በር ላይም ሆነ በስልክ የምናስጠናቸው ሰዎች እድገት እንዲያደርጉ መርዳት
1. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የምንመራበት ዓላማ ምንድን ነው?
1 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር እንዴት ያስደስታል! ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፍላጎት ያለው ሰው ማግኘት የመጀመሪያው እርምጃ ነው። የጥናቱ ዓላማ ግለሰቡን እውነተኛ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር እንዲሆን መርዳት ነው። (ማቴ. 28:19, 20) ታዲያ እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ምን ሊረዳን ይችላል?
2. በር ላይ እንደቆሙ ወይም በስልክ አማካኝነት የሚመራ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሲባል ምን ማለት ነው? ውጤታማ የሆነውስ ለምንድን ነው?
2 ሥራ የሚበዛባቸው ሰዎች:- በዛሬው ጊዜ ሰዎች ሥራ የሚበዛባቸው ሆነዋል። በአንዳንድ ቦታዎች ብዙ ሰዎች ለአንድ ሰዓት ያህል ተቀምጠው መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ፈቃደኛ ላይሆኑ ይችላሉ። እንደነዚህ ዓይነት ሰዎችን ለመርዳት ሲባል በር ላይ እንደቆምን አሊያም በስልክ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንድናስጀምር ብሎም እንድንመራ ማበረታቻ ተሰጥቶናል። ይህ ጥናት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተባለው መጽሐፍ ወይም ይህን በመሳሰሉ ሌሎች ጽሑፎች ላይ በሚገኙ አንድ ወይም ሁለት አንቀጾች ውስጥ ባሉ ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ የሚደረግ ውይይት ሲሆን መጀመሪያ አካባቢ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ የሚወስደው ጊዜ አጭር ነው። በአሁኑ ወቅት ብዙ አስፋፊዎች በር ላይ እንደቆሙ ወይም በስልክ እንዲህ ያለ ጥናት የሚመሩ መሆናቸው እንዴት የሚያስመሰግን ነው!
3. በር ላይ እንደቆምን የምንመራው ጥናት ሰዓቱ ከፍ እንዲል ለማድረግ መጣር ያለብን ለምንድን ነው?
3 ይሁንና በር ላይ እንደቆምን በምንመራው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ብቻ መርካት ይኖርብናል? በፍጹም። ጥናቱ በተጀመረበት ዕለት በር ላይ ረጅም ደቂቃ መቆየታችን ጥሩ ባይሆንም የግንቦት 1990 የመንግሥት አገልግሎታችን በገጽ 4 ላይ “ጥናቱ አንድ ጊዜ ከተጀመረና የቤቱ ባለቤት ፍላጎት ካደገ በኋላ በጥናቱ ላይ ረዘም ላለ ጊዜ መቆየት ይቻላል” የሚል ሐሳብ ሰጥቶ ነበር። እንዲህ ማድረጉ በጣም አስፈላጊ ነው። በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- አንድ በረሃብ የተጠቃ ልጅ የምግብ ፍላጎቱ ወደ ቀድሞው ሁኔታ እስኪመለስ ድረስ መጀመሪያ ላይ አነስተኛ መጠን ያለው ምግብ እንመግበው ይሆናል። ነገር ግን ለረጅም ጊዜ ትንሽ ትንሽ ብቻ እየመገብነው የተሟላ ጥንካሬና ትክክለኛ እድገት ይኖረዋል ብለን እንደማንጠብቅ የታወቀ ነው። በተመሳሳይም መጽሐፍ ቅዱስን የምናስጠናው ሰው እድገት አድርጎ ጎልማሳ ክርስቲያን እንዲሆን ጥናቱ በተገቢው ሥርዓት መከናወን ያለበት ከመሆኑም በላይ ቋሚ መሆን ይኖርበታል።—ዕብ. 5:13, 14
4. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትን ቤት ውስጥ መምራት ምን ጥቅሞች አሉት?
4 ቤት ውስጥ የሚመራ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት:- የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትን በቤት ውስጥ ወይም በሌላ አመቺ ሥፍራ መምራት ተመራጭነት አለው። ይህም የማስተማሩን ሂደት ይበልጥ ቀላል ከማድረጉም ሌላ ተማሪው የአምላክን ቃል እንዲያስተውል ይረዳዋል። (ማቴ. 13:23) እንዲሁም አስተማሪው ትምህርቱን ከተማሪው ሁኔታ ጋር በሚስማማ መንገድ ለማቅረብ ያስችለዋል። ከዚህም በላይ ረጅም ሰዓት ማጥናት እምነት የሚያጠናክረውን የአምላክን ቃል በቂ ጊዜ ሰጥቶ ለመመርመር ይረዳዋል።—ሮሜ 10:17
5. በር ላይ የሚመራን ጥናት ቤት ውስጥ ወደሚመራ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማሸጋገር የሚቻለው እንዴት ነው?
5 በር ላይ የሚመራውን ጥናት ቤት ውስጥ መምራት የሚቻልበትን መንገድ እንዴት ማመቻቸት ይቻላል? ለተወሰኑ ጊዜያት ለጥቂት ደቂቃዎች ካጠናችሁ በኋላ ጊዜ ወስነህ ረዘም ያለ ሰዓት ለማጥናት ለምን ሐሳብ አታቀርብለትም? ወይም እንዲህ የመሳሰሉትን ቀጥተኛ ያልሆኑ ጥያቄዎች መጠቀም ትችላለህ:- “ዛሬ ይህን ክፍል ቁጭ ብለን ለመወያየት የሚያስችል ጊዜ ይኖርሃል?” አሊያም “ይህንን ርዕሰ ጉዳይ ለመወያየት ምን ያህል ሰዓት ብንመድብ ደስ ይልሃል?” ይሁን እንጂ ይህን ሞክረህ ጥረትህ የማይሳካ ከሆነ በጀመርክለት ጥናት ማለትም በር ላይ እንደቆማችሁ ለአጭር ጊዜ በምታደርጉት ጥናት ቀጥሉበት። አመቺ ጊዜ ስታገኝ ግን ጥናቱን ቤት ውስጥ ወደሚመራ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማሸጋገር እንደገና ሞክር።
6. አገልግሎታችንን ማከናወን ያለብን በምን ዓላማ ተነሳስተን መሆን ይገባዋል? በዚህ ክፍል ውስጥ የተሰጡት ሐሳቦች ይህን ዓላማችንን ከግብ ለማድረስ እንዴት ሊረዱን ይችላሉ?
6 ምሥራቹ የሚገባቸውን ሰዎች ስንፈልግ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የምናስጀምርበትንና የምንመራበትን ዓላማ መዘንጋት የለብንም። ግባችን ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ራሳቸውን የወሰኑና የተጠመቁ የይሖዋ አገልጋዮች እንዲሆኑ መርዳት ነው። ይህን ዓላማ በመያዝ አገልግሎታችንን ስንፈጽም ይሖዋ ጥረታችንን እንዲባርከው እንመኛለን።—2 ጢሞ. 4:5