በጥናቶችህ አማካኝነት ጥናት ለማግኘት ሞክረሃል?
በአሁኑ ወቅት ጥናት ካለህ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚያስተምር ለማወቅ የሚፈልጉ ጓደኞች ወይም ዘመዶች ይኖሩት እንደሆነ አሊያም የሚያውቃቸው ሰዎች እንዳሉ ለምን አትጠይቀውም? አብዛኛውን ጊዜ የተወሰኑ ሰዎችን ሊጠቁምህ ይችላል። እነዚህ ሰዎች ጋር ሄደህ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ ግብዣ በምታቀርብበት ጊዜ ጥናትህ ፈቃደኛ ከሆነ እሱ እንደላከህ መጥቀስ ትችላለህ። እንዲህ ልትል ትችላለህ:- “[የጥናትህ ስም] መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቱን የወደደው ሲሆን እርስዎም ያለ ክፍያ ከምናደርገው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራም ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ያስባል።” ከዚያም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ በመጠቀም ጥናቱ እንዴት እንደሚካሄድ አጠር አድርገህ አሳያቸው።
ጥሩ እድገት በማድረግ ላይ ያለ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ካለህ ስለ አምላክ ቃል ማወቅ ለሚፈልጉ ጓደኞቹና ቤተሰቦቹ ጥናቱ እንዴት እንደሚካሄድ እንዲናገር ልታበረታታው ትችላለህ። በጥናቱም ወቅት እንዲገኙ ሊጋብዛቸው ይችላል። ይህ አመቺ ካልሆነ ደግሞ ከእነሱ ጋር ተገናኝተህ ጥናቱ እንዴት እንደሚካሄድ እንድታሳያቸው ቀጠሮ ሊይዝልህ ይችላል። እንዲህ ማድረጉ ተማሪው የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀቱን ለሌሎች ማካፈል እንዲጀምር ሊያበረታታው ይችላል።
በተጨማሪም በቋሚነት ተመላልሶ መጠየቅ የምታደርግላቸው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ባይጀምሩም እንኳ በእነሱ አማካኝነት ጥናት ልታገኝ ትችላለህ። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ስታበረክትላቸው “ይህን ጽሑፍ ማግኘት የሚፈልግ ሌላ የሚያውቁት ሰው ይኖር ይሆን?” ብለህ መጠየቅ ትችላለህ።
የጊዜውን አጣዳፊነት ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ሰዎች ምሥራቹን እንዲሰሙና እንዲቀበሉ መርዳት የምንችልበትን ማንኛውንም መንገድ መጠቀም እንፈልጋለን። ታዲያ አንተስ በጥናቶችህ አማካኝነት ጥናት ለማግኘት ሞክረሃል?