልሆኑ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?
◼ ገጽ 5:- አምላክ በእርግጥ ያስብልናል ብለህ እንድታምን የሚያደርግህ ምንድን ነው? ስለ አምላክም ሆነ እርሱ ስለሚያደርጋቸው ነገሮች እንደምናስብ የሚያሳየው ምንድን ነው?
◼ ከገጽ 6-8:- ማቴዎስ 24:1-8, 14 ስለ ዓለማችን ሁኔታ ምን ይናገራል? በ2 ጢሞቴዎስ 3:1-5 ላይ እንደተገለጸው የምንኖረው በየትኛው ዘመን ውስጥ ነው? የመጨረሻ ዘመን ሲባል የምን መጨረሻ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ የአምላክ ቃል ነው ብለህ እንድታምን ያደረገህ ምንድን ነው? የምንሰብከው ስለየትኛው መንግሥት ነው?
◼ ከገጽ 9-10:- በየዕለቱ ስለምናደርጋቸው ውሳኔዎችና በሕይወታችን ቅድሚያ ስለምንሰጣቸው ጉዳዮች በጥንቃቄ ማሰብ ያለብን ለምንድን ነው? (ሮሜ 2:6፤ ገላ. 6:7) በገጽ 10 ባሉት ጥያቄዎች ላይ ስታሰላስል በምታደርጋቸው ነገሮች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ምን ጥቅሶች ትዝ ይሉሃል?
ጥቅምት 31 የሚጀምር ሳምንት
◼ ገጽ 11:- በዚህ ገጽ ላይ ያሉትን ጥያቄዎች በግለሰብ ደረጃ ልናስብባቸው የሚገባን ለምንድን ነው? (1 ቆሮ. 10:12፤ ኤፌ. 6:10-18) ለእነዚህ ጥያቄዎች የምንሰጠው መልስ ኢየሱስ በማቴዎስ 24:44 ላይ የሰጠውን ምክር በቁም ነገር የምንመለከት መሆን አለመሆናችንን የሚጠቁመው እንዴት ነው?
◼ ከገጽ 12-14:- በራእይ 14:6, 7 ላይ የተጠቀሰው “የፍርዱ ሰዓት” ምን ያመለክታል? ‘እግዚአብሔርን መፍራትና ለእርሱ ክብር መስጠት’ ሲባል ምን ማለት ነው? ታላቂቱ ባቢሎን ማን ነች? በእርሷ ላይስ ምን ይደርስባታል? ከታላቂቱ ባቢሎን ጋር በተያያዘ ምን እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል? በፍርዱ ሰዓት ውስጥ የሚከናወን ሌላ ምን ነገር አለ? መጪው መለኮታዊ ፍርድ የሚፈጸምበትን ‘ቀን ወይም ሰዓት’ አለማወቃችን በእኛ ላይ ምን ውጤት ይኖረዋል? (ማቴ. 25:13)
◼ ገጽ 15:- ሉዓላዊነትን በሚመለከት የተነሳው አከራካሪ ጉዳይ ምንድን ነው? ይህስ በግለሰብ ደረጃ እንዴት ይነካናል?
◼ ከገጽ 16-19:- “አዲስ ሰማይ” እና “አዲስ ምድር” የተባሉት ምንድን ናቸው? (2 ጴጥ. 3:13) ይህን ተስፋ የሰጠውስ ማን ነው? በመጪዎቹ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ውስጥ የሚከናወኑት ለውጦች ምንድን ናቸው? በግለሰብ ደረጃ ከዚህ በረከት ተካፋይ መሆን እንችላለን?
ኅዳር 7 የሚጀምር ሳምንት
◼ ከገጽ 20-21:- ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ ተከታዮቹ ስለሽሽት ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል? (ሉቃስ 21:20, 21) ይሁንና መሸሽ የሚችሉት መቼ ነበር? በአፋጣኝ መሸሽ የነበረባቸው ለምንድን ነው? (ማቴ. 24:16-18, 21) ብዙዎች ማስጠንቀቂያውን ችላ ያሉት ለምን ነበር? በቻይና እና በፊሊፒንስ የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተአማኒነት ያላቸውን ማስጠንቀቂያዎች ሰምተው እርምጃ በመውሰዳቸው የተጠቀሙት እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ አሁን ያለው ሥርዓት እንደሚጠፋ የሚሰጠውን ማስጠንቀቂያ ሰምተን እርምጃ መውሰዳችን ይበልጥ አፋጣኝ የሆነው ለምንድን ነው? ከዚህ አጣዳፊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ምን ኃላፊነት አለብን? (ምሳሌ 24:11, 12)
◼ ከገጽ 22-23:- በ1974 በአውስትራሊያ እና በ1985 በኮሎምቢያ ብዙዎች የተሰጣቸውን የአደጋ ማስጠንቀቂያ አክብደው ያላዩት ለምንድን ነው? ውጤቱስ ምን ነበር? አንተ በዚያ ብትኖር ኖሮ ምን እርምጃ ትወስድ ነበር? ለምንስ? በኖኅ ዘመን ኖረን ቢሆን ኖሮ ለተነገረው ማስጠንቀቂያ ተገቢ ምላሽ መስጠት አለመስጠታችንን የሚያሳየው ምን ሊሆን ይችላል? ብዙ ሰዎች በጥንቷ ሰዶምም ሆነ በአቅራቢያዋ መኖር የሚፈልጉት ለምን ነበር? በሰዶም ላይ ስለደረሰው ጥፋት በቁም ነገር ማሰላሰላችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?
ኅዳር 14 የሚጀምር ሳምንት
◼ ከገጽ 24-27:- በገጽ 27 ላይ ያሉትን “ለጥናት የሚረዱ ጥያቄዎች” ተጠቀም።
ኅዳር 21 የሚጀምር ሳምንት
◼ ከገጽ 28-31:- በገጽ 31 ላይ ያሉትን “ለጥናት የሚረዱ ጥያቄዎች” ተጠቀም።
ብሮሹሩን ማጥናታችን ‘ነቅተን እንድንጠብቅና’ ምንጊዜም ዝግጁ ሆነን እንድንኖር ይረዳናል። አገልግሎታችንን የምናከናውንበት መንገድ “እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ክብርም ስጡት፤ ምክንያቱም የፍርዱ ሰዓት ደርሶአል” በማለት ያወጀው መልአክ የነበረው ዓይነት የጥድፊያ ስሜት እንዳለን የሚያሳይ ይሁን።—ማቴ. 24:42, 44፤ ራእይ 14:7