በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች ሊከተሉት የሚገባ አርዓያ
ከይሖዋ ጋር የጠበቀና የቀረበ ዝምድና ነበረው። ሕይወቱን የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ያዋለ ሰው ነበር። ‘አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር በማድረጉ’ ተባርኳል። ይህ ሰው ኖኅ ይባላል፤ ኖኅ በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች ሊኮርጁት የሚገባ ጥሩ ምሳሌ ትቷል። (ዘፍ. 6:9) ኖኅ—አካሄዱን ከአምላክ ጋር አደረገ የተሰኘው የቪዲዮ ፊልም የኖኅ ሕይወት ምን ይመስል እንደነበረ፣ የይሖዋን በረከት ያገኘው ለምን እንደሆነና ግሩም የሆኑ ባሕርያቱን እንዴት መኮረጅ እንደምንችል በዓይነ ሕሊናችን ለመመልከት ይረዳናል።
በዲቪዲ የተዘጋጀው ኖኅ የተባለው ይህ ፊልም ከዚህ በታች ያሉትን ጥያቄዎች ይዟል። ፊልሙን ከተመለከትክ በኋላ የሚከተሉትን ጥያቄዎች በመጠቀም ራስህን ፈትን:- (1) አንዳንድ መላእክት ምን ትክክል ያልሆነ ድርጊት ፈጸሙ? ኔፍሊሞች እነማን ነበሩ? (ዘፍ. 6:1, 2, 4) (2) ሰዎቹ በጣም ክፉ የነበሩት ለምንድን ነው? አምላክስ ስለ ክፋታቸው ምን ተሰማው? (ዘፍ. 6:4-6) (3) ኖኅ ከሌሎቹ ሰዎች የተለየ የነበረው እንዴት ነው? (ዘፍ. 6:22) (4) ክፉዎቹ ሰዎች የጠፉት እንዴት ነበር? (ዘፍ. 6:17) (5) መርከቧ ምን ያህል ትልቅ ነበረች? (ዘፍ. 6:15) (6) ኖኅ መርከብ ከመሥራት በተጨማሪ ምን ሥራ አከናውኗል? የሰዎቹስ ምላሽ ምን ነበር? (ማቴ. 24:38, 39፤ 2 ጴጥ. 2:5) (7) ከእያንዳንዱ የእንስሳ ዝርያ ወደ መርከቧ የገባው ስንት ነበር? (ዘፍ. 7:2, 3, 8, 9) (8) ዝናብ የዘነበው ለስንት ቀናት ነበር? ምድር ሙሉ በሙሉ በውኃ ተጥለቅልቃ የቆየችውስ? (ዘፍ. 7:11, 12፤ 8:3, 4) (9) ኖኅና ቤተሰቦቹ ከጥፋቱ ሊተርፉ የቻሉት ለምንድን ነው? (ዘፍ. 6:18, 22፤ 7:5) (10) መርከቧ ያረፈችው የት ነበር? (ዘፍ. 8:4) (11) ኖኅ ከመርከቧ መውጣት እንደሚችል ያወቀው እንዴት ነበር? (ዘፍ. 8:6-12) (12) ኖኅ ከመርከብ ከወጣ በኋላ ምን አደረገ? (ዘፍ. 8:20-22) (13) ቀስተ ደመናው ምን ያመለክታል? (ዘፍ. 9:8-16) (14) ‘አካሄድን ከአምላክ ጋር ማድረግ’ ሲባል ምን ማለት ነው? (ዘፍ. 6:9, 22፤ 7:5) (15) በገነቲቱ ምድር ላይ ከኖኅ ጋር መገናኘት እንድንችል ከእኛ ምን ይጠበቃል? (ማቴ. 28:19, 20፤ 1 ጴጥ. 2:21)
ታማኝና ታዛዥ ስለነበረው ስለ ኖኅ ከሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ፣ አካሄድህን ከአምላክ ጋር ማድረግም ሆነ ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ያሉትን ሕዝቦቹን ለማዳን ባለው ችሎታ ላይ እምነት ማሳደር ስለምትችልበት መንገድ ምን ትምህርት አግኝተሃል?—ዘፍ. 7:1፤ ምሳሌ 10:16፤ ዕብ. 11:7፤ 2 ጴጥ. 2:9