የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው?—እንዴትስ ልታገኘው ትችላለህ? የተባለውን ብሮሹር ለማበርከት የሚረዱ መግቢያዎች
ለቤቱ ባለቤት ሰላምታ ካቀረብክ በኋላ እንዲህ ልትል ትችላለህ:-
“በዛሬው ጊዜ የሰዎች ሕይወት በችግርና በሐዘን የተሞላ መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። አምላክ ሰውን የፈጠረው እንዲህ ያለ ሕይወት እንዲመራ ይመስልዎታል? [መልስ እስኪሰጥህ ጠብቀው።] ይህ ብሮሹር አምላክ ለሰው ልጆችና ለምድር የነበረው የመጀመሪያ ዓላማ ወደፊት ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ያብራራል። [በገጽ 20 እና 21 ላይ ያለውን ሥዕል ተወያዩበት። ከዚያም አንቀጽ 9ን አንብብና ኢሳይያስ 14:24ን እና 46:11ን ጎላ አድርገህ ግለጽ።] ሌላ ጊዜ አምላክ በምድር ላይ ገነትን እንደገና እንደሚያቋቁም የሚናገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ባሳይዎት ደስ ይለኛል።” ብሮሹሩን እንዲወስድ ጋብዘው፤ ከዚያም በሌላ ጊዜ ለመገናኘት ቀጠሮ ያዝ።
ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርግ እንዲህ ልትል ትችላለህ:-
“ባለፈው ጊዜ፣ የአምላክ ዓላማ የሰው ልጆች ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ መሆኑን ነግሬዎት ነበር። [በገጽ 20 እና 21 ላይ ያለውን ሥዕል እንደገና አሳየው።] ኢየሱስ፣ ጴጥሮስና ዳዊት ስለ ገነት ተናግረው እንደነበር ይመልከቱ።” የሰጠኸውን ብሮሹር እንዲያመጣ ጠይቀው። ከዚያም ገጽ 21 እና 22ን ገልጠህ ከአንቀጽ 10-13 ላይ ያሉትን ሐሳቦች አብራራ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምር ግብዣ አቅርብለት፤ ወይም በገጽ 29-30 ላይ ካሉት ንዑስ ርዕሶች አንዱን መሠረት አድርጋችሁ ለመወያየት ቀጠሮ ያዝ።
አንድ ወጣት አስፋፊ እንዲህ ሊል ይችላል:-
“በእኔ ዕድሜ ያሉ ብዙ ወጣቶች ስለ ወደፊቱ ጊዜ ሲያስቡ ብሩህ ተስፋ አይታያቸውም። መጪው ትውልድ የተሻለ ሕይወት ይመራል ብለው ያስባሉ? [መልስ እስኪሰጥህ ጠብቀው።] መጽሐፍ ቅዱስ መላው የሰው ዘር ብሩህ የሆነ የወደፊት ተስፋ እንዳለው ይናገራል። [ብሮሹሩን አውጥተህ በገጽ 31 ላይ ያለውን ሥዕል አሳየውና ለሥዕሉ የተሰጠውን ሐሳብ አንብብ። ከዚያም 2 ጴጥሮስ 3:13ን አንብብ።] ይህ ብሮሹር አምላክ ለሰው ልጆች ስላዘጋጃቸው በረከቶች ማብራሪያ ይሰጥዎታል። [በገጽ 29-30 ላይ ያሉትን ንዑስ ርዕሶች በማጉላት ብሮሹሩን እንዲወስድ ጋብዘው።] በድጋሚ መጥቼ ብጠይቅዎትና አምላክ ጦርነቶችን እንደሚያስወግድ የገባውን ቃል በተመለከተ ባወያይዎት ደስ ይለኛል።” ሌላ ጊዜ ለመገናኘት ቀጠሮ ያዝ።
ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርግ እንዲህ ልትል ትችላለህ:-
“ባለፈው የመጣሁ ጊዜ አምላክ ምድርን እንደገና ገነት ለማድረግ ዓላማ እንዳለው በአጭሩ ነግሬዎት ነበር። [በገጽ 31 ላይ ያለውን ሥዕል እንደገና አሳየው።] አምላክ ጦርነቶችን በሙሉ ለማስወገድ ያለውን ዓላማ በተመለከተ ምን አመለካከት እንዳለዎት ቢነግሩኝ ደስ ይለኛል።” የራሱን ብሮሹር እንዲያመጣ ጠይቀው። ከዚያም በገጽ 29 ላይ ከአንቀጽ 3-6ን አንብባችሁ ተወያዩበት። በሌላ ጊዜ አንቀጽ 7 እና 8ን ለመወያየት ቀጠሮ ያዝ።
በዕድሜ ትልቅ የሆነ አንድ አስፋፊ ከትንሽ ልጅ ጋር ሲያገለግል ራሱንና ልጁን ካስተዋወቀ በኋላ እንዲህ ሊል ይችላል:-
“ፈቃድዎ ቢሆን፣ እገሌ አንድ ሥዕል ሊያሳይዎትና አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ሊያነብልዎት ይፈልጋል። [ልጁ በገጽ 31 ላይ ያለውን ሥዕል ካሳየ በኋላ ለሥዕሉ የተሰጠውን ሐሳብ ያነብባል፤ ከዚያም ራእይ 21:4ን ያነብባል።] ይህ ብሮሹር አምላክ በዛሬው ጊዜ የሚያጋጥሙንን ችግሮች ወደፊት እንዴት እንደሚያስወግዳቸው ማብራሪያ ይሰጣል። [በገጽ 29 እና 30 ላይ ያሉትን ንዑስ ርዕሶች በአጭሩ አጉላ፤ በኋላም ብሮሹሩን እንዲወስድ ጋብዘው።] ተመልሰን ስንመጣ ማንኛውም ዓይነት የጤና ችግር የሚወገድበትን ጊዜ በማስመልከት መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ባሳይዎ ደስ ይለኛል።”
ተመላልሶ መጠየቅ ሲያደርጉ ትልቁ አስፋፊ እንዲህ ሊል ይችላል:-
“ባለፈው ጊዜ ባደረግነው ውይይት ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ማንኛውም ዓይነት የጤና ችግር የሚያበቃበትን ጊዜ በማስመልከት ምን እንደሚል ላሳይዎ እንደምፈልግ ነግሬዎት ነበር። እዚህ ላይ የተጠቀሰውን ሐሳብ ልብ ይበሉ።” የራሱን ብሮሹር እንዲያመጣ ጠይቀው። ከዚያም በገጽ 29 ላይ ከአንቀጽ 9-14 ያሉትን ሐሳቦች ተወያዩባቸው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠና ግብዣ አቅርብለት፤ ወይም ሌላ ጊዜ አንቀጽ 15-17ን እንድትወያዩ ቀጠሮ ያዝ።