ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ ተከተሉ
1. ኢየሱስ ምን ምሳሌ ትቷል?
1 ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ላይ በምንካፈልበት ወቅት የእኛ ምሳሌነት በሚመለከቱን ሰዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ማስታወስ አለብን። ኢየሱስ በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ አስተምሯል። ኢየሱስን ይመለከቱ የነበሩ ሰዎች ቅንዓቱን፣ ለሰዎች የነበረውን ፍቅር፣ የአባቱን ስም ለማስቀደስ የነበረውን ከፍተኛ ፍላጎትና የአባቱን ፈቃድ ለማከናወን የነበረውን ቁርጥ አቋም ማስተዋል ይችሉ ነበር።—1 ጴጥ. 2:21
2. የእኛ ምሳሌነት አብረውን በሚያገለግሉ ወንድሞችና እህቶች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
2 ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል:- እንደ ኢየሱስ ሁሉ የእኛም ምሳሌነት አብረውን በሚያገለግሉ ወንድሞችና እህቶች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። በአገልግሎት በቅንዓት ስንካፈል የሚመለከቱ አዲሶች እንዲሁም ብዙም ልምድ የሌላቸው አስፋፊዎች እነሱም በስብከቱ ሥራ ስለሚያደርጉት ተሳትፎ ጥራት ቆም ብለው እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል። ደስታችንንና ለሌሎች ያለንን ልባዊ አሳቢነት ሲመለከቱ በአገልግሎታቸው እንዲህ የመሰሉ ባሕርያትን የማንጸባረቁን አስፈላጊነት ያስታውሳሉ። መጽሐፍ ቅዱስን በመጠቀም፣ ተመላልሶ መጠየቆችን በማድረግና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በመምራት ረገድ የምናሳየውን ትጋት ሲመለከቱ እነሱም ተመሳሳይ ነገር ለማድረግ ይነሳሳሉ።
3. የእኛ ምሳሌነት ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን የሚያሠለጥናቸው እንዴት ሊሆን ይችላል? ምንስ ሊማሩ ይችላሉ?
3 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስንመራ:- የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን በተለይ ባሕርያችንን ይመለከታሉ። ለምሳሌ ያህል ለጥናቱ ተዘጋጅቶ የመምጣትን፣ ጥቅሶችን አውጥቶ የማንበብንና ቁልፍ የሆኑ ነጥቦች ላይ የማስመርን አስፈላጊነት አስረድተናቸው ሊሆን ቢችልም እኛ ራሳችን መዘጋጀት አለመዘጋጀታችንን ይመለከታሉ። (ሮሜ 2:21) ከእነሱ ጋር ለማጥናት የተቀጣጠርንበትን ሰዓት የምናከብር ከሆነ እነሱም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸውን ሌሎች እንቅስቃሴዎች እንዳያደናቅፉባቸው ጥረት ያደርጋሉ። በተጨማሪም አገልግሎታችንን ለማከናወን ስንል የምንከፍለውን መሥዋዕትነት እንዲሁም ያለንን ጠንካራ እምነት እንደሚመለከቱ ምንም ጥርጥር የለውም። የኢየሱስን ምሳሌ በጥብቅ የሚከተሉ አስጠኚዎች ያሏቸው ተማሪዎች ብዙውን ጊዜ ቀናተኞችና ውጤታማ ወንጌላውያን መሆናቸው ምንም አያስገርምም።
4. በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ የእኛ ምሳሌነት ለሌሎች ምን ትምህርት ይሰጣል?
4 በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ:- በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ሁሉ በስብሰባዎች ላይ ምሳሌ በመሆን ሌሎችን በማስተማር ረገድ የበኩላቸውን ድርሻ ማበርከት ይችላሉ። በስብሰባዎች ላይ መገኘት የጀመሩ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ጉባኤ ውስጥ ግሩም ምሳሌ የሚሆኑ ወንድሞችንና እህቶችን በመመልከት ጥቅም ያገኛሉ። እነዚህ ሰዎች በወንድሞች መካከል ያለውን ሞቅ ያለ ፍቅርና ክርስቲያናዊ አንድነት እንዲሁም በአለባበስና በአጋጌጥ ረገድ የሚያሳዩትን ልከኝነት ይመለከታሉ። (መዝ. 133:1) ከዚህም በተጨማሪ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን በመገኘትና በምናደርገው ተሳትፎ አማካኝነት ስለ እምነታችን ምሥክርነት በመስጠት የምንተወው ምሳሌ ከሌሎች እይታ የተሰወረ አይደለም። በአንዱ ስብሰባችን ላይ የተገኘ አንድ ሰው አንዲት ትንሽ ልጅ የሚጠቀሰውን ጥቅስ ከራሷ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ በፍጥነት ስታወጣ እንዲሁም ጥቅሱ ሲነበብ በትኩረት ስትከታተል ተመለከተ። ከእሷ እንዲህ ያለ ነገር ማየቱ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ጥያቄ እንዲያቀርብ ገፋፍቶታል።
5. የእኛ ምሳሌነት ያለውን ጠቀሜታ ፈጽሞ አቅልለን መመልከት የሌለብን ለምንድን ነው?
5 ቅዱሳን መጻሕፍት አንዳችን የሌላውን መልካም ምሳሌ እንድንኮርጅ ያበረታቱናል። (ፊልጵ. 3:17፤ ዕብ. 13:7) በመሆኑም ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ በጥብቅ የምንከተል ከሆነ ሌሎች ይህንን እንደሚመለከቱና በእነሱ ላይ በጎ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ማስታወስ ይኖርብናል። ይህን በመገንዘብ በ1 ጢሞቴዎስ 4:16 ላይ የሚገኘውን “ለሕይወትህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ” የሚለውን ሐሳብ ልብ እንበል።