ሰዎች ትኩረታቸውን ‘በዓለም ብርሃን’ ላይ እንዲያደርጉ እርዷቸው
1 ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል “በጨለማ የሚኖር ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላ ምድር ለኖሩትም ብርሃን ወጣላቸው” የሚል ትንቢት አስነግሯል። (ኢሳ. 9:2) ይህ “ታላቅ ብርሃን” በአምላክ የገዛ ልጅ ማለትም በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራዎች ተንጸባርቋል። ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለ ያከናወነው የስብከት ሥራና የከፈለው መሥዋዕትነት ያስገኛቸው በረከቶች በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ ይኖሩ የነበሩትን ሰዎች አስደስቷል። በእነዚህ የጨለማ ጊዜያትም ቢሆን ሰዎች የሚፈልጉት እንዲህ ዓይነቱን ብርሃን ነው። የጌታ እራት ሰዎች ትኩረታቸውን ‘በዓለም ብርሃን’ ላይ እንዲያደርጉ የምንረዳበት ልዩ አጋጣሚ ይከፍትልናል። (ዮሐ. 8:12) ባለፈው ዓመት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ኢየሱስ “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” ሲል የሰጠውን ትእዛዝ አክብረው አብረውን በመሰብሰብ ያላቸውን እምነት አሳይተዋል። (ሉቃስ 22:19) የመታሰቢያው በዓል የሚከበርበት ቀን እየቀረበ ባለበት ባሁኑ ወቅት፣ ሰዎች ይሖዋ እንዲበራ ላደረገው ታላቅ ብርሃን ትኩረት እንዲሰጡ ለማድረግ የበኩላችንን ድርሻ ማበርከት የምንችለው እንዴት ነው?—ፊልጵ. 2:15
2 ከልብ የመነጨ አድናቆት ማዳበር:- የመታሰቢያው በዓል ሰሞን ይሖዋና ልጁ የቤዛውን መሥዋዕት በማዘጋጀት ለሰው ልጆች ባሳዩት ታላቅ የፍቅር መግለጫ ላይ ለማሰላሰል የሚያስችል ምቹ አጋጣሚ ይፈጥርልናል። (ዮሐ. 3:16፤ 2 ቆሮ. 5:14, 15) እንዲህ ማድረጋችን ለዚህ ለተቀደሰ በዓል ያለን አድናቆት ይበልጥ እንዲጨምር እንደሚረዳን ምንም ጥርጥር የለውም። ሁሉም የአምላክ ሕዝቦች ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ መመርመር በተባለው ቡክሌት ላይ በወጣው ፕሮግራም መሠረት ለመታሰቢያው በዓል የተመደቡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ለማንበብና ባነበቡት ላይ ለማሰላሰል ጊዜ ይመድባሉ። ቤዛዊ መሥዋዕት ለማቅረብ ባደረገው ዝግጅት አማካኝነት በተንጸባረቁት የይሖዋ ወደር የለሽ ባሕርያት ላይ ማሰላሰላችን፣ እርሱን የመሰለ አምላክ በማግኘታችን እንድንኮራ ያደርገናል። ቤዛው ለእያንዳንዳችን ምን ትርጉም እንዳለው ማሰላሰላችን ልባችን ለአምላክና ለልጁ ባለን ጥልቅ ፍቅር እንዲሞላና የቻልነውን ያህል የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም እንድንጥር ያንቀሳቅሰናል።—ገላ. 2:20
3 ይሖዋ ላደረገልን የመዳን ዝግጅት ያለን የአድናቆት ስሜት ይበልጥ እንዲጨምር ካደረግን፣ ለመታሰቢያው በዓል የሚኖረን ጉጉት ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን፣ ተመላልሶ መጠየቅ ወደምናደርግላቸው ሰዎች፣ ወደ ዘመዶቻችን፣ ጎረቤቶቻችን፣ የትምህርት ቤት ጓደኞቻችን፣ የሥራ ባልደረቦቻችን እንዲሁም በዚህ ልዩ ዝግጅት ላይ እንዲገኙ ወደምንጋብዛቸው ሌሎች ሰዎች ይጋባል። (ሉቃስ 6:45) በመሆኑም ለእነዚህ ሰዎች የመታሰቢያውን በዓል የመጋበዣ ወረቀት እየሰጠህ ለመጋበዝ ልዩ ጥረት አድርግ፤ መጋበዣ ወረቀቱ ቀኑን እንዳይዘነጉት ይረዳቸዋል። አንዳንዶች በመታሰቢያው በዓል ላይ ለመጋበዝ ያሰቧቸውን ሰዎች ላለመርሳት ሲሉ የሁሉንም ስም ዝርዝር በማስታወሻቸው ላይ መጻፉን ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል። እንዲሁም በየዓመቱ አዳዲስ ሰዎችን በዚህ ዝርዝር ላይ ይጨምራሉ። በተደራጀ መልኩ እንዲህ ማድረጋችንና ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ለመጋበዝ የተቻለንን ያህል መጣራችን ይሖዋ አምላክ ለሰጠን “በቃላት ሊገለጥ ስለማይቻል ስጦታ” ያለንን አድናቆት የምንገልጽበት ግሩም መንገድ ነው።—2 ቆሮ. 9:15
4 በአገልግሎት ላይ የምናደርገውን ተሳትፎ መጨመር:- በመጋቢትና በሚያዝያ ወር የአገልግሎት እንቅስቃሴህን ከፍ ለማድረግ ትችላለህ? ‘የክርስቶስን የክብር ወንጌል’ ለሌሎች ለማካፈል የምንተጋ ከሆነ የአምላክን በረከት እንደምናገኝ እርግጠኛ መሆን እንችላለን። የመንፈሳዊ ብርሃን ምንጭ የሆነው ይሖዋ “በጨለማ ብርሃን ይብራ” በማለት አዝዟል። (2 ቆሮ. 4:4-6) የጉባኤ ሽማግሌዎች አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በተለያየ ጊዜና ቦታ የሚደረጉ ተጨማሪ የመስክ ስምሪት ስብሰባዎችን በማዘጋጀት በስብከቱ ሥራ ብዙ ሰዓት ማሳለፍ የሚፈልጉ አስፋፊዎችን ለመደገፍ ቀዳሚ ይሆናሉ። ይህም ምናልባት በማለዳ የመንገድ ላይ ምሥክርነት ለመስጠት አሊያም ከሰዓት በኋላና አመሻሹ ላይ በንግድ አካባቢዎች እንዲሁም በስልክ ለመመሥከር ዝግጅት ማድረግን ሊያጠቃልል ይችላል። የአገልግሎት እንቅስቃሴህን ከፍ ለማድረግ እንዲረዳህ ሊደረስበት የሚችል የሰዓት ግብ አውጥተህ ያሰብከውን ለማሟላት ብርቱ ጥረት ማድረግ ትችላለህ። ብዙዎች ለይሖዋ ምርጣቸውን ለመስጠት ረዳት አቅኚ ሆነው ያገለግላሉ።—ቈላ. 3:23, 24
5 ረዳት አቅኚ መሆን ትችላለህ? ከረዳት አቅኚዎች የሚጠበቀው የሰዓት ግብ ከተቀነሰ ከሰባት ዓመት በላይ ሆኖታል። ይህ ማስተካከያ ብዙዎች ረዳት አቅኚ ሆኖ ማገልገል የሚያስገኘውን በረከት እንዲቀምሱ አስችሏቸዋል። አንተስ ሞክረኸው ታውቃለህ? አንዳንዶች በየዓመቱ ረዳት አቅኚ የመሆን ልማድ አዳብረዋል። በበርካታ ጉባኤዎች ውስጥ በዛ ያሉ አስፋፊዎች አንድ ላይ ረዳት አቅኚዎች ይሆናሉ፤ ይህ ደግሞ ጉባኤው በዓመቱ ውስጥ ከሚያከናውናቸው እንቅስቃሴዎች መካከል ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ይሆናል። በመታሰቢያው በዓል ሰሞን በረዳት አቅኚነት አስደሳች ጊዜ ለማሳለፍ ከወዲሁ ፕሮግራም ማውጣት ትችላለህ? የሚያዝያ ወር አምስት ቅዳሜና እሁዶች እንዲሁም አንዳንድ የበዓል ቀናት ስላሉት ረዳት አቅኚ ለመሆን ያመቻል።
6 የወረዳ የበላይ ተመልካች ጉባኤያችሁን የሚጎበኘው በመጋቢት ወይም በሚያዝያ ነው? ከሆነ ተጨማሪ የሆኑ ልዩ አጋጣሚዎች ይኖሩሃል። ቀደም ብሎ በማስታወቂያ እንደተገለጸው፣ በ2006 የአገልግሎት ዓመት የወረዳ የበላይ ተመልካች በሚጎበኝበት ወር ረዳት አቅኚ ሆነው የሚያገለግሉ በሙሉ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ከዘወትር አቅኚዎች ጋር በሚያደርገው ስብሰባ የመጀመሪያ ክፍል ላይ የመገኘት መብት አላቸው። በዚህ ስብሰባ ላይ የሚሰጡት መንፈሳዊነትን የሚገነቡ ሐሳቦች ብዙዎቹን ረዳት አቅኚዎች የዘወትር አቅኚ ለመሆን እንዲጣጣሩ እንደሚረዳቸው እምነታችን ነው። ከዚህም በላይ በመጋቢት ወር ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? በተሰኘው አዲስ መጽሐፍ ተጠቅመን ሰዎች ወደ መንፈሳዊው ብርሃን እንዲመጡ የመርዳት አስደሳች መብት አለን። በዚህ አዲስ መጽሐፍ ተጠቅመህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ለምን ግብ አታወጣም?
7 ከአንድ ረዳት አቅኚ የሚጠበቀውን 50 ሰዓት ለማሟላት በየሳምንቱ ለ12 ሰዓት ያህል የእውነትን ብርሃን ለሌሎች ለማብራት የሚያስችልህን ተስማሚ ፕሮግራም አውጣ። ከዚህ ቀደም ይህን በማድረግ ጥሩ ውጤት ካገኙ እንዲሁም ከሌሎችም ጋር ተማከር። እንዲህ ማድረግህ እነርሱም ረዳት አቅኚ እንዲሆኑ ያነሳሳቸው ይሆናል። ወጣትም ሆኑ በዕድሜ የገፉ የተጠመቁ አስፋፊዎች ጥሩ የሆነ ፕሮግራም በማውጣት የሚጠበቅባቸውን የሰዓት ግብ በቀላሉ ማሟላት ይችላሉ። ስለ ሁኔታው ጸልይ። ከዚያም የምትችል ከሆነ የራስህን ፕሮግራም በማውጣት ረዳት አቅኚ ሁን።—ሚል. 3:10
8 በርካታ ቤተሰቦች የተቀናጀ ጥረት በማድረግ ከቤተሰባቸው መካከል ቢያንስ አንዱ ረዳት አቅኚ ሆኖ እንዲያገለግል ለመርዳት ችለዋል። አንድ ቤተሰብ፣ በቤት ውስጥ ያሉት አምስት የተጠመቁ አስፋፊዎች በሙሉ ረዳት አቅኚ ሆነው እንዲያገለግሉ ወስኗል። ገና ያልተጠመቁ ሁለት ልጆች ደግሞ የአገልግሎት እንቅስቃሴያቸውን ከፍ ለማድረግ ብርቱ ጥረት አድርገዋል። ቤተሰቡ ይህን ዓይነቱን ተጨማሪ ትጋት በማሳየቱ የተባረከው እንዴት ነው? እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ወሩን አስደሳች በሆነ ሁኔታ አሳልፈናል እንዲሁም የቤተሰቡ አንድነት ይበልጥ እንደጠነከረም ተሰምቶናል። ስለሰጠን ግሩም በረከቶች ይሖዋን እናመሰግነዋለን!”
9 በመጋቢትና በሚያዝያ ወር የምናደርገው ልዩ እንቅስቃሴ ይበልጥ የሚያነቃቃንና ወደ ይሖዋ እንድንቀርብ የሚያስችለን ይሆን? ይህ በአብዛኛው ለአምላክና ለልጁ ያለንን ፍቅር ለማጎልበት እንዲሁም የአገልግሎት እንቅስቃሴያችንን ከፍ ለማድረግ በምናሳየው የግል ጥረት ላይ የተመካ ነው። የሁላችንም ውሳኔ “እግዚአብሔርን በአንደበቴ እጅግ አመሰግናለሁ፤ በታላቅ ሕዝብም መካከል አወድሰዋለሁ” ሲል እንደዘመረው መዝሙራዊ ይሆን ዘንድ እንመኛለን። (መዝ. 109:30) ይሖዋ በመታሰቢያው በዓል ሰሞን የምናደርገውን ቅንዓት የታከለበት እንቅስቃሴ ይባርከዋል። በመሆኑም ብዙዎች ከጨለማ እንዲወጡና ‘የሕይወት ብርሃን እንዲሆንላቸው’ ታላቁን ብርሃን ማብራታችንን እንቀጥል።—ዮሐ. 8:12
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
1. በአምላክ ቃል ውስጥ ስለየትኛው ታላቅ ብርሃን ትንቢት ተነግሯል? ለዚህ ብርሃን ልዩ ትኩረት ለመስጠት የሚያስችለው አጋጣሚስ የትኛው ነው?
2. ለቤዛው ያለንን ከልብ የመነጨ አድናቆት ይበልጥ ማሳደግ የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ ማድረጋችንስ ምን ውጤት ያስገኛል?
3. ለመታሰቢያው በዓል አድናቆት እንዳለን እንዴት ማሳየት እንችላለን?
4. በመጋቢትና በሚያዝያ ወር የአገልግሎት እንቅስቃሴያችንን ከፍ ለማድረግ ምን ሊረዳን ይችላል?
5. ከረዳት አቅኚዎች የሚጠበቀው የሰዓት ግብ በመቀነሱ ብዙዎች የተጠቀሙት እንዴት ነው?
6. ምን ዓይነት አስደናቂ ዝግጅቶች ተደርገውልናል?
7, 8. (ሀ) በረዳት አቅኚነት ለማገልገል የሚያስችል ጥሩ ፕሮግራም ለማውጣት ምን ሊያግዘን ይችላል? (ለ) የቤተሰብ አባሎች የተቀናጀ ጥረት ማድረጋቸው የሚረዳቸው እንዴት ነው? መላው ቤተሰብስ የሚጠቀመው እንዴት ነው?
9. በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ብርሃናችንን ማብራት የምንችለው እንዴት ነው?