ክርስቲያኖች ስለ ግርዘት ያላቸው አመለካከት
1 ሐዋርያው ጴጥሮስ “ወዳጆች ሆይ፤ እነዚህን ሁሉ ነገሮች የምትጠባበቁ ስለ ሆናችሁ፣ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ከእርሱ ጋር በሰላም እንድትገኙ ትጉ” በማለት ጽፏል። (2 ጴጥ. 3:14) የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ማሳሰቢያ በሥራ ላይ በማዋል ከግርዘት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ጨምሮ ከማንኛውም ክርስቲያናዊ ያልሆነ ልማድ ይርቃሉ።
2 መጽሐፍ ቅዱስ የወንዶችን መገረዝ አይከለክልም። እንዲያውም ግርዛት ይሖዋ ለእስራኤላውያን ከሰጣቸው ሕጎች መካከል አንዱ ነው። ኢየሱስ እስከሞተበት ዘመን ድረስ ያልተገረዘ ወንድ ርኩስ እንደሆነ ተደርጎ ሲታይ ቆይቷል። ሆኖም ሕጉ ‘ወደ ክርስቶስ የሚያደርስ ሞግዚት’ ብቻ ነበር። በአሁኑ ጊዜ የወንዶች ግርዛት በአምላክ ፊት የተለየ ሞገስ የማያስገኝ ከመሆኑም በላይ አንድ ክርስቲያን የመገረዝ ግዴታ የለበትም።—ገላ. 3:24፤ 5:6
3 በመሆኑም ወላጆች ከጤና አንጻር ወንዶች ልጆቻቸው እንዲገረዙ ከወሰኑ ይህ የግል ጉዳይ ነው። ሆኖም በአንዳንድ አካባቢዎች በተወሰነ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ በርካታ ወንዶች ልጆች በኅብረት የሚገረዙበት ለየት ያለ ቀን ይመደባል። ለተገረዙት ልጆች ክብር ለመስጠትና በማኅበረሰቡ ውስጥ ከፍ ወዳለ ደረጃ እንዲሸጋገሩ ለማበረታታት ሲባል ዘፈንና ጭፈራ ያለበት ድግስ ይዘጋጅላቸዋል። እነዚህ ሥነ ሥርዓቶች ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ሲሆኑ አንድ ክርስቲያን አምላክን በማያስከብረው በዚህ ድርጊት ለመካፈል ፈቃደኛ አይሆንም።
4 ስለ ሴቶች ግርዛትስ ምን ማለት ይቻላል? በአብዛኛው የሴቶችን የጾታ ብልት መቁረጥ በመባል የሚታወቀው ይህ ልማድ አሁንም በበርካታ የአፍሪካ አገሮች የተለመደ ነው። ይህ ግርዛት የሚከናወንባቸው የተለያዩ መንገዶች ቢኖሩም ሁሉም በወጣት ልጃገረዶች ላይ ከባድና አላስፈላጊ ሥቃይ ያስከትላሉ። አንድ ጋዜጣ እንደሚከተለው ሲል ዘግቧል:- “የሴቶች ግርዛት ወዲያውኑ ከሚያስከትላቸው የተለመዱ የጤና እክሎች መካከል ከፍተኛ ሕመም፣ ድንጋጤ፣ ብዙ ደም መፍሰስ፣ በአቅራቢያው ያሉ የሰውነት ክፍሎች መጎዳት፣ የቁስል ማመርቀዝና ሞት ይገኙበታል።” ክርስቲያን ወላጆች እነዚህ ሁኔታዎች በሴት ልጆቻቸው ላይ እንዲደርሱ እንደማይፈልጉ እሙን ነው! ከባዕድ አምልኮ ጋር ንክኪ ያለው የመሆኑ ጉዳይም በቁም ነገር ሊታሰብበት ይገባል።
5 ግርዛት በሴቶች የጾታ ፍላጎት ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ያሳድራል፤ ይሖዋ ሴቶች ከባሎቻቸው ጋር በሚያደርጉት የጾታ ግንኙነት እንዲደሰቱ አድርጎ ፈጥሯቸዋል። ሴት ልጅ የምትገረዘው እስክታገባ ድረስ ድንግልናዋን ጠብቃ እንድትቆይ ለማድረግ ሲባል እንደሆነ ይነገራል። ይሁንና አንዲት ልጅ፣ ድንግል ሆና እንድትቆይ የሚረዳት አካሏ መቆረጡ ሳይሆን በክርስቲያናዊ መመሪያዎች ተኮትኩታ ማደጓ ነው። የጥቅምት 1993 ንቁ! መጽሔት እንደሚከተለው ይላል:- “መጥፎ ድርጊቶች ሊወገዱ የሚችሉት የአካል ክፍልን በመቁረጥ ሳይሆን ትምህርት በመስጠት ነው። በምሳሌ ለማስረዳት:- ሕጻናት ወደፊት ሌቦች እንዳይሆኑ ለማድረግ እጃቸውን መቁረጥ ይኖርብናልን? ወይም መጥፎ ነገሮች ፈጽሞ እንዳይናገሩ ምላሳቸውን መቁረጥ ይገባናልን?” ሴት ልጅን መግረዝ አደገኛ ሲሆን የደም ባለዕዳ ወደ መሆንም ሊመራ ይችላል።—1 ዜና 11:17-19፤ መዝ. 51:14
6 እንዲህ ያለውን የጭካኔ ድርጊት የሚደግፍ ማንኛውም ሰው ‘የበጎ ስጦታና’ “የሕይወት ምንጭ” ለሆነው ለይሖዋ አክብሮት እንደሌለው ያሳያል። (መዝ. 36:9፤ ያዕ. 1:17) ድርጊቱ በአገራችን ሕገ ወጥ እንደሆነ ተደርጎ መታየቱ ክርስቲያን ወላጆች ከዚህ ልማድ እንዲርቁ የሚያደርግ ተጨማሪ ምክንያት ይሆንላቸዋል። ክርስቲያኖች እንደመሆናቸው መጠን መንግሥት የሚያወጣቸውን ሕጎች ማክበር ይኖርባቸዋል። (ሮሜ 13:1) ሴቶች ልጆቻቸውን የሚያስገርዙ ክርስቲያኖች በጉባኤ ውስጥ ለሚገኙት ልዩ የአገልግሎት መብቶች ብቁ አይሆኑም። እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት እንዲፈጸምባት ፈቃደኛ ለምትሆን እህትም ቢሆን ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።
7 ይሖዋን በማያውቅ ሕዝብ መካከል ሆነን እርሱን በማገልገል ስንመላለስ ከግርዘት ጋር የተያያዙ አንዳንድ ችግሮች ያጋጥሙን ይሆናል። ያም ሆኖ ይሖዋን የሚያስከብር አኗኗር በመምራት ራሳችንን ‘በእግዚአብሔር ፍቅር እየጠበቅን የዘላለም ሕይወትን እንጠባበቃለን’።—ይሁዳ 21፤ 2 ጴጥ. 3:13