የአውራጃ ስብሰባ ማሳሰቢያዎች
◼ ሰዓት፦ ፕሮግራሙ በሦስቱም ቀናት ከጠዋቱ 3:20 ላይ ይጀምራል። የመሰብሰቢያ ቦታው በር የሚከፈተው ከጠዋቱ 2:00 ላይ ነው። የመክፈቻ ሙዚቃው መሰማት ሲጀምር ሁላችንም ቦታ ቦታችንን መያዝ ይኖርብናል። ይህም ስብሰባውን ሥርዓት ባለው መንገድ ለመጀመር ያስችላል። ፕሮግራሙ ዓርብ እና ቅዳሜ 10:55 እንዲሁም እሁድ 10:00 ላይ ይደመደማል።
◼ ጥምቀት፦ አንድ ሰው ራሱን ለይሖዋ መወሰኑን ለሕዝብ የሚያሳይበት ይህ ሥነ ሥርዓት ምን ያህል ክብደት እንደሚሰጠው ወላጆች ለትንንሾቹም ሆኑ ከፍ ላሉት ልጆቻቸው በሚገባ እንዲያስገነዝቧቸው እናበረታታቸዋለን። ይህን ማድረጋችሁ ጥምቀት አስደሳች ወቅት ቢሆንም በተጠማቂዎች ላይ መሳቅ ተገቢ አለመሆኑን ትንንሽ ልጆችም እንኳ ሳይቀሩ እንዲገነዘቡ ያስችላቸዋል።
◼ መኪና ማቆሚያ፦ የአውራጃ ስብሰባ በምናደርግባቸው ቦታዎች የሚገኙ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራዎች በእኛ ኃላፊነት ሥር ከሆኑ መኪና ለማቆም ክፍያ የማይጠየቅ ከመሆኑም በላይ መጀመሪያ ለመጣው ቅድሚያ በመስጠት መኪናዎቹ ሁሉ እንደ አመጣጣቸው እንዲስተናገዱ ይደረጋል።
◼ መቀመጫ መያዝ፦ መቀመጫ መያዝ የሚቻለው አብረዋችሁ ለሚኖሩና ከእናንተ ጋር በመኪና ለሚመጡ ሰዎች ብቻ መሆኑን አስታውሱ።
◼ ምሳ፦ በእረፍት ሰዓት ምግብ ፍለጋ የስብሰባውን ቦታ ትታችሁ ከመሄድ ይልቅ እባካችሁ ምሳ ይዛችሁ ኑ። በመቀመጫችሁ ሥር ሊቀመጥ የሚችል መጠነኛ ዕቃ መጠቀም ይቻላል። ትላልቅ ዕቃዎችን፣ ጠርሙስ ነክ ዕቃዎችንና የአልኮል መጠጦችን ወደ ስብሰባው ቦታ ማምጣት አይፈቀድም።
◼ መዋጮ፦ በመንግሥት አዳራሽም ሆነ በአውራጃ ስብሰባ ላይ ለዓለም አቀፉ ሥራ በፈቃደኝነት መዋጮ በማድረግ አድናቆታችንን ማሳየት እንችላለን።
◼ አደጋዎችና ድንገተኛ ሕመም፦ አንድ ሰው በስብሰባው ቦታ ላይ ድንገተኛ ሕመም ካጋጠመው የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ መስጫ ክፍል የሚገኝበትን ቦታ እንዲጠቁማችሁ በቅርብ ያለውን አስተናጋጅ አነጋግሩ።
◼ ቅጾች፦ እባካችሁ ተከታትላችሁ እርዱት (S-43) የሚለው ቅጽ በስብሰባው ላይ መደበኛ ባልሆነ መንገድ መሥክረንለት ፍላጎት ስላሳየ ሰው መረጃ ለመስጠት ያገለግላል። ቅጹን ከሞላችሁ በኋላ ለአውራጃ ስብሰባው የጽሑፍ ክፍል አሊያም ወደ ጉባኤያችሁ ስትመለሱ ለጉባኤው ጸሐፊ ልትሰጡት ትችላላችሁ።